1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ምግብ ዋስትና አሳሳቢነት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 7 2011

ከዓለም ሕዝብ መካከል ከየዘጠኙ ሰው አንዱ በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም በቂ ምግብ እንዳላገኘ የተመድ አስታወቀ። የሚራበው ሰው ቁጥርም ባለፉት ዓመታት እየጨመረ በመምጣቱም፣ በዚህ አንጻር ባስቸኳይ ርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ድርጅቱ በትናንቱ ዕለት የታሰበውን የዓለም ምግብ ቀን ምክንያት በማድረግ  አሳስቦዋል።

https://p.dw.com/p/36iHW
eco@africa Uganda Mais
ምስል DW

ዓ/አቀፉ ማህበረ ሰብ እስከ 2030 ረሀብን እንዲያጠፋ ጥሪ ቀርቦለታል።»

አምስት የተመድ መስሪያ ቤቶች፣ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት( ፋኦ)፣ የዓለም የጤና ድርጅት፣ የህጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ)፣  ዓለም አቀፉ የእርሻ ልማት (IFAD) እና የዓለም የምግብ ድርጅት(WFP) በመጨረሻ በጋራ ያወጡት ዘገባ እንደሚያሳየው፣ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በዓለም በረሀብ የሚሰቃየው ሰው ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። በተለይ ባለፈው ዓመት ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ  ደርሶ፣ ቁጥሩ ባለፈው አሰርተ ዓመት ወደነበረበት ከፍተኛ መጠን እየተመለሰ መሆኑን የተመ የምግብ እና እርሻ ድርጅት፣ በምህፃሩ ፋኦ  ዋና ስራ አስኪያጅ  ኾዜ ግራሲያኖ ዳ ሲልቫ  ከትናንት ጀምሮ በሮም እየተካሄደ ያለውን የአንድ ሳምንት የዓለም የምግብ ዋስትና ኮሚቴ ስብሰባ በከፈቱበት ወቅት አስታውቀዋል። 
« በዓለም የምግብ ዋስትና ዘገባ መሰረት፣ በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም ወደ 820 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች በቂ ምግብ አላገኙም። »
«የሚጠፋ ጊዜ የለም፣» የሚል ማስጠንቀቂያ ያሰሙት ዳ ሲልቫ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት ከተፈለገ አሳሳቢ እየሆነ በመጣው ረሀብ  እና በመንስዔዎቹ አንፃር ትግሉን ማጠናከር የግድ እንደሚል አስታውቀውዋል። በዚህም የተነሳ  የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓም ድረስ ረሀብን የማጥፋት ዓላማ ማስቀመጡን አመልክተዋል።

« ውዝግቦች፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥ የሆነው  አሳሳቢ የአየር ፀባይ ሁኔታ እና የኤኮኖሚ እድገት ዝግመት ረሀብን  በመታገሉ ረገድ የተገኙ መሻሻሎችን እየቀለበሱ ይገኛል። ረሀብን በጠቅላላ ለማጥፋት የተቀመጠውን ዓላማ ለማሳካት የተጀመሩ ጥረቶችን በእጥፍ የማሳደጉ ጊዜ አሁን ነው። »
በሞቃታማ አካባቢዎች የሚከሰተው ድርቅ እና ጎርፍ የስንዴ፣ ሩዝ እና በቆሎ ምርት እንዲቀንስ  በማድረግ ላይ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ እየባሰ ሊሄድ እንደሚችል የዓለም የምግብ ድርጅት ኃላፊ ዴቪድ ቤይስሊ ገልጸዋል። እንደ ቤይስሊ በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱ ወደ 23 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቅለዋል።
የተመድ አባል ሀገራት ከሶስት ዓመታት በፊት ለዘላቂዎቹ የልማት ግቦች ማሳኪያ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ድህነትን እና ረሀብን ለማብቃት ቃል ገብተው እንደነበር ያስታወሱት የፋኦ ዋና ስራ አስኪያጅ ዳ ሲልቫ ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ አቅሙን በሰባሰብ በጋራ እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።
« በረሀብ አንጻር ርምጃ መውሰድ ምርጫ አይደለም፣ ለሁሉም ዘላቂ አስተማማኝ የወደፊት ሁኔታ ለመፍጠር አስፈላጊ ርምጃ ነው። አሁን የምናደርገው የወደፊቱን እጣችንን ይወስናል። እስከ 2030 ረሀብን በጠቅላላ ማጥፋት አሁንም የሚቻል ነገር ነው። »
አለቅጥ ውፍረትም እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ከረሀብ ጎን ለጎን ሌላ አሳሳቢ ችግር መሆኑን ዘገባውን ያዘጋጁት የተመድ መስሪኢ ቤቶች በማመልከት፣ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለመሻቱ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ