1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ ገበያ እና የግሉ ዘርፍ ፈተናዎች

ረቡዕ፣ ነሐሴ 16 2010

የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች የግሉ ዘርፍ በገበያው ውስጥ ያለው ሚና በግልፅ የተለየ አልነበረም፤ መንግሥት በገበያው ውስጥ ያለው ሚና ሊቀየር ይገባል ብለው ያምናሉ። የግሉ ዘርፍ የሚፈልገውን ነፃነት ቢያገኝ እንኳ ካሉበት ችግሮች አኳያ የኢትዮጵያን ፍላጎት መሙላት ይቻለዋል?

https://p.dw.com/p/33bWL
Äthiopien Wirtschaft und Privatsektor
ምስል Ethiopian Chamber of Commerce

የግሉ ዘርፍ ፈተናዎች

ኢሕአዴግ የሚያቀነቅነው የልማታዊ መንግሥት ሞዴል እና የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ገበያ የተጣጣመ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል የኢትዮጵያ ፕላኒንግ ኮሚሽነር አቶ እዮብ ተካልኝ ያምናሉ። ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ የግሉ ዘርፍ እና ወቅታዊ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ፈተናዎቹና ዕድሎቹ በሚል ርዕስ በተካሔደ ውይይት ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ እዮብ መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ግንኙነታቸውን እንደገና ሊፈትሹ እንደሚገባ ግን ጠቁመዋል። 
ኢሕአዴግ የሚያቀነቅነው የልማታዊ መንግሥት መርሕ ለግል አምራቾች፣ አስመጪ እና ላኪዎች እና አቀነባባሪዎች ቦታ የለውም እየተባለ ይወቀሳል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች በበኩላቸው የግሉ ዘርፍ በገበያው የሚፈለገውን ነፃነት ቢያገኝ የአገሪቱን የማኑፋክቸሪንግ ፍላጎት መሙላት ለመቻሉ ጥርጣሬ አላቸው። የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የተገኙ አንድ ተሳታፊ ዘርፉ ለ27 አመታት እስኪርብቶ እና ሳህን የመሳሰሉ ሸቀጦች ከመነገድ ፈቅ ማለት ተስኖታል ሲሉ ተችተዋል።
በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠን ወደ 70 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥሌት ደግሞ በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት 8.5 በመቶ ገደማ ያድጋል። በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ስንት ነው? በእርግጥ በደምሳሳው የግሉ ዘርፍ ሲባል የትኞቹን የሥራ አይነቶች ያካትታል? አቶ እዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ውስጥ ያለውን ድርሻ በግልጽ አይታወቅም።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ነጋዴዎች እና የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች መንግሥት በገበያው ውስጥ ያለው ሚና ይቀየራል የሚል ተስፋ አሳድረዋል። ኢሕአዴግ ባለፉት አመታት የወጠናቸው ግዙፍ የመሠረተ-ልማት አዉታር ግንባታዎች፣ የተከተላቸው ፖሊሲዎች እና አሰራሮች ስኬት እና ኪሳራን ገምግሞ በእርግጥ ለግሉ ዘርፍ ከፍ ያለ ዕድል ይሰጥ እንደሁ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ፕሮፌሰር ጥላዬ ካሳሁን እንደሚሉት ግን አሁን ያለው ገበያ ወደ መንግሥት ያዘነበለ ነው። ባንኮችን ጨምሮ የግል ኩባንያዎች ከመንግሥቶቹ አኳያ በገበያው ዕኩል ዕድል የላቸውም። 

በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ተመራማሪ አቶ አሚን አብደላ ይኸው የግሉ ዘርፍ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እንደነበር ይስማማሉ። እንደ አቶ አሚን ከሆነ የግሉ ዘርፍ በገበያው ውስጥ ያለው ሚና በግልፅ የተለየ አልነበረም፤ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ለዘርፍ ያላቸው አተያይ መልካም ሳይሆን ቆይቷል። 
ፕሮፌሰር ጥላዬ የኢትዮጵያ መንግሥት የልማት ድርጅቶችን ድርሻ ለመሸጥ መወሰኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በገበያው ውስጥ ያለውን ሚና ለመለወጥ ያለው ዝግጁነት ማሳያ አድርገው ይቆጥሩታል። አዲስ አበባ፣ መቀሌ እና ጅማን በመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት ያገለግሉት እና የፕሪን ኢንተርናሽናል አማካሪ ባለቤት ኢትዮጵያ በርካታ ማሻሻያዎች ልታደርግ ይገባል የሚል ዕምነት አላቸው። 


ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ 
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ