1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በሶማሌ ክልል

ረቡዕ፣ ኅዳር 26 2016

በሶማሌ ክልል አስር ወረዳዎች እና ሁለት ከተሞች በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ 38 ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች አስፈላጊው መድሀኒት ፣ ባለሞያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች መላካቸውን እና በመንግስት ተቋማት እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች የወረርሽኙን ጉዳት ለመቀነስ የሚረዳ ርብርብ እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4ZpxP
አሳሳቢዉ የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በሶማሌ ክልል
የጎርፍ መጥለቅለቅ እና ኮሌራ በሶማሌ ክልልምስል Mesay Teklu/DW

በኮሌራ ወረርሽኝ ሰላሳ ስምንት ሰዎች ሞተዋል

በሶማሌ ክልል አስር ወረዳዎች እና ሁለት ከተሞች በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ ሰላሳ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቋል። ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች አስፈላጊው መድሀኒት ፣ ባለሞያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች መላካቸውን እና በመንግስት ተቋማት እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች የወረርሽኙን ጉዳት ለመቀነስ የሚረዳ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ  ጤና ቢሮ ኃላፊ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም ችግሩ ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉ ተገልጿል ።

የሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሴ አህመድ በተለይ ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩት በክልሉ በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ከተያዙ ታማሚዎች ከራቅ ያለ ስፍራ መተው ወደ ህክምና ተቋም መድረስ ያልቻሉ እና በህክምና ተቋም የሞቱ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር ሰላሳ ስምንት ደርሷል። በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ከሁለት ወራት በፊት በተከሰተ የጎርፍ እና የወንዞች ሙላት ሳቢያ ህብረተሰቡ በሚገለገልባቸው የውሀ መሰረተ ልማት እና መፀዳጃ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የጠቀሱት ኃላፊው በዚህም ሳቢያ በአስር ወረዳዎች እና በሁለት ከተሞች ወረርሽኙ መከሰቱን አስተድተዋል። 

ችግር ያጋጠማቸውን የውሀ እና የፍሳሽ ገንዳዎችን የማስተካከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሙሴ በተቀናጀ መልኩ በተጀመረው የመከላከል ስራ ለውጥ እየመጣ መሆኑን አብራርተዋል። ሰሞኑን በተዘዋወርንበት የሼቤሌ ዞን ምስራቅ ኢሜ ወረዳ ነዋሪው አቶ መሀመድ በአካባቢው በተከሰተ ኮሌራ ሰዎች  እየሞቱ መሆናቸውን በመግለጥ መፍትሄ ይደረግ ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ሰተዋል።

ይህንን በሚመለከት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሴ በየቦታው የሚያስፈልጉ መድሀኒቶች ፣ ባለሞያዎች እና ግብዓቶች መላካቸውን እና በተለያዩ ተቋማትም የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።  

ጎርፍ እና ውሀ መጥለቅለቅ

በቅርቡ በክልሉ በጣለው ዝናብ እና የወንዝ ሙላት ሳቢያ የተከሰተው የውሀ መጥለቅለቅ በርካቶችን ከመኖርያ ቀያቸው ሲያፈናቅል ትምህርት እንስሳት ጤናንጨምሮ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ መገለፁ ይታወሳል። ሰሞኑን በክልሉ ውሀ መጥለቅለቅ ጉዳት ከደረሰባቸው ዞኖች አንዱ በሆነው እና በኣካል በተገኘንበት ሼቤሌ ዞን ከሃምሳ ሰባት ሺህ በላይ አባወራዎች መፈናቀላቸውን እና አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የልማት ተቋማት መጎዳታቸውን የዞኑ አስተዳደሪ ገልጸዋል።

የሼቤሌ ዞን ምስራቅ ኢሜ ወረዳ ነዋሪው አቶ መሀመድ በአካባቢው በደረደው የውሀ መጥለቅለቅ መፀዳጃ ቤቶች ወደ ውጭ መፍሰሳቸውን እና በዚህም ሳቢታ በተከሰተ ኮሌራ ሰዎች  እየሞቱ መሆናቸውን በመግለጥ መፍትሄ ይደረግ ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ሰተዋል።

የጎርፍ መጥለቅለቅ እና ኮሌራ በሶማሌ ክልል
የጎርፍ መጥለቅለቅ እና ኮሌራ በሶማሌ ክልልምስል Mesay Teklu/DW

የኮሌራ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው ወረዳዎች መድሀኒት ፣ ባለሞያዎች እና ተሽከርካሪ ተመድቦ ጉዳቱን የመቀነስ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሴ አህመድ ለDW ተናግረዋል። በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ እስካሁን የሞቱ ሰዎች ሰላሳ ስምንት መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሰው የውሀ መጥለቅለቅ አሁንም ባለመድረቁ ሌሎች የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ሲነሳ ቆይቷል።

Save the Children የተባለው የህፃናት አድን ግብረ ሰናይ ድርጅት በጎርፍ ውሃ ምክንያት ከቤታቸው ለቀው እንዲወጡ ለተገደዱ ሰዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ እና የመፀዳጃ አገልግሎቶችን በማቅረብ በመንግስት እና በለጋሾች አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለው የኮሌራ ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል።

መሳይ ተክሉ

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ