1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢንጂነሩ ሞት ሰበብ፤ የታማኝ ንግግር እና የራያ ጥያቄ

ዓርብ፣ ጳጉሜን 2 2010

የህዳሴው ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ራሳቸውን አጥፍተዋል መባሉ፤ አርቲስትና የመብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ በባህር ዳር ያሰማው ንግግር በሰፊው አነጋግረዋል። የራያ ተወላጆችን በተመለከተ የተሰማው ቅሬታና የትግራይ ክልል መልስ፤ እንዲሁም ለውሳኔ ቀረበ የተባለው የአዲስ አበባ ዲጂታል መታወቂያም አወያይቷል።

https://p.dw.com/p/34Rqn
Äthiopien Simegnew Bekele Chefingenieur von GERD getötet
ምስል Tigist Endalamaw

የሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዐቢይ መነጋገሪያ

«አንድ ሕዝብ አንድ ኢትዮጵያ!» አርቲስትና የመብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ በዚህ ሳምንት መንደርደሪያ ከባህርዳር ካሰማው ንግግሩ የተቀነጨበ ነው። ታማኝ በርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት በባህርዳር  ስታዲየም ያሰማው ንግግሩ  ብዙዎችን ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ለድጋፍ እና ለተቃውሞ አስነስቷል። አዲሱ «የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታወቂያ ይዘትና ንድፍ ለውሳኔ» የመቅረቡ ዜና በተመሳሳይ ድጋፍና ተቃውሞ አጭሯል። የራያ ተወላጆች ላይ ትግራይ ክልል ውስጥ ይደርሳል የተባለውን በደል በመቃወም በዚሁ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሰልፍ ተከናውኗል። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት፦ ወልቃይት እና ራያን በተመለከተ ያወጣው መግለጫም መነጋገሪያ ኾኗል።

ታዋቂ ሰዎች የትኛውንም አመለካከት ያራምዱ የሚያሰሟቸው ንግግሮች ተጽዕኖ ብርቱ ነው። ከአርቲስትና የመብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ከባህርዳር የተሰማው የሰሞኑ ንግግር በብዙዎች ዘንድ ድጋፍ እና ተቃውሞ አጭሯል። ታማኝ ያሰማው ንግግር ከጎሳ ይልቅ ኢትዮጵያዊነት ላይ ትኩረት እንዲሰጥ አጽንዖት ሰጥቷል። በንግግሩ ጣልቃም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎቹ «ይደገም» እያሉ ድጋፍ ሲሰጡት ነበር።

ታማኝ ያደረገው ንግግርን ተመርኩዘው ከተሰነዘሩ አስተያየቶች መካከል አቤል ጂራታ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «አንድ ህዝብ አንድ ኢትዮጵያ ሲል በመጠየቅ ይጀምራል።  «ስንት ኢትዮጵያን ነበር የሚያውቀው? የመረጠው አንዱ ህዝብስ የትኛው ህዝብ ነው? የቀረውን ህዝብ ምን ሊያደርገው አስቦታል ሲልም አክሏል። የማግለል «ዘመን ግን ላይመለስ ተቀብሯልና በከንቱ ጊዜያችሁን አትጨርሱ» ብሏል።

Empfang von Menschenrechtsaktivist Tamagne Beyene in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ከአቤል ጂራታ ተቃራኒ ሐሳብ በማንሳት ጽሑፉን እዛው ፌስቡክ ላይ ያሰፈረው አብርሃም ሀብተየሱስ አቤል ነው። «ታማኝ አብይና ለማ ከሚሉት የተለየ አላለም» በሚለው ጽሑፉ የተንደረደረው አብርሃም፦ «ሕዝቦችዋ በእኩልነት በመከባበር ስለሚኖሩባት ሀገር፣ እያንዳንዱ ዜጋዋ በመረጠበት የሀገሪቷ ክፍል ለመኖር መብቱ የተጠበቀባት ስለመሆኗ ነው የተናገረው» ሲል አክሏል። «27 እ ከዚያም በላይ ለሆነ ግዜ ስለመለያየት ተስብኳል፤ ስለዚህም አልጠቀመንም» ያለው አብርሃም «ስለ ሌላውን ማግለል የተናገረው በፍፁም የለም» ብሏል።

ታማኝ የባህርዳር ንግግሩን ያደምጡ ለነበሩ ታዳሚያን ምክር አዘል መልእክት አስተላልፏል። «ማንም ይምጣ፤ ማንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚመለከተው ሁሉ መጥቼ ሐሳቤን እገልጻለሁ ካለ ቁጭ ብላችሁ አዳምጣችሁ ሞግቱ፤ አትምጡብን ማለት ግን የጠባቦች እንጂ የእናንተ ሊኾን አይገባም» ሲል ተደምጧል። «አማራ ክልል የለውም፤ ክልሉ ኢትዮጵያ ነች» የሚል እና ሌሎች ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያተኩሩ መልእክቶችንም አሰምቷል።  

ብዙ ሰዎች ታማኝ እንደስሙ ታማኝ ኾኖ ለዓመታት ዘልቋል በበማለት አድናቆታቸውን ገልጠውለታል። ዳንኤል አሰፋ ትዊተር ላይ «ታማኝ ጀግና ነው» ሲል ጽፏል። ዳንኤል የታማኝን ንግግር በመደገፍ በፌስቡክ ጽሑፉ፦ «ሰው ሰው ነው። ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊ። ፈጣሪ ሲፈጥር በብሔር ከፋፍሎ አደለም። በፈጣሪ ፊት ሁሉም የሰው ልጆች የእጆቹ ሥራዎች ናቸው። አንተ አማራ አንተ ኦሮሞ አንተ ደቡብ አንተ ትግሬ ብሎ አይጠራም። የኔ ብሔር ይበልጣል ሌላው አናሳ ነው ፣ የኔ ብሔር ቅድሚያ ሌላው ተከታይ ነው ብሎ መስበክ ፈጣሪን ደካማ ፈጣሪ አድርጎ እንደማሰብ ነው» ሲል አትቷል። «እንዲህ ብሎ የሚታበይ አክቲቪስትም ይሁን ፓለቲከኛ፣ እወደድ ባይና ትምክህተኛ ጥቅም ፈላጊ ነው። ያልፈጠረውን ሰው በምላሱ እየነዳ የአላማው ማስፈፀሚያ ለማድረግ የሚፈልግ ጨለምተኛ እና ጠባብ ነው» ሲል ጽሑፉን አጠናቋል። 

Äthiopien Addis Abeba Simegnew Bekele tot aufgefunden
ምስል Reuters/T. Negeri

የህዳሴው ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ራሳቸውን አጥፍተዋል  የሚል መደምደሚያ ላይ ፖሊስ ደረስኩ ሲል ዛሬ መግለጡን በተመለከተ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው መጉረፍ የጀመሩት ወዲያው ነው። አስተያየት ሰጪዎቹ ስለ ኢንጂነር ስመኘው አስክሬን በመስቀል አደጻጻይ ላይ መገኘት እና ሰበቡን በተመለከተ  የየራሳቸውን መላምት ሰንዝረዋል። በማኅበራዊ መገኛ በርካታ አስተያየት ሰቺች  የምርመራ  ውጤቱን አልተቀበሉም። ቢንያም ትዊተር ላይ ያሠፈረው ጽሑፍ የብዙዎቹን ሐሳብ የሚጋራ ይመስላል። «በጣም የሚገርም የምርመራ ውጤት ነው» ሲል ይንደረደራል የቢንያም ጽሑፍ። «እንደ ስመኘው ያለ ትጉህ፣ አስተዋይ፣ ታታሪ ባለሙያ ራሱን ያጠፋል ብዬ ለማመን እቸገራለሁ። መቼም የነበረበት የሥራ እና የበንዲቶቹ ጫና እንደ ምክንያት ከተቀመጠ ለምን በዚህ ወቅት ራሱን ለማጥፋት ወሰነ?» ሲል በመጠየቅ ጽሑፉ ይቋጫል።

«አዲሱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታወቂያ ይዘትና ንድፍ ለውሳኔ ቀረበ» የሚለው የሪፖርተር የረቡዕ ዕለት ዘገባ ይዘትን በመንተራስ በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየት ሰጥተዋል። «አዲሱ የአዲስ አበባ መታወቂያ ይሄን ይመስላል ተብለናል» ሲል ትዊተር ላይ የጻፈው ሲራክ ተመስገን፦ «የአዲስ አበባ የከተማ የነዋሪ መታወቂያ» የሚል ዲጂታል ፎቶግራፍን አያይዟል። ፎቶግራፉ ላይ የትውልድ ቀን እንጂ ቦታን አይጠቅስም፤ የነገድ ስያሜን የሚጠይቅ ሳይኾን ዜግነት የሚል ነው ያለው።

አዲሱ መታወቂያን በተመለከተ ትዊተር ላይ ኪዳኔ ጫኔ ቀጣዩን ጥያቄ አስፍሯል።  «የአዲስ አበባ መታወቂያ እንደብዙ ሀገሮች ለማንኛውም የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚሠጥ ነው?  ዲያስፖራውን ነዋናሪና የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ወይስ ለኢትዮጵያዊያን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ ነው?»

«የአዲሱ መታወቂያ አጠቃላይ ወጪ ኅትመትን ጨምሮ 300 ብር ያህል ቢሆንም፣ ነዋሪዎች ግን የሚከፍሉት የካርዱን ዋጋ ብቻ 80 ብር እንደሆነ ታውቋል» ሲል ሪፖርተር ዘግቧል። ይኽንኑ ዘገባ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከጽሑፎቻቸው ጋር ያያዙ ሰዎች፦ «የምዝገባ ሒደቱ በኮምፒዩተር የታገዘ የዲጂታል አሠራር የሚከተል» መኾኑን ጠቅሰዋል። ዘገባው፦ አዲሱ መታወቂያ «በአሻራ የተደገፈ» እንደሆኾነ «ዋጋውም 80 ብር» እንደሚኾን ያትታል። በርካቶች ጋር እንደደረሰው ዘገባ ከኾነ፦ አዲሱ መታወቂያ በሁለት ቀለማት የተዘጋጀ ሲኾን፤ በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ፣ በሁለቱ አማራጭ መታወቂያዎች ላይ «ከመከረ በኋላ አንዱን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል» ተብሏል።

Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

አዲሱ መታወቂያ ንድፍ ላይ የተቃውሞ አስተያየት ካሰፈሩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች መካከል ወጋየሁ ጉተማ፦ «ምኑን መታወቂያ ሆነ ታዲያ» ብሏል ትዊተር ላይ በአጭሩ። ጋዲሳ ሆማ ደግሞ በፌስ ቡክ አስተያየቱ፦«ዞር ዞር ብዬ እንዳየሁት ከሆነ የባንዲራ ጉዳይ፣ የራያ ጉዳይ፣ የሜቴክ ጉዳይና የቀበሌ መታወቂያ ላይ ብሔር መጠቀስ መቅረትና ሌሎችም የፌቡ አጃንዳዎች ናቸው። ከመጨረሻው አጀንዳ በስተቀር ሌሎቹ አዲስ አይደሉም። ለጋዲሳ መታወቂያው ላይ ብሔር መኖር አለመኖር ምኑ ነው?» ሲል አጠይቋል።

አዲሱ ቸኮል ይህንኑ የመታወቂያ ጉዳይ በተመለከተ የዛሬ አንድ ዓመት ግድም ያቀረበው የፌስቡክ ጽሑፉ፦ «በነገራችን ላይ የድሬዳዋ መታወቂያ ላይ ብሔር አይጠይቅም፡፡ አማራ ክልልም እንደማይጠይቅ ሰምቻለሁ። ሌሎች ክልሎችም ይሄንኑ እንዲከተሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ አስፈላጊ የሚያደርገው አንዳች ምክንያት የለም» ይላል።

የመታወቂያ ጉዳይ ከተነሳ ከሁለት ዓመት በፊት «የመታወቂያ ጉዳይ መረጃ» በሚል የፊልም ባለሞያው ያሬድ ሹመቴ ተከታታይ ጽሑፎቹን በፌስቡክ አስነብቧል። ያሬድ መታወቂያዬ ላይ «ኢትዮጵያዊ» የሚለው ዜግነት ነው መስፈር ያለበት በማለት በብቸኝነት አቤት እያለ የገጠመውንም በተከታታይ በፌስቡክ ጽሑፎቹ ለአደባባይ በማቅረብ ከፍተኛ ግንዛቤ አስጨብጧል። ያሬድ የመታወቂያ ጉዳዩ ላይ ያቀረበው የዓመታት ውትወታው እልባት ሊያገኝ  መዳረሱን በመመልከቱም፦ «እንኳን ደስ አለን፤ እንኳን ደስ አላችሁ! ምኞታችን ዳር ደርሷል። የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታወቂያ መመርያ ተሻሻለ» ሲል ደስታውን ገልጧል።

Karte Äthiopien englisch

የማንነት ጥያቄ ላለፉት ሁለት ዐሥርተ-ዓመታት ስር በሰደደ መልኩ ሲሠራበት ቆይቷል። እናም በአሁኑ ወቅት በየቦታው የማንነት ጥያቄ እና ግጭቶች ሄድ መለስ ሲሉ ይስተዋላሉ። ከሰሞኑ የራያ ነዋሪዎችን የሚመለከት፦ «የራያ ሕዝብ ጩኸት ይሰማ!» በሚል መፈክር አዲስ አበባ ዋናው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሕንጻ ፊት ለፊት ሰልፍ ተከናውኗል። ሰልፈኞቹ «ሞት፤ አፈና እና ጭቆና ይቁም» ሲሉ ተደምጠዋል።

አማኑኤል ፓራሜራ፦ «እንደምን አደራችሁ ራያ ፤ ወሎ፤ አማራ፤ ከተዳፈነበት፣ ከተረሳበት፣ አይደረግም ከተባለት የጨለማዉ ዘመን ወጠን በግልፅ/በአደባባይ መብታችን መጠየቃችን ደስ ይላል። ይህ ቀን እንደሚመጣ እርግጠኛ ነበርን» ሲል ፌስቡክ ላይ ጽፏል።

የረቡዕ ዕለት የአዲስ አበባው ሰልፍ በተደረገበት ምሽት የትግራይ ክልል «የትግራይን እና የህዘቦቿን አንድነት ለማዳከም ሆነ ተብሎ የሚካሄድ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተቀባይነት የሌለው» እንደኾነ የሚያሳስብ መግለጫ አውጥቷል። ሰልፉንም መግለጫውንም በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰጡ አብዛኞቹ አስተያየቶች በዋናነት «ራያ የእኛ ነው» የሚል መልእክት ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ