1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእርቀ ሰላም ጉባዔዉ ጀምሮአል

ዓርብ፣ ሐምሌ 13 2010

ለሁለት የተከፈሉትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ሲኖዶሶች ለማቀራረብ የተጀመረዉ ጥረት ዛሬ በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ላይ እንደሚጀምር የጠበቃል። ለአስር ቀናት እንደሚዘልቅ በተነገረዉ ጉባዔ የሚሳተፉ የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ ተወካዮችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አግኝተው አወያይተዋል።

https://p.dw.com/p/31maB
Kirche in Äthiopien
ምስል AP

«ምዕመኑ በትግስትና በፀሎት መጠበቅ ይኖርበታል»

በሀገር ውስጥና በውጭ ባሉት ሁለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ሲኖዶሶች መካከል እርቀ ሰላም ለማውረድ ዳግም ጥረት ተጀምሮ እየተካሄደ ነው። ከዓለም ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት አንዷ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕድሜ ዘመኗ እጅግ ብዙ ፈተናዎችን ማለፏን ታሪኳን ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ ይናገራሉ። በቤተ-ክርስትያኒቱ የተፈጠረው መከፈል፤ በሀገር ውስጥና በውጭ በሚንቀሳቀሱ ሁለት ሲኖዶሶች መለያየት የሃይማኖት አባቶችን ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስትያኒቱን ምዕመናን ሲያሳስብ የቆየ ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያኗ የተለያዩ ፈተናና ችግሮችን እያሳለፈች መምጣቷ ቢነገርም ላለፉት 27 ዓመታት እንደሆነው ግን ለሁለት የተከፈለችበት ታሪክ አለመኖሩም ሌላው ሊጠቀስ የሚገባ ነጥብ ነው። በሁለቱም ጎራ ያሉ አባቶችን ለማቀራረብና የቤተ ክርስቲያኒቷንም አንድነት በተደጋጋሚ በተለያዩ ጊዜዎች ጥረቶች  መደረጋቸዉን የሚናገሩት በኔዘርላንድ ነዋሪ የሆኑት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ- ክርስትያን ሁለተኛ ዙር የሰላም እና የአንድነት ጉባዔ አባል ዲያቆን ማንያዘዋል አበበ እንደሚሉት ጉባኤዉ በሁለቱም ጎራ በተለያየ መዋቅር የሚያገለግሉ፤ ካህናት ምዕመናንን ያቀፈ ጉባዔ ነው።

«ይህ ጉባዔ ጉባዔ ነዉ መጠርያ ስያሜዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ- ክርስትያን ሁለተኛ ዙር የሰላም እና የአንድነት ጉባዔ ነዉ የሚባለዉ ። በአዉሮጳ በካናዳ እና በአሜሪካ የሚገኙ አሁን በተፈጠረዉ አሳዛኝ ክስተት ምክንያት በሁለቱም ጎራ በተለያየ መዋቅር የሚያገለግሉ ካህናት ፤ ምእመናን ያቀፈ ጉባዔ ነዉ። በተጨማሪም በአዉሮጳና በሰሜን አሜሪካ የማስተባበርያ ቅርንቻፍ ጽ/ቤት የዚሁ ስያሜ አለዉ፤ በኢትዮጵያ በኩል ያለዉን ነገር የሚከታተል፤ እንደዚሁ እራሱን የቻለ ቅርንጫፍ አለዉ። ይሄ ጉባዔ መቼ ተጀመረ የሚለዉን እርግጠኛዉን ለመናገር አስቸጋሪ ቢሆንም የጎላዉን ለመግለፅ ያህል ግን በትንሹ ሁለት ዓመት ያስቆጠረ ነዉ። በዋነኝነት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ፤ መተዳደርያ ደንቡን አዘጋጅቶ፤ አባላትን መልምሉ አደራጀትን ከጨረሰ በኋላ ፤ ራሱን ገልጦ በሁሉቱ ፓትሪያሪኮች እና ፤ በሁለቱ ሲኖዶሶች እዉቅና እንዲሰጠዉ፤ የጠየቀዉ የዛሬ ዓመት ሐምሌ ነዉ። እንግዲህ ከዝያ በኋላ በተከታታይ በጥቅምት ሲኖዶስ ከዝያም በኋላ በተለያዩ አስቸኳይ ስብሰባዎች እንደገናም አሁን በመደበኛዉ በግንቦት ሲኖዶስ ይሄንኑ ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶአል። በርግጥ ጉባዔዉ ቅድመ ዝግጅቱን ያጠናቀቀዉ የዛሬ ዓመት ሐምሌ ላይ ነዉ። ከጉባዔዉ ወገን ሳይሆን ከሌላ አካላት መm።ላት የሚገባቸዉ ነገሮች መሟላት ባለመቻላቸዉ እስካሁን ቆይቶአል። አሁን ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ጉባዔ ፤ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር ወይም ወደ ሁለት ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ጥረት ካደረገ በኋላ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ እንደ ቤተ-ክርስትያኒቱ አቆጣጠር ከሐምሌ ሚካኤል እስከ ሐምሌ ማርያም ማለትም ከሐምሌ 12 እስከ ሐምሌ 19 ጉባዔዉ ይካሄዳል።     

አዜብ ታደሰ

ተስፋለም ወልደየስ