1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የዓለም የቱሪዝም ቀን በጋምቤላ ተከበረ

Merga Yonas Bula
ሐሙስ፣ መስከረም 17 2011

የዓለም የቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ ዘንድሮ በርካታ የተፈጥሮ ሐብት በሚገኝበት የጋምቤላ ክልል ላለፉት ሶስት ቀናት ተከብሯል። በክልሉ የአገር ጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ መዳረሻዎች ቢኖሩም የመሰረተ-ልማት እጥረትን የመሰሉ ችግሮች ለዘርፉ ፈተና ሆነዋል። ነጃት ኢብራሒም የክልሉን ኃላፊ በበዓሉ አከባበር ላይ አነጋግራቸዋለች። 

https://p.dw.com/p/35bFh
Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

በየአመቱ መስከረም 17 ቀን የሚከበረው የአለም የቱሪዝም ቀን ዘንድሮም ለ39ኛ ጊዜ በጋምቤላ ተከብሯል። የጋምቤላ ክልል የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኩዋንግ ኦካይ እንደተናገሩት በዓሉ ሲከበር በአኙዋክ ዞን አቦቦ ወረዳ በሚገኘው የአልዌሮ ግድብ ጉብኝት ተደርጓል። የበዓል አከባበሩ ገና ሲጀመር ግን በጋምቤላ ተፈጥሮ በነበረ ግጭት ምክንያት የጸጥታ ሥጋት ያጠላበት ነበር። አቶ ኩዋንግ እንደሚሉት የበዓሉ አዘጋጆች እንግዶቻቸውን እንኳ መቀበል አልቻሉም።

አቶ ኩዋንግ እንደሚሉት የዘንድሮው በዓል አከባበር የምሳ ግብዣ፣ ባሕላዊ ጭፈራ እና የጀልባ ቀዘፋ ውድድር የተካተተበት ነበር። ለሶስት ቀናት በዘለቀው እና ትናንት የተጠናቀቀው የበዓል አከባበር በቱሪዝም ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ተደርገዋል። የፌደራል መንግሥት እና የክልሉ ሹማምንት የተሳተፉበትን በዓል ያከበረችው ጋምቤላ ብሔራዊ በርካታ አዕዋፋት እና የዱር እንስሳት የሚገኙባቸው ብሔራዊ ፓርክ እና ጥብቅ ደን የሚገኙባት ናት።

ከአዲስ አበባ በ850 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው እና ከ50 ሔክታር በላይ ስፋት ያለው የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ከሚገኙ አቻዎቹ ሁሉ በዱር እንስሳት ሐብቱ የበለጸገ ነው። የአኮቦ፣ ጊሎ እና ባሮ ወንዞች ፓርኩን አቋርጠው ይፈሳሉ። እስከ ሶስት ሜትር እርዝመት ባለው የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የሳር ምድር አንበሳ፣ ጉማሬ፣ ጎሽ እና የተለያዩ የአጋዘን ዝርያዎችን ጨምሮ ከ40 በላይ የዱር እንስሳት ይገኛሉ። አካባቢው ለአዕዋፍ ተመልካቾች እና ደን አፍቃሪዎች ተመራጭ ነው። አቶ ኩዋንግ እንደሚሉት ግን በፓርኩ የመሠረተ-ልማት ግንባታዎችን ጨምሮ በርካታ ያልተሰሩ ስራዎች አሉ።

ወደ ጋምቤላ የሚያቀኑ የአገር ጎብኚዎችን ፍላጎት ለማሟላት ብዙ ስራዎች ይቀራሉ የሚሉት አቶ ኩዋንግ የሚመሩት ተቋማት ሊጠናከሩ እንደሚገባ ያምናሉ። ለአገር ጎብኚዎቹ የሚሆኑ ማረፊያዎች፣ መዝናኛዎች እና የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል። በጋምቤላ ክልል የሚገኙት የቱሪስት መስህቦች ከኢትዮጵያውያን ይልቅ በውጭ አገር ጎብኚዎች እንደሚዘወተሩ የሚገልጹት አቶ ኩዋንግ ቁጥሩ ግን አናሳ መሆኑን ገልጸዋል።

ነጃት ኢብራሒም

ሸዋዬ ለገሠ