1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ ቴሌኮም የታሪፍ ቅነሳና የሞባይል ቀፎዎች ምዝገባ መነሳት

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ ነሐሴ 18 2010

ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጣቸው የተለያዩ የስልክ አገልግሎቶች ላይ የዋጋ  ቅናሽ ማድረጉን አስዉቋል። ይህም ተጠቃሚ የሚያደርገዉ ሞባይልን ለስልክ ጥሪ፣ ለአጭር የጽሁፍ መልዕክትና ለእንቴርኔት ለሚጠቀሙ ሁሉም የማህበረሰብ አካል ቢሆንም  በተለይ ወጣቶች ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያስረዳሉ።

https://p.dw.com/p/33ilz
Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

የሞባይል ታሪፍ ቅነሳ

ቅናሹ የታወጀዉ የኢትዮ ቴሌኮም ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ባለፈዉ ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነዉ። በዚሁ መሠረት በሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት የ43 በመቶ፣ በሃገር ውስጥ የሞባይል ድምጽ ጥሪ 40 በመቶ እንዲሁም በአጭር የሞባይል የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎት ላይ የ43 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል።የዋጋ ቅናሹም ከማክሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል። ይህም በገንዘብ ሲሰላ ቀደም ሲል «በደቂቃ 83 ሳንቲም የነበረው የሞባይል ስልክ ጥሪ አገልግሎት ወደ 50 ሳንቲም ዝቅ መደረጉን፣ በሜጋ ባይት 35 ሳንቲም የነበረው የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ወደ 23 ሳንቲም ዝቅ መደረጉን  አጭር የጽሁፍ መልዕክትም ከቀድሞው ክፍያ 35 ሳንቲም አሁን 20 ሳንቲም መሆኑ ተዘግበዋል።

ይህም ተጠቃሚ የሚያደርገዉ ሞባይልን ለስልክ ጥሪ፣ ለአጭር የጽሁፍ መልዕክትና ለእንቴርኔት ለሚጠቀሙ ሁሉም የማህበረሰብ አካል ቢሆንም በተለይ ወጣቶች ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያስረዳሉ። መቀመጫዉን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገዉ በዓለም አቀፍ አመለካከቶች እና አዝማሚያዎች /Global Attitudes & Trends/ ላይ ምርምር የሚያካህደዉ  ተቋም በኢትዮጵያ የስልክ ቀፎ ያላቸዉና እንቴርኔት የሚጠቀሙት አብዛኛዎቹ ሰዎች በ18-34 የእድሜ ክልል ዉስጥ እንደምገኙ ይጠቅሳል።

በዚህ እድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙት አዲሱን የዋጋ ቅናሽ  እንዴት ይመለከቱታል? በምዕራብ ሸዋ በልባን-ጃዊ ወረዳ የባብች ከተማ ነዋሪ መሆኑን የሚናገረዉ ተስፋዬ ጥላሁን የኢትዮ ቴሌኮም ርምጃን በበጎ ይመለከተዋል። የባቱ (ዝዋይ) ነዋሪ የሆነዉ ሌልሳ ባጫ በበኩሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዉሳኔ የደሃዉን ህብረተሰብ ያማከለ ነዉ ይላል። ስለዚህ የኢትዮ ቴሌኮም የወሰደዉን ዓይነት ርምጃ የመብራት ኃይልና የመጠጥ ዉሃ አጋልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም መዉሰድ እንደሚገባቸዉ  ላልሳ አሳስበዋል።

Äthiopien: IT Entwickler helfen bei Hausaufgaben
ምስል DW/N. Schwarzbeck

ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጣቸው የስልክ ኢንተርኔት፣ በድምጽ ጥሪ እና በሞባይል አጭር የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎቶች ላይ ቅናሽ ማድረጉ አንድ ግለሰብን ከመጥቀም አልፎ ራሱን ኢትዮ ቴሌኮምንና ሐገሪቱን በኢኮኖሚ ረገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ «አይስ አዲስ» የተሰኘው የቴክኖሎጂ ድርጅት መስራች ማርቆስ ለማ ይናገራል። የኢትዮ ቴሌኮም ርምጃ መረጃ መለዋወጥን ስለሚያቀል አበረታች ነዉ የሚለዉ ደግሞ በድሬ ዳዋ ከተማ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጠበቃ ታረቀኝ አለማየሁ ነዉ።

ጅግጅጋ በነበረዉ የፀጥታ ችግር ምክንያት የኢንቴርኔት አገልግሎት በሐገሪቱ ምስራቅ ክፍል ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ ተቋርጦ እንደሚገኝ በድሬ-ዳዋ ከተማ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጠበቃ የሆነዉ ታረቀኝ አለማየዉ ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል። ድሬ-ዳዋ ከተማ እንደምትገኝ የተናገረችዉ ጦማሪና የሰብአዊ መብት ተከራካር ማህሌት ፋንታሁንም የኔትዎርኩ መቋረጥ በኢንቴርኔት ላይ የተደረገዉን  ማሻሻያ ለመፈተሽ እንዳላስቻላት አክላበታለች።

ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ቀፎዎች በኔትዎርኩ እንዲመዘገቡ ማዘዙ ይታወሳል።ይሕን ርምጃን በተመለከተም ብዙ ነጋዴዎች ከሥራ ውጭ መሆናቸዉን፣ ተጠቃሚዎችም እንደ ልባቸዉ ቀፎ ማግኘት እንዳልቻሉ ሲዘገብ ነበር። የሞባይል ቆፎ ምዝገባዉም ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት ወደ 300 ሚሊዮን ብር ገቢ የሚያስገኝለት ቢሆንም «የደንበኞች ቅሬታ ከቢልዮን ብር በላይ በመሆኑና ፍላጎታቸዉ በመገፋቱ» ምዝገባዉ እንዲቋረጥ ተደርጓል ሲሉ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሃመድ