1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራንና የዩናይትድ ስቴትስ ዉዝግብ

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2011

ዩናይትድ ስቴትስ «ለኢራን ግልፅ መልዕክት» ለማስተላለፍ ያለችዉን ዘመቻ ከፍታለች።አብረሐም ሊንከን የተባለችዉ አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ መካከለኛዉ ምስራቅ ቀዝፋለች።ዩናይትድ ስቴትስ ከመርከቡ በተጨማሪ ቢ52 ቦምብ ጣይ ግዙፍ አዉሮፕላኖችዋንን እና ተጨማሪ ፓትርየት የተባለ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ አዝምታለች።

https://p.dw.com/p/3IR3x
U.S. Air Force - B-52 und F-16
ምስል picture alliance/Newscom/U.S. Air Force/Senior Airman Erin Babis

የኢራን እና የአሜሪካ ፍጥጫ

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት የዶናልድ ትራምፕ የፀጥታ አማካሪ ጆን ቦልተን ቀን ቆርጠዉ ፎክረዉ ነበር።«የ1979ኙ የአያቶላሕ ሆሚኒ አብዮት 40ኛ ዓመቱን መድፈን አይችልም።»ፓሪስ ኃምሌ 2017 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የኢራን እስላማዊ አብዮት ባለፈዉ የካቲት አርባኛ ዓመቱን ደፍኗል።እና ቦልተን የቆረጡት ቀን ስቷል።ፉከራ፣ የጦር ዝግጅት፣ዘመቻዉ ግን እንደቀጠለ ነዉ።ኢራን ዳግማዊት አፍቃኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያን ትሆን ይሆን ወይስ ቬትናምን?ላፍታ እንጠይቅ።

                        

ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ጦር በ2001 አፍቃኒስታን ላይ የከፈተዉ ጦርነት የደቡብ እስያዊቱን ሐገር የሽብር፣ጥፋት፣ምስቅልቅል ማዕከል ካደረጋት አስራ-ስምተኛ ዓመቱ።የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ መሪዎች በ2003 ያስወረሯት ኢራቅ ከሐብታም፣ሥልጡን፣ ዘመናዊ አረባዊት ሐገርነት ወደ አስከሬን መከመሪያነት ከተለወጠች አስራ-ስድተኛ ዓመቷ።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ፈረንሳይና ብሪታንያ የመሩና ያቀነባበሩት ወታደራዊ ዘመቻ ሊቢያን የታጣቂዎች መፈልፈያ፣የወሮበሎች መፈንጪያ፣ የስተደኞች መሰቃያ ካደረጋት ስምተኛ ዓመትዋ።የዋይት ሐዉስ መሪዎችና የአረብ ተከታዮቻቸዉ ሶሪያን ከነአፍቃኒስታን፣ ኢራቅ ወይም ሊቢያ ጎራ ለመቀየጥ ሰባት ዓመት ያደረጉት ሙከራ በርግጥ ከሽፏል።ቴሕራን ላይ ግን ዓመታት ያስቆጠረዉ ሴራ፣ ሙከራ፣ ፉከራዉ አላባራም።

«በዚሕ ድግስ ላይ መካፈል ከጀመርኩበት ጊዜ  ላለፉት አስር ዓመታ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ግልፅ መርሕ የቴሕራን ሙላሆች ሥርዓት የሚያስወግድ መሆን እንዳለበት ስናገር ነበር።»

ጆን ሮበርት ቦልተን።ከ2001 እስከ 2005 የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ የጦር መሳሪያና የፀጥታ ቁጥጥር ምክትል ሚንስትር ነበሩ።ኢራቅ ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ ታጥቃለች ብለዉ ከተሟገቱ፣ ኢራቅን ዛሬም ድረስ የሚያጠፋዉን አሜሪካንን ያከሰረዉን ወረራ በግንባር ቀደምትነት ያቀነባበሩ ፖለቲከኛ ነበሩ።

Begleitschiffe des Flugzeugträger USS Abraham Lincoln im Sueskanal vor der Küste von Ägypten
ምስል picture-alliance/Mass Communication Specialist 3r/U.S. Navy/AP/dpa

የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የፀጥታ አማካሪ ከሆኑበት ከ2018 ጀምሮ ደግሞ የሥርዓት ለዉጥ ላሉት የረጅም ጊዜ ዓላማቸዉ ስኬት ቴሕራንን ለማስወረር እየባተሉ ነዉ። ለአሜሪካዉ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴ (ሴናተር) ለበርኒ ሳንደርስ ግን የቦልተን ግፊት ጥረት የዳግም ጥፋት ዝግጅት ነዉ።

« ሰዉዬዉ (ቦልተን) የፕሬዝደንት ጆርጅ ቡሽ ቁልፍ አማካሪ በነበሩበት ወቅት ኢራቅ ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ አላት በሚል ሰበብ (ቡሽ) ኢራቅን እንዲወርሩ ያሳሰቡ ናቸዉ።አብዛኛዉ አሜሪካዊ አሁን እንደሚያዉቀዉ በዚች ሐገር ዘመናይ ታሪክ ከፍተኛ ጥፋት ያሰደረሰ የዉጪ መርሕ ነዉ።4 400 የአሜሪካ ወታደሮች፣ ጀግና ወታደሮች አጥተናል።31 ሺሕ ቆስለዋል።ግማሽ ሚሊዮን ኢራቃዉያን ተገድለዋል።--- እንዳለመታደል ሆኖ ለሁሉም ነገር መፍትሔዉ ጦርነትና ወታደራዊ እርምጃ ነዉ ብለዉ የሚያስቡ ሰዎች ዋሽግተን ዉስጥ አሉ።ቦልተን አንዱ ናቸዉ።»

ሳደርስ እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስ በኢራቅና በአፍቃኒስታኑ ጦርነት ብቻ ከ2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ከስራለች።ይሁንና  ቦልተንን መሰል ፖለቲከኞች የተጠራቀሙበት የፕሬዝደንት ትራምፕ ኢራንን በኃይል ለማንበርከክ የቆረጠ መስሏል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ የኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብር ለማስቆም በፀጥታዉ ምክር ቤት  ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ አምስቱ ሐገራትና ጀርመን ከኢራን ጋር ያደረጉትን ዉል ካፈረሱ ወዲሕ በዳግም ማዕቀብ ያዘገመዉ የማንበርከክ ዝግጅት ሰሞኑን ወደ ጦር ዘመቻ ንሯል።ባለፈዉ ሚያዚያ 29 (21 በኢትዮጵያ) የትራምፕ የፀጥታ አማካሪ ጆን ቦልተን፣ የሐገሪቱን ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (CIA) ኃላፊን፣ የዉጪ ጉዳይ ሚንስርን፤ የብሔራዊ የስለላ ድርጅት ኃላፊን፣ ተጠባባቂ መከላከያ ሚንስትርንና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዞር ሹሞች ሊቀመንበርን ሰብስበዉ ነበር።ብዙ ያልተለመደዉ ስብሰባ ዓላማ ኢራን በዩናይትድ ስቴትስና በተባባሪዎች ላይ ጥቃት ታደርሳለች የሚል መረጃ ሥለደረሰን» ከሚል በስተቀር ዝርዝሩ አልተነገረም።

ከስብሰባዉ በኋላ ግን ዩናይትድ ስቴትስ «ለኢራን ግልፅ መልዕክት» ለማስተላለፍ ያለችዉን ዘመቻ ከፍታለች።አብረሐም ሊንከን የተባለችዉ አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ መካከለኛዉ ምስራቅ ቀዝፋለች።ዩናይትድ ስቴትስ ከመርከቡ በተጨማሪ ቢ52 ቦምብ ጣይ ግዙፍ አዉሮፕላኖችዋንን እና ተጨማሪ ፓትርየት የተባለ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ አዝምታለች።

ዩናይትድ ስቴትስ በአስራ-ሁለት የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐገራት ዉስጥ እስከ አፍንጫዉ የታጠቀ 52 ሺሕ ጦር አላት።አሁን የቀዘፈችዉ መርከብ ዘጠና ተዋጊ ጄቶች ወይም ሔሊኮፕተሮች ትሸከማለች። ከሰወስት ኳስ ሜዳ የምትበልጠዉ «መለስተኛ ደሴት» ፣ ጄት አብራሪዎቹን ጨምሮ ስድስት ሺሕ ያሕል ተዋጊዎችን ታሳፍራለች።

ቢ 52 የተባለዉ ተዋጊ አዉሮፕላን ስምንት ሚሳዬል ማወንጨፊያዎች፣ እያንዳዳቸዉ 500 ፓዉንድ የሚመዝኑ ሐምሳ አንድ ቦምቦች፣ አንድ ሺሕ ፓዉንድ የሚመዝኑ 30 ቦምቦች፣ ሌሎች 24 የሩቅ ርቀት መሳሪያዎች ተሸክሞ አየር ላይ መክነፍ ይችላል።

Iran | Präsident Hassan Rohani
ምስል picture-alliance/abaca/Parspix

ለአሜሪካኖች የጦር ድግስ እስካሁን ከኢራን እንደ አፀፋ የተቆጠረዉ የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ሐሰን ሩሐኒ መንግስታቸዉ በ2015 ከተፈረመዉ የኑክሌር ስምምነት (JCPOA) የተወሰኑትን ለማጠፍ ለተፈራራሚዎች የሰጡት ቀነ-ገደብ ነዉ።ሩሐኒ ባለፈዉ ሮብ እንዳሉት አምስቱ ሐገራት፣ በስምምነቱ መሠረት ኢራን የነዳጅ ዘይት እንድትሸጥና የባንክ ግንኙነተቿ እንዲቀጥሉ ማድረግ አለባቸዉ።

                                           

ሩሲያና ቻይና የኢራንን ጥያቄና ማስጠንቀቂያ የተቀበሉት መስለዋል።የሁለቱ ሐገራት ባለስልጣናት በየፊናቸዉ እንዳሉት ዉዝግቡ ዳግም ያገረሸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ስምምነቱን ሥላፈረሰች ነዉ።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እንዳሉት ዩናይትድ ስቴትስ ያፈረሰችዉ በመንግሥታት መካከል የተደረገ ስምምነትን ብቻ አይደለም።የፀጥታዉ ምክር ቤትን ያፀደቀዉን ዉሳኔ ጭምር እንጂ።

«እንደሚገባኝ ዋና ምግባራችን JCPOAን በተመለከተ ሥላጋጠመን ተቀባይነት ስለሌለዉ ሁኔታ መነጋገር ነዉ።(ችግሩ) የተፈጠረዉ በዩናይትድ ስቴትስ ኃላፊነት የጎደለዉ ባሕሪ ምክንያት ነዉ።በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የተለያዩ ደንቦች መሠረት የፀደቀዉን ስምምነት ጥሳ ግዴታዋን አፍርሳለች።»

የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ጌንግ ሹዋንግም ተጠያቂ ያደረጉትን ዩናይትድ ስቴትስን ነዉ።ቃል አቀባዩ ዉጥረቱን ማርገቢያዉ ድርድር ነዉ ባይ ናቸዉ።

«ያሁኑ ዉጥረት የተከሰተዉ ዩናይትድ ስቴትስ ከአጠቃላዩ ስምምነት መዉጣትዋና በተናጥል ማዕቀብ በመጣልዋ ምክንያት ነዉ።በጣም ያሳዝናል።ግጭትና ፍጥጫ ከችግሩ መዉጪያ ዘዴ እንዳልሆነ በድጋሚ ማስታወቅ እፈልጋለሁ።ብቸኛዉ መፍትሔ ድርድርና ምክክር ነዉ።»

የትራም ዉሳኔ አጣብቂኝ ዉስጥ የከተተዉ የአዉሮጳ ሐገራትን ነዉ።«ትራምፕ በየመስኩ የሚወስዱት የተናጥል እርምጃ «ላም እሳት ወለደች» አይነት የሆነባቸዉ አዉሮጶች ለገቡት ቃል፣ለፈረሙት ዉል፣ ከሁሉም በላይ ለዓለም ሰላም የመቆም ሐቅን ከትራምፕዋ ዩናይትድ ስቴትስ ከመሰለፍ «ሸፍጥ» መሐል አንዱን መምረጥ ተስኛቸዉ ግራ ቀኝ እየዋዠቁ ነዉ።

የፓሪስ፣የለንደንና የበርሊን መሪዎች ለኢራኑ ፕሬዝደንት ማስጠንቀቂያ የሰጡት መልስም ለየቅል ነዉ።ይሁንና ሁሉም ስምምነቱ መፍረስ የለበትም በሚለዉ ሐሳብ ቢያንስ እስካሁን አንድ ናቸዉ።ሶስቱ መንግስታት ብቻ ሳይሆኑ የአዉሮጳ ሕብረት ባጠቃላይ ስምምነቱ እንዲከበር ይሻል።የሕብረቱ የዉጪ ግንኙነት የበላይ ፌደሪካ ሞግሕሪኒ ዛሬ እንዳሉት ስምምነቱ ለአካባቢዉ ሰላም መሰረት ነዉ ብለዉ ያምናሉ።

USA UN Botschafter John bolten tritt zurück
ምስል AP

                             

«ከኢራን ጋር የተደረገዉን የኑክሌር ስምምነት ሙሉ በሙሉ መደገፋችንን ፣ገቢራዊ እንዲሆን መጣራችንንም እንቀጥላለን።ስምነቱ ለአካባቢያችን ፀጥታና ደሕንነት ዋና መሠረት ነዉ።ለኛ ዓለምን ከኑሌር ቦምብ የማፅዳት እርምጃ ዋና ክፍል ነዉ።አካባቢያችንም መላዉ ዓለምንም ከኑክሌር ስጋት ለማፅዳት ለሚደረገዉ ጥረት አብነት ነዉ።»

ስምነቱ ለዓለም ሠላም ሞግሕሪኒ ያሉትን ያክል ከጠቀመ ስምምነቱን የሚያፈርሱ ወይም የሚፃረሩ ወገኖች የዓለምን ሠላም እያደፈረሱ ነዉ ማለት-ነዉ ተጠየቃዊዉ ግንዛቤ።የጠየቀ ፖለቲከኛ ግን ቢያንስ እስካሁን በይፋ አልተሰማም።የተሰማዉ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ዛሬ ብራስልስ ዉስጥ ከዩናይትድ ስቴትሱ አቻቸዉ ማይክ ፖምፒዮ ጋር ባደረጉትን ዉይይት ይህንኑ አቋማቸዉን አንፀባርቀዋል መባሉ ነዉ።

ፖምፒዮ፣ ጆን ቦልተን በመሩት ስብሰባ ላይ የሐገራቸዉ ተጨማሪ ምርጥ ጦርና መሳሪያ ወደመካከለኛዉ ምሥራቅ እንዲዘምት ከወሰኑ በኋላ ለንደንን፣ ባግዳድን ዛሬ ደግሞ ብራስልስን ጎብኝተዋል።ጉብኝቱ የጦር ዝግጅቱ-አካል ይሁን ሌላ በርግጥ አለየም።የለየዉ የአዲስ ድርድር መልዕክት እንዳልሆነ ለብዙዎች ግልፅ መሆኑ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ