1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቦ ፍትህ ያጠላበት ለዉጥ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 9 2010

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በኦሮሚያ ፣በአማራ ፣በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በደቡብና በቤንሻንጉል ክልሎች መነሻቸዉ የተለያዬ ቢሆንም ግጭቶች ተከሰተዋል።በእነዚህ ግጭቶች የሰዎች ህይወት ጠፍቷል ንብረትም ወድሟል።በርካቶችንም ለመፈናቀል ዳርጓል።ከግጭቶች በተጨማሪም በደቦና በስሜታዊነት የሚፈጸሙ ጥቃቶችም  እየተበራከቱ መጥተዋል።

https://p.dw.com/p/33A51
Äthiopien Unruhen in Shashemene
ምስል Privat

Recent Mob Actions in Ethiopia. - MP3-Stereo

 እነዚህ ጥቃቶች የተጀመረዉን ለዉጥ ወደኋላ እንዳይመልሱ ብዙዎችን አስግቷል። ዶክተር ዐብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነዉ ከተሾሙ ካለፉት 4 ወራት ወዲህ በሀገሪቱ አሉታዊ የፖለቲካዊ ለዉጦች የታዩ ቢሆንም፤በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋሉት የሰዉ ህይወትና ንብረትን የሚያወድሙ ግጭቶች በተለይም የለዉጡ ዋና ተዋናይ በነበረዉ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ በስሜትና  በደቦ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸዉ ብዙዎችን እያነጋገረ ነዉ። በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈፀሙ ጥቃቶችና  በኦሮሚያ ክልል ሻሻመኔ ከተማ የተፈፀመዉ አሰቃቂ ግድያ ከዚያም በፊት በደብረ ማርቆስ፣ በባህርዳር እና በደሴ በወጣቶች የተፈጸሙ ጥቃቶች ለዚህ  ማሳያዎች መሆናቸዉ ይነገራል። እነዚህ ጥቃቶች በብዙዎች ዘንድ  በሀገሪቱ የተጀመረዉን ለዉጥ ሊያጠለሹ ይችላሉ የሚል ስጋትም አሳድሯል።የፖለቲካና የደህንነት ተመራማሪና ተንታኝኙ አቶ ሀሌሉያ ሉሌ ስጋቱን ይጋሩታል።
«ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር በአመፅ ከመጠየቅ በመንግስት ተቋማት ህግና ሥነ-ስርዓትን በተከተለ መልኩ ወደሚጠይቁበት ስርዓት መግባት የሚያስፈልግበት ወቅት ነዉ ብዬ አስባለሁ።ይህ ካልሆነ ህገወጥነት ስርዓት አልበኝነት እንደ ስርዓት ሆኖ ሊቀጥል የሚችልበት እድል ሊፈጠር ይችላል።»
የፀጥታና የደህንነት ተቋሞች ባለፉት ሶስት ዓመታት ለህዝባዊ ተቃዉሞዉ በሰጡት ምላሽ ሳቢያ ተቀባይነታቸዉና የመፈፀም አቅማቸዉ መዳከም፣ «ይህ ለዉጥ የመጣዉ በህዝብ ትግል ነዉ» በሚል የህዝብ የአሸናፊነትና የፈለግነዉን ማድረግ እንችላለን የሚል የድል መንፈስ፣እንዲሁም ለዉጡን ያልተቀበሉ ኃይሎች ግፊት ለችግሩ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ተመራማሪዉ አስረድተዋል። የአምቦ ዩንቨርሲቲ መምህርና ጦማሪ አቶ ስዩም ተሾመ በበኩላቸዉ በመሰል ጥቃቶች የሚገደለዉ ዜጋ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለዉ ገልፀዉ የችግሩን መነሻ በሁለት መንገድ ያዩታል።«አንድ በተቀነባበረ ሴራ ሆን ተብሎ እንዲህ ያለ ድርጊት እንዳይፈፀም ለዉጡን ለማጠልሸት ፤ጥላሸት ለመቀባት የሚደረግ እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል።ሁለተኛዉ ነገር እኛ ራሳችን የፖለቲካ ሊሂቃን፣ፀሃፊያን ጦማሪያን የምንባለዉ፤ሚዲያዉ ጭምር ህዝቡ ለእነዚህ የፀጥታ  ሀይሎች  እንዳይታዘዝ ተገዥ እንዳይሆን ከእነሱ ጋር ተባብሮ እንዳይሰራ ስናደርግ ስለነበር በዚህ ላይ የተሰራዉ ስራ ነዉ እንግዲህ አሁን እንዲህ ያሉ ክስተቶችን እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነዉ።»  ብለዋል።

Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher
Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu
ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

በዚህ መሰረት ለዉጥ እንዲመጣ ሲቀሰቅሱ የቆዩ አካላት በሙሉ  ወጣቱ በደቦ ከሚፈፅማቸዉ ስሜታዊ ጥቃቶች እንዲቆጠብ  የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸዉ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተካሄደዉ ህዝባዊ ትግል የመጣዉ ለዉጥ፤ መሰረታዊ የሆነ  የህግ ፣የፖለቲካና የትርክት ለዉጦች የታዩበት በመሆኑ በሀገሪቱ አብዮት ተብሎ ሊጠራ ይችላል ያሉት አቶ ሀሌሉያ ይህ አብዮት በህዝባዊ ተቃዉሞና እንቅስቃሴ የመጣ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን መንግስት የተወሰኑ የፖለቲካ ጥያቄዎች እየመለሰ በመሆኑና የቀሩትንም ለመመለስ ፈቃደኝነት እያሳየ በመሆኑ ለዉጡ አደጋ ዉስጥ እንዳይገባ ይህ ድርጊት ሊቆም ይገባል ነዉ ያሉት። ለዚህም መፍትሄ ያሉትን ይጠቁማሉ።
«መንግስትም ይሁን ተቃዋሚዎችና የመብት አቀንቃኞችም ቢሆኑ ህዝቦች ያላቸዉን ጥያቄ በህጋዊ መንገድ እንዲያቀርቡ ማበረታታትና ማስተማር። ሁለተኛዉና ዘላቂ የሚሆነዉ ግን በአካባቢ ደረጃ በክልልም በሀገርም ደረጃ ያሉ የደህንነትና የፀጥታ ተቋማት አጥፊዎችን ህግን በተከተለ መልኩ መቅጣት አለባቸዉ።»ነዉ ያሉት
መንግስት በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን ማህበረሰቡ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ይህንን ድርጊት ለማስቆም ማስተማር እንዳለባቸዉም ሙህራኑ ጨምረዉ አሳስበዋል።

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ