1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ጭማሪ ማሽቆልቆል

ሰኞ፣ ኅዳር 3 2011

በኢትዮጵያ በዘንድሮዉ የበጀት ዓመት በጣም ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡን አንድ ዘገባ አመለከተ።  የኢትዮጵያ ብሄራዊ  የጥናትና የልማት ኮሚሽን ሰሞኑን ባወጣዉ ዘገባ እንዳመለከተዉ በጎርጎሮሳዉያኑ 2018 የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ የተመዘገበዉ የኢኮኖሚ እድገት ጭማሪ 7.7 ሲሆን፤

https://p.dw.com/p/37yJz
Äthiopien Windpark
ምስል Getty Images/AFP/J. Vaughn

Ethiopia Records single digit GDP growth. - MP3-Stereo

 ይህም ባለፉት ሁለት ዓስርተ አመታት ተመዘገበ ከተባለዉ በእጅጉ ያነሰ ነዉ። ያም ሆኖ ግን አማካኝ የነብስ ወከፍ ገቢ ካለፈዉ ዓመት ጋር ሲነፃፀር  ጭማሪ ማሳየቱን  የኮሚሽኑ ዘገባ አመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የዕቅድና የልማት ኮሚሽን ሰሞኑን ባወጣዉ ዘገባ ሀገሪቱ በዘንድሮዉ የጎርጎሮሳዉያኑ 2018  በጀት ዓመት 11.1 የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ዕቅድ ይዛ ነበር።ይሁን እንጅ ከታቀደው ሁለት ድጂት አሃዝ የተመዘገበዉ 7.7 ብቻ መሆኑን ነዉ ያመለከተዉ። ጉዳዩን በተመለከተ DW ያነጋገራቸዉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ጌታቸዉ ተክለማርያም እንደሚሉት ከዚህ ቀደም ተመዘገቡ የተባሉ የኢኮኖሚ እድገቶች ላይ በመንግስት፣ በዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና በባለሙያዎች መካከል አጨቃጫቂ ሆኖ የቆየ ቢሆንም  ሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ስታስመዘግብ  መቆየቷን ገልፀዋል።
በዋናነት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በግብርና ላይ ያተኮረ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሆቴል፣ የቱሪዝም፣ የሪል ስቴት እና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች በኢኮኖሚዉ ሰፊ ድርሻ እየያዙ መጥተዋል ይላሉ። ይህ የአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ የተረጋጋ አካባቢንና ሁኔታን የሚፈልግ በመሆኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገሪቱ የተከሰተዉ የፖለቲካ አለመረጋጋት ለኢኮኖሚ እድገቱ ተግዳሮት መሆኑን አቶ ጌታቸዉ ገልፀዋል። የግብርና ግብዓቶች ለገበሬዉ በጊዜ እንዳይደርሱና ያመረተዉን ምርት በአግባቡ እንዳይሸጥ በማድረግ፤ በግብርናዉ ዘርፍም አለመረጋጋቱ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱንም አመልክተዋል። 
የፖለቲካ መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ የተረጋጋ ኢኮኖሚ አይታሰብም ያሉት አቶ ጌታቸዉ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የፖለቲካ ስርዓቱ በአጠቃላይ ተፈጥረዉ የነበሩ ግጭቶችን ለማብረድ፣ ህብረተሰቡንና ፖለቲካዊ አካባቢን ለማረጋጋት ከመጣር ዉጭ  ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት የሚሆን የፖሊሲ አመራርና ድጋፍ  አለማድረጉም ለእድገቱ ማሽቆልቆል ሌላዉ ምክንያት መሆኑን ባለሙያዉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከዉጭ በምታስገባቸዉና ወደ ዉጭ በምትልካቸዉ ምርቶች መካከል ያለዉን ሚዛን በመጠበቅ ረገድም በዘንድሮዉ ዓመት የተሳካ አፈፃጸም አለመታየቱን የብሄራዊ የዕቅድና የልማት ኮሚሽን ዘገባ አመልክቷል። ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶች ከሀገሪቱ ጠቅላላላ የምርት መጠን በካፒታል 23 በመቶ ሲሆን ወደ ዉጭ የሚላኩ ምርቶች ግን 8.4 በመቶ ብቻ በመሆን ከፍተኛ ልዩነት መኖሩ ተመልክቷል። ያም ሆኖ ግን በጎርጎሮሳዊው 2017  የበጀት ዓመት በሀገሪቱ የነበረዉ 722 የአሜሪካን ዶላር አማካኝ የነብስ ወከፍ ገቢ ወደ 822 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ማለቱ ተብራርቷል። ለመሆኑ የኢኮኖሚ እድገት በሌለበት የነብስ ወከፍ ገቢ ሊያድግ ይችላልን? አቶ ጌታቸዉ ምላሽ አላቸው።
ምንም እንኳ አማካኝ የነብስ ወከፍ ገቢ የሚያድግበት ሁኔታ ቢፈጠርም  የዋጋ ንረትን በመሳሰሉ ተግዳሮቶች  የገንዘብ የመግዛት አቅም ዝቅተኛ ስለሚሆን፤ በሰዎች ህይወት ላይ የሚያመጣዉ ለዉጥ ያን ያህል እንዳልሆነ ነዉ ባለሙያዉ ይገልጻሉ። የዋጋ ግሽበትን በሚመለከትም ወደ አንድ ዲጅት አሃዝ ለማዉረድ በዚሁ በጀት ዓመት በመንግስት የታቀደ ቢሆንም እሴት ያልተጨመረበት ከፍተኛ የገንዘብ ዝዉዉር በአገልግሎት ዘርፉ መግባቱ ችግሩን እንዳባባሰዉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ አብራርተዋል።
ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ በመተግበርና ያለ አግባብ የተሰራጨዉን ገንዘብ በመሰብሰብ መንግስት የገንዘብ የመግዛት አቅምን መጨመር እንደሚችል ባለሙያዉ መክረዋል። በአጠቃላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ወቅታዊ ፣ ሀገራዊ እንዲሁም አለማቀፋዊ የኢኮኖሚ ዕድሎችንና ተግዳሮቶችን ግምት ዉስጥ ያስገባ ፈጣን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለችግሩ መፍትሄ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ አቶ ጌታቸዉ ተክለ ማርያም አስረድተዋል። 

Äthiopien neuer politischer Führer ist auf Unterstützung der Jugend angewiesen
ምስል Reuters/T. Negeri
Bees for Development Ethiopia
ምስል Bees for Development Ethiopia/Tilahun Gebey


ፀሐይ ጫኔ

ተስፋለም ወልደየስ