1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዒድ ጥሪ ለዲያስፖራ ማህበረሰብ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 20 2014

ከኢድ እስከ ኢድ በሚል የተላለፈ ጥሪን ተከትሎ ለመጡ ሙስሊሞች በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ በተደረገው አቀባበል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ መገፋፋትና ጽንፈኝነትንም አውግዘዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4AYq0
Äthiopien Eid-to-Eid Great Ethiopian Homecoming
ምስል Seyoum Getu/DW

የዒድ ጥሪ ለዲያስፖራ ማህበረሰብ

የኢትዮጵያ መንግስት ለአገር ገጽታ ግንባታ ጉልህ ሚና ይጫወታል በሚል ከአገር ውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ጥሪ ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጥሪው በኢትዮጵያውያን መካከል አንድነትን በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅምንም ለመገንባት ጉልህ ድርሻ ያለው ነው ይባልለታል፡፡ ከኢድ እስከ ኢድ በሚል በቅርቡ ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን በተደረገው የአገር ቤት መመለስ ጥሪ መሠረት ወደ አገሪቱ ለተመለሱ ኢትዮጵያንም አቀባበል ተደርጓል፡፡

ያሲን ሳሌህ አብዱራሃማን በአውሮፓ ስዊድን አገር ለ46 ኣመታት ያህል ኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ የወቅቱ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የረመዳን ወርን ተከትሎ ወደ አገር ቤት ጉዞ እንዲያደርጉ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት መምጣታቸውንም ይገልጻሉ፡፡ አሁን በችግሮች ብዛት ተተብትባ በምትገኝ አገር ውስጥ ተስፋ እንደሚታያቸውና ይህም በአገራቸው ለመስራት እንዳነሳሳቸው አውስተዋል፡፡ 
ከኢድ እስከ ኢድ በሚል በእስልምና ሃማኖት ተከታዮች ዘንድ እንደ ቅዱስ ወር በሚታየው በረመዳን ፆም ወቅት የወደ አገር ቤት ጥሪን ተከትሎ ለመጡ ትናንት በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ በተደረገው የእንኳን ደህና መጣችው መርሃ ግብር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ 
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ በመልእክታቸው መገፋፋትና ጽንፈኝነትንም አውግዘው ለአንድነት እና መተባበር ተማጽነዋል፡፡ 
በዚሁ የእንኳን ደህና መጣችሁ መድረክ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የጉዞ ጥሪው የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባትና የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ጉልህ ሚና ያለው ነው ብለዋል፡፡ 

Äthiopien Eid-to-Eid Great Ethiopian Homecoming
ምስል Seyoum Getu/DW

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻል ዘመናትን ያለፈ ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸው ሰሞኑን በጎንደር የተከሰተውን ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ግጭት የማይገልፀን ብለው ኮንነውታል፡፡ ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪውም መንግስታቸው እየተገበረ የሚገኘው የአዲስ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋልም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ