1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ያልተሳካው የኢትዮጵያ ባለወረቶች አጋር ፍለጋ

ረቡዕ፣ ግንቦት 30 2009

የሥራ አጋር ፤ ቴክኖሎጂ እና ክህሎት ፍለጋ ወደ ጀርመን ብቅ ያሉት የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በሐኖቨር እና ሽቱትጋርት ከተሞች ሥራቸውን ሲያስተዋውቁ ነበር። ሁሉም ግን እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም። 

https://p.dw.com/p/2eHj6
3. Deutsch-äthiopischer Wirtschaftstag Teilnehmer
ምስል DW/E. B. Tekle

ያልተሳካው የኢትዮጵያ ባለወረቶች አጋር ፍለጋ

የምሕንድሥና ባለሙያው መላኩ አርጋሞ ወደ ጀርመን ያቀኑት አገራቸው ያጡትን ፍለጋ ነበር። በዘመናት ሒደት የካበት እውቀት፤ የተመሰከረለት ቴክኖሎጂ እና የዳበረ ካፒታል ካለባት ጀርመን አብሯቸው የሚሠራ አጋር ይሻሉ። ግን ብቻቸውን አይደሉም። የግንባታ ኩባንያዎች ባለቤቶች አብረዋቸው ተጉዘዋል። የምግብ እና ውኃ አምራቾች ፤ አስመጪ እና ላኪዎች አብረዋቸው መጥተዋል። ተወዳጅ የኢትዮጵያ የቡና ዝርያዎችን ቆልተው እና ፈጭተው ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡትም ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ ምኞታቸው ነበር። ወኪል አከፋፋይ ከተገኘም አይጠሉም። እነ መላኩ፤ አንዋር እና አማኑኤል ዓይናቸውን የጣሉባት ጀርመን የዩሮ ሸረፍ የልብ ምት ሆናለች። ባለፈው ዓመት ከበለፀጉት የቡድን ሰባት አገሮች ፈጣን ኤኮኖሚያዊ እድገት የነበራት የምዕራብ አውሮጳዋ ጀርመን ነበረች። ባለፈው ዓመት ጀርመን ኤኮኖሚዋ 1.9 በመቶ ሲያድግ በአምስት ተከታታይ አመታት ትልቁ ነበር። ዓመቱ በአውሮጳ የግዙፍ ኤኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጀርመን የግል ዘርፍ በፍጥነት ያደገበት ነበር። አይ.ኤች.ኤስ. ማርኬት የተባለው ዓለም አቀፍ የገበያ ጥናት እና ኤኮኖሚ ትንበያ ተቋም ከጀርመን ኤኮኖሚ ሁለት ሦስተኛ ገደማ ድርሻ ያለው የግሉ ዘርፍ በመስከረም 2016 ዓ.ም. 52.8 በመቶ በዚያው ዓመት ወርኃ ጥቅምት ደግሞ 55.1 በመቶ ማደጉን አስታውቋል። 

3. Deutsch-äthiopischer Wirtschaftstag Teilnehmer
ምስል DW/E. B. Tekle

የጀርመን መንገድ

ከአስራ ሰባት አመታት በፊት አካባቢ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ጀርመንን "የአውሮጳው ገመምተኛ (በሽተኛ)" ብለው ይጠሯት ነበር። ያኔ ኤኮኖሚያዊ እድገቷ በአማካኝ 1.2 በመቶ ብቻ ሲሆን ከ9 እስከ 11 በመቶ የሚደርሰው ሕዝቧም ሥራ አጥ ነበር። ዛሬ ግን ያ ሁሉ አሁን ታሪክ የሆነ ይመስላል። ጀርመን ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ዓመታዊ የምርት መጠን እጅጉን አድጓል፤ ሥራ አጥነት ቀንሷል፤ የሠራተኞች ክፍያም ከፍተኛ ነው። 
ሥራ አጥነት በአውሮጳ በአማካኝ 21 በመቶ በነበረበት የጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. በጀርመን ወደ 4.8 በመቶ አሽቆልቁሎ ነበር። ኦስትሪያዊቷ የኤኮኖሚ ፕሮፌሰር ብሪግተ ኡንገር (Brigitte Unger) የኤኮኖሚ እድገቱ ምሥጢር በሠራተኛ ገበያው ላይ የተደረገው ማሻሻያ እና አመርቂ ክፍያ እንደሆነ ጽፈዋል። የቀድሞው የጀርመን መራሔ-መንግሥት ጌርሐርድ ሽሩደር በጎርጎሮሳዊው 2005 ዓ.ም. በሠራተኛ ገበያው ላይ ያደረጉትን ማሻሻያ ኡንገር በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ለአባሎቻቸው መብቶች ጥብቅና የሚቆሙት የሠራተኛ ማኅበራት ኩባንያዎች የአመራረት ሒደታቸውን እንዲያሻሽሉ የምርት መጠናቸውንም እንዲያሳድጉ እድል ሰጥቷቸዋል። ብሪግተ ኡንገር እንደሚሉት የጀርመን ኩባንያዎች ምርቶች በጥራት እና በዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆናቸው አገሪቱ ያካሔደቻቸው ማሻሻያዎች ላቅ ያለ ሚና አላቸው። 
የሥራ አጥነት ጉዳይ አብዝቶ እንቅልፍ የሚነሳው የኢትዮጵያ መንግሥት ታዲያ ያደጉት አገሮች ኩባንያዎች መዋዕለ-ንዋይ መፍትሔ ይሆነው ዘንድ ማፈላለግ ይዟል። በኢትዮ-ጀርመን የንግድ እና መዋዕለ ንዋይ መድረክ ላይ የተገኙት ባለሥልጣናት ባደረጓቸው ንግግሮች አገሪቱ አሏት ያሉትን ዕድል ሲያስተዋውቁ ነበር። ከልዑካን ቡድኑ መካከል የተገኙት አስመጪ እና ላኪዎችም ከጀርመናውያኑ አጋርነት መሻታቸው አልቀረም። የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ እንደ ሚሉት አገራቸው የምዕራባውያኑን ኩባንያዎች እና ባለወረቶች ቀልብ የሚገዛ ገበያ እና የንግድ ስምምነቶች አሏት
የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ባለወረቶችን ያካተተው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በጀርመኖቹ የሐኖቨር እና ሽቱት ጋርት ከተሞች በተዘጋጁ የንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ መድረኮች ተሳትፏል። በመድረኮቹ የተሳተፉት ጀርመናውያን ዋነኛ ትኩረት ያረፈው የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲዎች እና አሰራሮች ላይ ሆኖ ተስተውሏል። የመንግሥቱ ሹማምንት አገሪቱ የምትገነባቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስተዋወቅ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉም ነበር። ከሐኖቨሩ የተሻለ የውይይት መድረክ በሽቱትጋርት የገጠማቸው አቶ አማኑኤል ሳሕለ ማርያም ቆልተው ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡት ቡና የሚሆን ማሸጊያ አግኝተዋል። ቡና ነጋዴው የጀርመን ጉዟቸው ያቀዱትን ያክል አልሰመረላቸውም። ቢሆንም ቢያንስ አድራሻ መለዋወጣቸዉን ይናገራሉ።መላኩ አርጋሞ ፈጽሞ በጉዞው ደስተኛ አልነበሩም። መሰናዶውን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሥራውን በአግባቡ አልተወጣም ሲሉ ይወቅሳሉ። 
ይኸ ስሜት የአቶ መላኩ አርጋሞ ብቻ አልነበረም። አጋር፤ እውቀት እና ቴክኖሎጂ ፍለጋ ወደ ጀርመን ብቅ ብለው ያልተሳካላቸው ቅሬታቸውን ሲገልጡ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መሰል መድረኮች ሲያዘጋጅ የመጀመሪያው አይደለም። ዋና ጸሃፊው አቶ እንዳልካቸው ስሜ ዝግጅታቸው «መንገራገጮች» እንደነበሩት አይሸሽጉም። 
ምዕራባውያኑ ወደ ኢትዮጵያ ማማተራቸውን የመንግሥት ሹማምንቱም ይሁን የኤኮኖሚ ባለሙያዎቹ ይስማማሉ። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሴት ልጅ የኢቫንካ ትራምፕን ጫማዎች የሚያመርተው ሑጂያን ኢንተርናሽናል የተባለ ኩባንያ ተመሳሳይ መንገድ ለመከተል እያቀደ መሆኑን አስታውቋል። ኩባንያው ግን በቻይና የሠራተኞች መብት ተሟጋቾች ተቀጣሪዎቹን ለረጅም ሰዓታት ያለ በቂ ክፍያ ያሠራል የሚል ወቀሳ ይሰነዘርበታል። እንደ ጀርመናውያኑ ለመብቶቻቸው የሚታገል ጠንካራ የሠራተኛ ማኅበራትም ይሁን ሕግጋት በሌላት ኢትዮጵያ የምዕራባውያኑን ቀልብ የሳበው የደሞዝ ክፍያ ጉዳይ ግን አነጋጋሪ ይመስላል። 

3. Deutsch-äthiopischer Wirtschaftstag Kuma Demeksa Tokon
ምስል DW/E. B. Tekle
Bildergalerie Das Ruhrgebiet leuchtet
ምስል picture alliance/blickwinkel/S. Ziese


እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ