1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካሜሩን ቀውስ እና ቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ

ቅዳሜ፣ መስከረም 12 2011

በካሜሩን የፊታችን መስከረም 27፣ 2011 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሰረትም የምርጫው ዘመቻ በዛሬው ዕለት በይፋ ዘመቻ ተጀምሯል።

https://p.dw.com/p/35JbO
Karte Nigeria Adikpo Kamerun EN

የካሜሩን ምርጫ

ካሜሩንን ካለፉት 36 ዓመት ወዲህ በሚመሩት ፕሬዚደንት ፖል ቢያ አንፃር ስምንት እጩዎች በተወዳዳሪነት ቀርበዋል።ይሁንና፣ ውዝግብ በቀጠለበት እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ በሆነው የሀገሪቱ አካባቢ ምርጫውን እና ዘመቻውን እንደታሰበው ማካሄድ መቻሉ አጠራጣሪ ሆኗል። ይህንኑ አካባቢ ከተቀረው ካሜሩን ለመገንጠል የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች እነርሱ ሀገር በሚሉት በዚሁ አካባቢ የውጭ ምርጫ እንዲካሄድ እንደማይፈቅዱ ዝተዋል። በካሜሩን የሚገኙት ሁለት ውሁዳን እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ አካባቢዎች፣ ማለትም፣ ሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ግዛቶች ከ2009 ዓም ወዲህ በቀጠለው ግጭት መረጋጋት የተሳነው ሲሆን፣ በግጭቱ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሰዎች ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣  ወደ 200,000 የሚጠጋ ደግሞ ከመኖሪያ አካባቢው ተፈናቅሏል። ውሁዳን እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የካሜሩን አካባቢ በብዙሀኑ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች አድልዎ እየተፈጸመበት ነው በሚል ቅሬታ የሚያሰሙት ዓማፅያን ፕሬዚደንታዊው ምርጫን ለማከላከል እንደሚሰሩ ነው ያመለከቱት።  ከ18 ሚልዮኑ የካሜሩን ህዝብ መካከል 80% ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነው።

ይህን ተከትሎ ታድያ ብዙ ሕዝብ በአካባቢው ተደጋግሞ በመታየት ላይ ያለውን ግጭት  መሸሹን መርጧል። የካሜሩን ባለስልጣናት ሰው አካባቢውን ለቆ እንዳይወጣ እገዳ አሳርፈዋል። ያም ሆኖ ግን ፍርሀት እና ስጋት ያደረባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች  የተረጋጋ ወደሚሉት አካባቢ ለመሄድ መነሳሳታቸውን የደቡብ ምዕራብ ካሜሩን ግዛት ዋና ከተማ ቡዌአ ነዋሪዎች ገልጸዋል። የግዛቱ ዋና አስተዳዳሪ ቤርናር ኦካሊያ ቢላይ በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ነዋሪዎቹ ወደየመኖሪያቸው እንዲመለሱ ተማፅነዋል።
« የጦር ኃይሉ ጥቃት ይሰነዝራል የሚል የሀሰት ወሬ ተስፋፍቷል። ይህ ሀሰት ነው። የጦር ኃይሉ በዚያ ያለው ህዝቡን እና ንብረቱን ከጥቃት ለመከላከል እና ጥቃቱን ለማስቆም ነው።  ሰዉ በየቤቱ እንዲቆዩ ነው የምንፈልገው። »
እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ ዓማፅያን ናቸው የኃይል ተግባር እየፈጸሙ ያሉት በሚል ዋና አስተዳዳሪ ቤርናር ኦካሊያ ቢላይ ያካባቢውን ህዝብ ለማረጋጋት ሙከራቸውን ቀጥለዋል። ከባልተቤታቸው እና ከአምስት ልጆቻቸው ጋር በ ቡዌአ ከተማ የሚኖሩት መምህሩ ጆን ሎም ግን የግዛቱን ዋና አስተዳዳሪ መንግሥት የነዋሪው ደህንነትን እንደሚከላከል የሰጡትን ዋስትና እምብዛም አላመኑትም።
« ነዋሪዎች ከለላ እንደሚደረግላቸው በማስታወቅ በየቤታቸው እንዲቆዩ የተማፀኑት ዋና አስተዳዳሪው ራሳቸው በሚከ,,ላከሏቸው ወታደሮች ታጅበው ነው የሚዘዋወሩት። እና ወታደሮቹ ህዝቡን ሁሉ ይከላከላሉ? በዚህ ምክንያት ነው ባካባቢው ለመቆየት የማልፈልገው። ለቅቄ መውጣት አለብኝ። »   
ባጠቃላይ ነዋሪዎቹ ውዝግቡ ባካባቢው  እስካላበቃ ድረስ ነፃና ትክክለና ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብለው አያምኑም።

China Peking - Kameruns Präsident Paul Biya
ምስል picture-alliance/AP Photo/L. Zhang

« በሰሜን ምዕራቡ እና በደቡብ ምዕራቡ ካሜሩን ግዛቶች ተዓማኒ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። በሁለቱ አካባቢዎች የሚገኙ ከተሞች ነዋሪ አልባ ሆነዋል። እና በሁለቱ አካባቢዎች ነፃ እና ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ ቢፈለግም ፣ ጊዜው በማለፉ በወቅቱ ምንም ሊደረግ አይችልም። »

ብዙ እጩዎች  ሰዎች ድምፃቸውን እንዲሰጡ ለማበረታትት በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ይሁንና፣ እስካሁን የተቃዋሚው የካሜሩን ብሔራዊ ዜግነት ንቅናቄ ፓርቲ እጩ  አፋኑዊ ብቻ ናቸው ውዝግብ ወደሚታይበት አካባቢ የሄዱት።  የዳግም ተሀድሶ ንቅናቄ ፓርቲ ፕሬዚደንታዊ እጩ ሞሪስ ካማቶ  ተገንጣዮቹ ዓማፅያን የመገንጠል እቅድቻውን በመተው አካባቢያቸው ይደርስበታል ያሉትን አድልዎ ለማብቃት  ከፈለጉ ህዝቡ ስርዓቱን በምርጫ መቀየር እንዲችል በምርጫው እንዲሳተፍ እድል መስጠት እንዳለባቸው ለDW ተናግረዋል።
«  ጦርነቱን አያሸንፉም። እና ለምንድን ነው ውጊያውን መቀጠላቸው? የህዝቡን ጥያቄ እና ፍላጎት የማያዳምጥ መንግሥት ስላለን ብቻ በውዝግብ ላይ የምትገ።ነውን ሀገር ለሁለት መክፈል መፍትሔ ነውን? ሂዱ እና ድምፃችሁን ስጡ፤  ብቸኛው መፍትሔ ይህ ነው።  ህዝባችንን መስዋዕት ማድረግ የለብንም። »
ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ ዓማፅያኑ ለእንግሊዝኛ ተናጋሪው አካባቢ ጥቅምት፣ 2010 ዓም  ሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር በጠየቁበት ጊዜ መንግሥት በወሰደው የኃይል ርምጃ ከ400 የሚበልጡ ሰዎች ነበር የተገደሉት። 
ሌላው ፕሬዚደንታዊ እጩ ጆሹዋ ኦሲህ ለቀውሱ የተሻለ መፍትሔ እንዳላቸው ነው የገለጹት።

Kamerun Wahlen
ምስል Dr. Dirke Köpp

« ችግሩ መገንጠል አይደለም። ችግሩ ወደ መገንጠል ጥያቄ ያመራው ህዝቡን የማግለሉ ድርጊት እና በህዝቡም ላይ እየተፈጸመ ያለው ኢፍትሓዊ አሰራር ነው። መገንጠል ችግሩን ያስወግዳል ብዬ አልገምትም። ጉዳዩን የሚረዳ ፕሬዚደንት ካለ፣ ችግሩን ለማስወገድ በመጀመሪያ ህዝብ ለሚገለልበት አሰራር መፍትሄ መስጠት ነው። እኔ ፕሬዚደንት ሆኜ ብመረጥ የመጀመሪያው ውሳኔዬ የሚሆነው ጉዳዩ የፖለቲካ ችግር መሆኑን አምኖ መቀበል ነው። »
የካሜሩን አስመራጭ ቦርድ ሊቀ መንበር ኤኖው አብራምስ ምርጫው በሁሉም አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

« መወሰድ ያለባቸውን የፀጥታ ርምጃዎች በተመለከተ፣ በቦታው ከሚገኙት አጋሮቻችን ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ካካሄድን በኋላ ለምሳሌ የምርጫ ጣቢያዎቹን በአንድ የምርጫ ማዕከል ስር ማሰባሰብ  ወስነናል። ለምርጫ የሚያስፈልገው ቁሳቁስ ከሞላ ጎደል ተዘጋጅቷል፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን የመሳሰሉት ቁሳቁሶችም ወዳካባቢው  በመላክ ላይ ነው።
በካሜሩን የአውሮጳ ህብረት ተጠሪ ሀንስ ፔተር ሻዴክ እንዳስታወቁት፣ ህብረቱ በምርጫው በታዛቢነት ባይሰማራም የምርጫውን ሂደት መከታተሉ አይቀርም።
« የምርጫ ታዛቢ ቡድን ለመላክ አልታቀደም።  አልተዘጋጀም። ይሁንና፣ በቦታው በመገኘት የሚሆነውን እንከታተላለን። »
 

አርያም ተክሌ

ተስፋለም ወልደየስ