1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የመጀመሪያዎቹ አራት ኩባንያዎች 7 ሚሊዮን ብር ከባለወረቶች አግኝተዋል

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 1 2009

የወጣቶቹ አራት ጀማሪ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እየተንደረደሩ ነው። ዶ/ር እሌኒ ገብረመድኅን ባቋቋሙት ብሉ ሙን ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት ውስጥ የንግድ ሐሳባቸውን ሲያጠኑ እና ሲያደራጁ የከረሙት ወጣቶች ባለፈው ዓርብ ከባለወረቶች ጋር ተገናኝተው ሥራቸውን ለመጀመር ከ600,000 እስከ 3.2 ሚሊዮን ብር አሰባስበዋል።

https://p.dw.com/p/2jSZC
Äthiopien - Junge Young Unternehmer pitchen Ihre Start-Up-Ideen für potentielle Investoren
ምስል BlueMoon Ethiopia

ጀማሪዎቹ ኩባንያዎች ከባለወረቶች 7 ሚሊዮን ብር ሰብስበዋል

በአዲስ ጋራዥ ሐሳብ ይሰለቃል። ጋራዡ ለፈጠራ ሥራ የሚመች፤ ቀለል ያለ እና የተለያዩ ድርጊቶች እንዲከወኑበት ታቅዶ የተዘጋጀ የጀማሪ ኩባንያዎች መሰባሰቢያ፤ መተጋገዣም ጭምር ነው። ጋራዥ ቢሏችሁ ግን ጋራዥ እንዳይመስላችሁ። ጀማሪ ኩባንያዎች የንግድ ሐሳባቸውን የሚያዳብሩበት፤ ሙያዊ ሥልጠናዎች የሚከታተሉበት ፈጣን ገመድ አልባ ኢንተርኔት እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ያሉበት ማዕከል ነው። የብሉ ሙን ኢትዮጵያ ኢንኩቤተር የሥራ ፈጣሪዎች መፈልፈያም የሚገኘው ከዚያው ከአዲስ ጋራዥ ውስጥ ነው። 

ሥመ-ጥሩዋ የኤኮኖሚ ባለሙያ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድኅን የመሠረቱት እና አዲስ ጋራዥ የሚገኝበት ብሉ ሙን ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ አዋጪ የንግድ ኃሳብ ይዘው ብቅ ያሉ ወጣት የሥራ ፈጣሪዎችን ትኩረት ከሳበ ወራት ተቆጠሩ። ወጣት የሥራ ፈጣሪዎች በብሉ ሙን ኢትዮጵያ ሐሳባቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዛቸው ሥልጠናዎች ያገኛሉ። የህግ፤የሒሳብ አያያዝ እና የገንዘብ አስተዳደር አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ግንኙነት እንዲጀምሩም እገዛ ይደረግላቸዋል። የላቀ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር ተገናኝተው እንዲነጋገሩ እድል ያገኛሉ። ዶ/ር እሌኒ ጀማሪ ኩባንያዎች በተቋማቸው ውስጥ የሚያሳልፉት ጊዜ የፈጠራ ሐሳባቸው ወደ ተግባር የሚቀየርበት እንደሆነ ያስረዳሉ።

ዶ/ር እሌኒ ተቋማቸውን ከጫጩት ማስፈልፈያ ጋር ያመሳስሉታል። ኢንኩቤተር እንቁላሎች ጫጩት ሆነው እንዲፈለፈሉ የሚያሻቸውን ሙቀት እንደሚያቀርብ ሁሉ ብሉ ሙንም ሥራ ፈጣሪዎችን በሥልጠና ክህሎት ያስታጥቃል።

Äthiopien - Junge Young Unternehmer pitchen Ihre Start-Up-Ideen für potentielle Investoren
ምስል BlueMoon Ethiopia

ብሉ ሙን ኢትዮጵያ አዋጪ የንግድ ሐሳብ ላላቸው በሩን አንድ ብሎ ሲከፍት ቀድመው ከገቡ መካከል ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓመት በሜካኒካል ምኅንድስና የተመረቁት ሦስት ወጣቶች ይገኙበታል። ቢኒያም ወንድወሰን፤ ብርሐኔ አብርሐሌ እና ብሩክ ግርማ ይባላሉ። ሜካኒካል መኅንዲሶቹ ከብስባሽ ማዳበሪያ የማምረት እቅድ ነበራቸው። "ከጓደኞቼ ጋር ሥራ ለመስራት አስበን ምንም አይነት የገንዘብ ምንች አላገኘንም። አዲስ ተመራቂዎች ነን" የሚለው ብሩክ ቤተሰቦቻቸው ለሥራቸው መነሻ የሚሆን ገንዘብ የመስጠት አቅም እንደሌላቸው ይናገራል። ብሩክ ግርማ እንደሚለው የገንዘብ እጦት እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ጋሬጣ ሆኖባቸው እርግፍ አድርገው ለመተው ሲያማትሩ ብሉ ሙን ኢትዮጵያ ብቅ አለ።

ብሉ ሙን ኢትዮጵያ የሚቀበላቸው የፈጣራ ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ በግብርና ላይ ያተኮሩ ናቸው። ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን እንደሚሉት ወደ ኢንዱስትሪ ለሚንደረደረው የአገሪቱ ኤኮኖሚ ዛሬም ድረስ ግብርና የጀርባ አጥንት መሆኑ በዘርፉ ላይ ለማተኮራቸው ቀዳሚው ምክንያት ነው። ከምርት በፊት እና በኋላ ባሉት የእሴት ሰንሰለቶች ላይ የታቀዱ ሐሳቦች፤ የእንስሳት እና የዓሣ ሐብትን የተመለከቱ ውጥኖችም በብሉ ሙን ቦታ አላቸው።

እንደነ ብሩክ ሁሉ ወደ ብሉ ሙን ኢትዮጵያ ቀድመው ከገቡት መካከል ኑ ኤክስቼንጅ ሌላው የወጣቶች ጀማሪ ኩባንያ ነው። አምስት አባላት ያሉት ኑ ኤክስቼንጅ ኩባንያ መረጃን በድረ-ገፅ እና በአጭር የፅሁፍ መልዕክት በማቀበል የቀንድ ከብት ግብይትን የማዘመን ውጥን አለው። ኩባንያው ወደ ሥራ ሊያስገባው ያቀደው የመገበያያ ድረ-ገፅ በገዢ እና ሻጭ መካከል ያለውን ርቀት የሚሞላ ነው። ለሽያጭ ስለሚቀርበው የቁም ከብት አስፈላጊ መረጃዎችን ሁሉ ከአንዱ ወደ ሌላው ያቀብላል። የኩባንያው ሥራ አስፈፃሚ ስባጋዲስ ሊጋር እንደሚለው ስራቸው በቄራ አገልግሎት አቅራቢዎች እና የስጋ ምርት ለውጭ ገበያ በሚያቀርቡ ነጋዴዎች ዘንድ ተፈላጊነት እንዳለው አረጋግጠዋል።  

Äthiopien - Junge Young Unternehmer pitchen Ihre Start-Up-Ideen für potentielle Investoren
ምስል BlueMoon Ethiopia

ላለፉት አራት ወራት ኒቸር ፎር ኔቸር፤ ኑ ኤክስቼንጅን ጨምሮ የአትክልት ምርቶችን በኢንተርኔት የማገበያየት ሐሳብ ያለው ገበያ ኔት እንዲሁም ከግብርና ተረፈ ምርት ታዳሽ ኃይል የማምረት ውጥን ያለው እፎይታ የተባለ ኩባንያ በብሉ ሙን ኢትዮጵያ የንግድ ሐሳቦቻቸውን ሲያደራጁ፤ ገበያቸውን ሲያጠኑ እና ፈተናዎቻቸውን ሲመረምሩ ቆይተዋል።

ብሉ ሙን ኢትዮጵያ አዋጪ የንግድ ሐሳብ እና ክኅሎት ያላቸውን ፍለጋ መላ አገሪቷን አስሷል። ከኢትዮጵያ መንግሥት የሲቪክ ተቋማት እና የሙያ ማሰልጠኛ ት/ቤቶች ጋር በመተባበር በሰባት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሥራ ፈጣሪዎችን ቀልብ ለመግዛት የመንገድ ላይ ትዕይንቶች አካሒዷል። የድርጅቱ ጥሪ ቀልባቸውን የሳባቸው አንዳች የሥራ ውጥን ያላቸው ወደ ብሉ ሙን ኢትዮጵያ ከመቀላቀላቸው በፊት ግን ሊያሟሉ የሚገቧቸው መሥፈርቶች መኖራቸውን ዶ/ር እሌኒ ይናገራሉ።

አራቱ ኩባንያዎች ሊሰሩ የወጠኑት በግብርና እና ተያያዥ የሥራ ዘርፍ ላይ ነው። አቶ ብሩክ የወጣቶቹ እቅዶች ሲመረጡ ከፍ ያለ ፈተና ያላቸው ነገር ግን ለውጥ የማምጣት አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑት ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል። በአራት ወራት ቆይታቸውም የንግድ ሐሳብ ዝግጅት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ገበያቸውን አጥንተዋል፤ ተወዳዳሪዎቻቸውንም ለይተዋል።

ኑ ኤክስቼንጅ ወደ ሥራ ሲገባ በአምስት አመታት ውስጥ በቀንድ ከብት ግብይት ውስጥ የጎላ ሚና ሊጫወት አቅዷል። ኩባንያቸው ከዚህ ቀደም በሌሎች ተቋማት የተዘጋጁ የአሰራር ሥልቶችን በመጠቀም አስፈላጊውን መረጃ በግብይት ሒደቱ ውስጥ ለሚገኙ ሻጭ እና ገዢዎች ያቀርባል። የኑ ኤክስቼንጅ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ስባጋዲስ ሊጋር ወደ 59 ቢሊዮን ዶላር ከሚደርሰው የቁም እንስሳት ግብይት አንድ በመቶ ድርሻ እንኳ ቢኖረን እቅዳችን ችግር ፈቺ ይሆናል የሚል እምነት አለው። በቀን እስከ 14,000 የቁም እንስሳት ለግብይት በሚቀርቡበት የአዳማ ገበያ የተሞከረው እቅድ በብሉ ሙን ታሽቶ ወደ ተገልጋዮቹ ሊያመራ በዝግጅት ላይ ነው።

Äthiopien - Junge Young Unternehmer pitchen Ihre Start-Up-Ideen für potentielle Investoren
ምስል BlueMoon Ethiopia

እነ ስባጋዲስ ሊጋር የኩባንያቸውን 49 በመቶ ለባለወረቶች የሸጡት ለወራት የተዘጋጁበትን የንግድ ሐሳብ ለባለሃብቶች አስረድተው የቀረበላቸውን ጥያቄ መልሰው ከብዙ የማሳመን ሒደት በኋላ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ ሲያደርጉ የሚታዩት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፤ አቶ ዳንኤል ጋድ፤ ቤተልሔም ጥላሁን እና አቶ አዲስ አለማየሁ የወጣቶቹን የሥራ እቅዶች መዝነው ከአራቱ ኩባንያዎች መካከል አክሲዮን ገዝተዋል። ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን አራቱን ባለወረቶች አንበሶች፤ ዝግጅቱን የአንበሶች ዋሻ ሲሉ ይጠሩታል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው ይኸ አሰራር መሔጃ ላጡ ጀማሪ ኩባንያዎች እና ወጣቶች መላ መዘየድ ዋንኛ እቅዱ ነው።

ነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሔደው ዝግጅት የአራቱ ኩባንያዎች ዋጋ በ200 እጥፍ አድጓል። አራቱ ባለወረቶች ለአራቱ ኩባንያዎች 7 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገዋል። የኩባንያውን 13,200 ድርሻዎች የሸጠው ኔቸር ፎር ኔቸር ሥራውን ለመጀመር 3.2 ሚሊዮን ብር ከባለወረቶቹ አግኝቷል። ወጣቱ ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ግርማ እንደሚለው ገንዘቡን ከማግኘታቸው በላይ ከስኬታማ ሰዎች ጋር ለመስራት መቻላቸው ደስታ ፈጥሮላቸዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥራቿ እና የመጀመሪያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር እሌኒ በአራቱ ኩባንያዎች ሥኬታማነት ደስተኛ ናቸው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ