1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካርቦን ዳይኦክሳይድ ዋጋ ስንት ነው?

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 28 2010

የከባቢ አየር ለውጥ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ፓሪስ-ፈረንሳይ ዉስጥ ከተደረገዉ ዓለም አቀፍ ስምምነት ወዲሕ፤ አገራት ሊቀንሱ ቃል የገቡትን የሙቀት የልቀት መጠንን እንዴት ተግባራዊ ያደርጉታል በሚለው ሐሳብ ላይ መሥማማት፤ እዚሕ ቦን-ጀርመን የተሰየመዉ ጉባኤ ሁነኛው ፈተና ነው።

https://p.dw.com/p/2nCgv
Äthiopien Dürre Wassertransport
ምስል picture-alliance-akg-images/Y. Travert

የከባቢ አየር ለውጥ ጉባኤ በቦን እየተካሔደ ነው

የጉባኤዉ መሪ የፊጂው ጠቅላይ ሚኒሥትር ፍራንክ ባይኒማራማ ወደ ቦን ሲመጡ ከሐገራቸዉና አካባቢዉ "በቃ-በቃ ነው" የሚል መልዕክት ይዘዉ ነዉ። ጠቅላይ ሚኒሥትሩ በቃ የሚሉት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝን ነው። እየጨመረ የሚሔደው የውቅያኖስ ውሐ ትንሿን አገራቸውን ጨርሶ ከመዋጡ በፊት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርምጃ እንዲወስድ ይሻሉ። በከባቢ አየር ለውጥ ምክንያት አንድ መንደር ሙሉ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ያሸጋገረች አገር ፊጂ ብቻ ነች።

የሙቀት መጠን መጨመሩ የሚያሳስባቸው ግን የፊጂው ጠቅላይ ሚኒሥትር ብቻ አይደሉም። የዓለም ሜትዎሮሎጂ ድርጅት ሊቀመንበር ፔቴሪ ታላስ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው የበካይ ጋዝ መጠንም ሆነ የዓለም የሙቀት መጠን እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል። 

"2017 በታሪክ እጅግ ሞቃታማ ተብለው ከተመዘገቡ ሶስት አመታት አንዱ ነው። ባለፉት ሁለት አመታት የዓለም የሙቀት መጠን በኤል-ኒንኞ ምክንያት እጅግ ጨምሯል። የ2017 የዓለም የሙቀት መጠን ኤልኒንኞ ከመከሰቱ በፊት ከነበረው 2014 ጋር ካነፃጸርነው እጅግ ጨምሯል። ይኸ ደግሞ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው የበካይ ጋዝ በተለይ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ምክንያት ነው"

Datenvisualisierung ENGLISH CO2 Emissionen

በእርግጥ በምድር ዋልታ የነበረው በረዶ እየቀለጠ ነው። ድርቅ እና ወጀብ የቀላቀለ አውሎ ንፋስም በተለያዩ የዓለም ማዕዘኖች ከወትሮው በተለየ ሲከሰቱ ይታያል። ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳንን የመሳሰሉ አገራት ለዚህ ምስክር ናቸው። የጀርመኑ የልማት ሚኒሥትር ጌርድ ሙለር የሰው ልጅ መፃኢ እጣ-ፈንታ አደጋ ላይ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

"ከባቢ አየርን መጠበቅ የሰው ልጅን ከጥፋት ለመትረፍ ያለው ብቸኛ አማራጭ ነው። ጥቂት የመንግሥት መሪዎች ይኸን የማያምኑ ቢኖሩም እንኳ"

የሚኒሥትሩ መልዕክት በቀጥታ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታለመ ይመስላል። ፕሬዝዳንቱ በከባቢ አየር ለውጥ አያምኑም። አገራቸውን ከፓሪሱ ስምምነት ለማስወጣት የወሰኑት ትራምፕ የቦኑን ጉባኤ ለመሳተፍ አልፈቀዱም። 

የዓለም የሙቀት መጠንን በተጨባጭ መቀነስ ማለት የፓሪሱን የከባቢ አየር ለውጥ ጉባኤ ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ነው። የቦኑ ጉባኤ የፓሪሱ የከባቢ አየር ለውጥ ሥምምነት አተገባበር ዝርዝር ይዘጋጅበታል ተብሎ ይጠበቃል። የፓሪሱ ስምምነት የዓለም የሙቀት መጠን ከ2 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ እንዳይጨምር የመግታት ውጥን አለው። በሥምምነቱ መሰረት የዓለም አገሮች ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን ራሳቸው ያቅዳሉ። ለደሐ አገሮች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በእርዳታ ለመስጠትም ውጥን አለ።

COP23 in Bonn
ምስል DW/I. Banos Ruiz

 

የካርቦን ዳይኦክሳይድ ዋጋ ስንት ነው?

የዓለም የሙቀት መጠንን በእቅዱ መሰረት ከ2 ዲግሪ ሴልሽየስ በታች ለማድረግ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ወደ ካርቦን ንግድ ፊታቸውን ያዞራሉ። የድንጋይ ከሰል፤ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ሲቃጠሉ የዓለም የሙቀት መጠን ከፍ የሚያደርገውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ይለቃሉ። የምጣኔ ሐብት ባለሙያቹ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው እያንዳንዱ ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ውድ ዋጋ ሊያስከፍል ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ። ዋጋ ሲጨምር ፍላጎት በአንፃሩ ይቀንሳል። ዓለምም አማራጭ ኃይል ታፈላልጋለች። ግን አንድ ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ስንስት ያወጣል? ዛሬም ምላሽ ያልተገኘለት አወዛጋቢ ጉዳይ ነው።

በየል ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ምጣኔ ሐብት ባለሙያው  ሮበርት ሜንደልሰን "እቅዱ የዓለም የሙቀት መጠንን ዝቅተኛ ማድረግ ከሆነ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መነሻ ዋጋ ከፍ ማለት አለበት። እጅግ ከፍ ማለት አለበት። በአንድ ቶን 100 ዶላር ሊሆን ይገባል። አሁን ያለው ዋጋ በ5 እና በ10 ዶላር መካከል ነው። ይህ እቅዱ 4 ዲግሪ ሴልሽየስ ከሆነ ብቻ ነው የሚሰራው።" ሲሉ ይናገራሉ። 

የከባቢ አየር ተሟጋቾች የዓለም የሙቀት መጠን ወደ 4 ዲግሪ ሴልሽየስ ከፍ ካለ አደገኛ እንደሚሆን ይወተውታሉ። የበካይ ጋዝ በከፍተኛ መጠን ወደ ከባቢ አየር ከሚለቁ አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ በሌለችበት የሚከናወነው የቦኑ ጉባኤ ምን ያሳካ ይሆን? 

እሸቴ በቀለ 
ነጋሽ መሐመድ