1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የውጭ ምንዛሪ ክምችት መሻሻል እያሳየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 8 2011

የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት መሻሻል እያሳየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አሁን አገሪቱ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበራት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በካዝናዋ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/36nMq
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M.W. Hailu

በዚህ አመት የደሞዝ ጭማሪ የለም ብለዋል

በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ማብራሪያ መሠረት የኢትዮጵያ የመንግሥት ሰራተኞች በአመቱ የደመወዝ ጭማሪ አያገኙም። በመከላከያና ሲቢልን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰራተኞች መኖራቸዉን የገለፁት ዶ/ር ዐብይ የሲቪል ሰርቪሱ «ጂኤጂ» ጥናት ዋና አላማው የደመወዝ ጭማሪ ሳይሆን የተረጋጋ የስራ ምህዳር ለመፍጠር እንደሆነም ጠቁመዋል።
የስራ አከባቢን ለማረጋጋት እና የሰራተኞች ፍልሰት ችግርን ለመቅረፍ ፤ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር እንደማይገናኝ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄው ግን እውነተኛና ትክክል ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።  የደመወዝ ማስተካከያ መወሰን ቢችል ዝቅተኛው 37 ቢሊዮን ከፍተኛው ደግሞ 100 ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል ሲሉ ከፍተኛ የበጀት ጫና መኖሩን፣ የተፈናቀሉ ሰዎች መርዳት፣ ገቢ መሰብሰብ አለመቻል እና የእዳ ክፍያ ችግሮች በመኖራቸው የደመወዝ ጥያቄውን ለማስተናገድ እንደማይቻልም አስረግጠው ተናግረዋል።ራሳቸው ጠቅላይ ምኒስትሩን ጨምሮ የመንግሥት ሰራተኞች ዝቅተኛ ተከፋዮች መሆናቸውን የገለጹት አብይ የግሪክን ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ በምሳሌነት ጠቅሰው ዜጎች የአገሪቱ ኤኮኖሚ እስኪያገግም እንዲታገሱ ጥሪ አቅርበዋል። 
የፖሊሲና ኢንቨስትመንት አማካሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ተክለማርያም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በእርግጥም ባለፉት ሶስት አመታት ካለፈበት ውጣ ውረድ አኳያ የመረጋጋት አዝማሚያ እንዳሳየ ይስማማሉ። አቶ ጌታቸው እንደሚሉት አንጻራዊው ፖለቲካዊ ለውጥ ለምጣኔ ሐብቱ መረጋጋት አስተዋጽዖ ካበረከቱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።  
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሀገሪቷ ያለባትን እዳ በአንድ ጊዜ መክፈል አሁን ያለችበት ሁኔታ ስለማይፈቅድ በረጅም ጊዜ ለመክፈል የተሳካ የዲፕሎማቲክ ስራ ሰርተናል ብለዋል። በዛሬው የምክር ቤት ውሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሷቸው አበይት ጉዳዮች መካከል የአገሪቱን ምጣኔ ሐብት ወጥሮ የያዘው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የተመለከተ ነበር። ባለፉት አመታት በአገሪቱ ምጣኔ ሐብት በተለይም በገቢ እና ወጪ ንግድ ላይ የከፋ አስተዋጽዖ ያሳደረው የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት መሻሻል እያሳየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አሁን አገሪቱ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበራት የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በእጅጉ ይገኛል። 

Äthiopien Addis Ababa - Äthiopiens neues Kabinett besteht zur Hälfte aus Frauen
ምስል Getty Images/AFP/Stringer

ነጃት ኢብራሒም
ሸዋዬ ለገሠ