1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

የኢትዮጵያን የትምሕርት ሥርዓት ፖሊሲ ማሻሻያ ረቂቅ ሰነድ 

ሐሙስ፣ ነሐሴ 17 2010

በኢትዮጵያ በትምሕርት እና ሥልጠናው ዘርፍ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን በጥልቀት አጥንቶ የመፍትሄ አቅጣጫ ይጠቁማል የተባለ ረቂቅ ሰነድ በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ ለውይይት መቅረቡን የትምሕርት ሚኒስቴር አስታወቀ ::

https://p.dw.com/p/33eir
Äthiopien Symbolbild Schule
ምስል picture-alliance/KEYSTONE/D. Steinmann

የትምህርት ስርዓት

ይኸው የትምሕርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ላለፉት 20 ዓመታት ሲሰራበት የቆየውን የሃገሪቱን የትምሕርት ሥርዓት ፖሊሲ የሚቀይር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱንም በሶስት የተለያዩ ዘርፎች የሚያዋቅር መሆኑ ተጠቁሟል:: የትምሕርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ በተለይ ለዶቼቨለ እንደገለጹት የሚሻሻለው የሃገሪቱ የትምሕርት ፖሊሲ የመማር ማስተማሩን የጥራት ደረጃ ለማሻሻል እንዲሁም ሙያዊ ግዴታውን በብቃት የሚወጣ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድንም ለመፍጠር ይረዳል ::

በቅርቡ መንግሥት እንዳስታወቀው ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ገቢራዊ ሆኖ ሲሰራበት የቆየው የትምህርት ፖሊሲ በርካታ ውስብስብ ችግሮች የነበሩበት ነው :: ከአገር በቀል ዕሴቶች እና ዕውቀቶች ይልቅ ለምዕራባውያን አመለካከት እና ፍልሥፍና ትኩረት ሰቶ መቆየቱም ሃገሪቱ በቂ የተማረ እና ለውጥ የሚያመጣ ትውልድን በመቅረጽ ረገድ ያደረገችውን ጥረት በእጅጉ ጎድቶታል ተብሏል :: አጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱን የትምሕርት ተቋማቱን አደረጃጀት እና የትምሕርት ፕሮግራሞች ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት የሚያጠና ገለልተኛ ተቋም አለመቋቋሙ እንዲሁም የመምህራኑ ምልመላ እና ክህሎት ከትምህርት አሰጣጡ ጉድለት ጋር ተደማምሮ የተማሪዎች ውጤት እንዲያሽቆለቁል እና የተፈለገው ውጤት እንዳይገኝ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረጉንም መንግሥት ገልጿል:: በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት፣የመፍትሄ አቅጣጫ ለመጠቆም አዲስ የመነሻ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለውይይት መቅረቡን የኢትዮጵያ መንግሥት የትምሕርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ሃረጓ ማሞ ይገልጻሉ::
የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ዘርፉም በሁሉም አካባቢ የፍትሃዊነት እና የተደራሽነትን ጥያቄ ሊፈታ በሚችል መንገድ ትኩረት ተሰቶት ዳግም እንዲጠና ተጠይቋል :: አዲሱ የትምሕርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ረቂቅ ሰነድ ፣የትምሕርት ፖሊሲውን ለማሳለጥ የሃገሪቱን የትምሕርት ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስት ክፍሎች እንደሚያደራጅም ይጠበቃል:: እነዚህም መስሪያቤቶች የከፍተኛ ትምሕርት እና ሥልጠና ፣አጠቃላይ የትምሕርት እና ሥልጠና እንዲሁም የክህሎት እና ፈጠራ ሥራ ሚኒስቴሮች ተብለው መከፋፈላቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተዘጋጀው ውይይት ላይ ተጠቁሟል :: ወይዘሮ ሃረጓ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከመዋቅር እና አደረጃጀት አኳያ የተነሱ ችግሮች መኖራቸውን ይናገራሉ:: 
መንግሥት ከ 20 ዓመታት በላይ በተግባር ተፈትኖ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻለም ያለውን የሃገሪቱን የትምሕርት ፖሊሲ ለማሻሻል አሁን ያቀረበው የውይይት ሰነድ የአጠቃላይ ትምህርት የቴክኒክ እና ሙያ የከፍተኛ ትምሕርትን እና የትምሕርት ዘርፍ አስተዳድሩን ለመለወጥ እና ለማሻሻል የሚረዳ ነው ተብሏል :: ሃገሪቱ የቋንቋ ፖሊሲ የሌላት በመሆኑ የትምሕርት መስጫ ቋንቋዎች በተመለከተ በሂደት ሶስት ቋንቋዎችን በአጠቃላይ ትምሕርቱ ላይ የመጠቀም ዕቅድ መኖሩም ተጠቁሟል :: ብዙውን ጊዜ አከራካሪ ሆኖ የቆየው የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቆይታ ጊዜም እንደ ትምህርት ፕሮግራሞቹ ዓይነት ከ 4 ዓመት ጀምሮ ቢሆኑ የሚል የመወያያ ሃሳብ መቅረቡን የትምሕርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ሃረጓ ማሞ ጠቁመዋል:: 
ሕብረተሰቡ መምሕራን ወላጆች እና ሌሎችም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሁሉ ከመጭው መስከረም ጀምሮ ለ 6 ወራት ያህል ጥልቅ ውይይት ያደርጉበታል ተብሎ የሚጠበቀው ረቂቅ ሰነድ ወደ ሚስትሮች ምክር ቤት ተልኮ በተወካዮች ምክር ቤት ዳብሮ ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ እንደሚደረግ ታውቋል :: 

MStudenten auf dem Campus der Universität Addis Abeba
ምስል DW

እንዳልካቸው ፈቃደ

ነጋሽ መሀመድ