1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን አምባሳደር ስለጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 6 2011

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን መንበሩ ከመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ ዐርብ ታኅሣሥ 5 ቀን፣ 2011 ዓም ከ30 በላይ ከሚኾኑ የተለያዩ የአውሮጳ አምባሰደሮች ጋር ተገናኝነተው ተነጋገሩ። ጠቅላይ ሚንሥትሩ ከአምባሳደሮቹ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ስለ ወደፊት ርእያቸው እና የለውጥ ዕቅዳቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል።  

https://p.dw.com/p/3ACAo
Brita Wagener Botschafterin im Irak Archiv 2013
ምስል picture-alliance/dpa/Jörg Carstensen

«ግባቸውን ማሳካት የሚችሉት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሃገራት ድጋፍ ሲያገኙ ነው»

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን መንበሩ ከመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ ዐርብ ታኅሣሥ 5 ቀን፣ 2011 ዓም ከ30 በላይ ከሚኾኑ የተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት አምባሰደሮች ጋር ተገናኝነተው ተነጋገሩ። ጠቅላይ ሚንሥትሩ ከአምባሳደሮቹ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ስለ ወደፊት ርእያቸው እና የለውጥ ዕቅዳቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚንሥትሩ አዲስ አበባ ከሚገኙ አምባሰደሮች ጋር የተነጋገሩት ዐርብ ጠዋት ነበር። በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫገነር ከDW ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ጠቅላይ ሚንሥትሩ በዋናነት «እስካሁን የትኛው ለውጥ እንደተኪያሔደ፤ የትኞቹ ዕቅዶችስ እንደሚኖሩ» ለአምባሳደሮቹ መግለጥ መፈለጋቸውን ተናግረዋል።

አምባሳደሯ አክለውም፦ «ጥልቅ ለውጥ መኖር እንደሚገባው፤ ሀገሪቱም ወደ ዲሞክራሲ ጎዳና እያቀናች፤ ግልጽ እየኾነችም እንደሆነ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚኖሩ ዜጎች በአጠቃላይ በዘላቂነት ሕይወታቸው እንዲስተካከል  ኢኮኖሚያዊ ለውጥ መኖር እንዳለበት» ጠቅላይ ሚንሥትሩ መግለጣቸውን ተናግረዋል። ከዚያ ባሻገርም  ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ፦ «አኹን ያለው ሽግግር ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ መኾኑን ግልጽ» ማድረጋቸውን «ለዚያም ምክንያታቸውን ሲገልጡ ባለፉት ጊዜያት የፖለቲካ ለውጥ ሲኖር ወይንም በአመራር ለውጥ ሲከሰት ሁሌም ከአመጽ ጋር የተቆራኘ መኾኑን ተናግረዋል። «ይኽ የአኹኑ ሽግግር ወሳኝ የኾነው ሠላማዊ በመኾኑ ነው» ማለታቸውን አክለዋል።   

የወደፊት ርእይ ሊኖር የሚገባው ነገር ነው ያሉት አምባሳደሯ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ርእይ እና ግባቸውን ማሳካት የሚችሉት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሃገራት ድጋፍ ሲያገኙ ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚንሥትሩ ላለአምባሳደሮቹ ካሰሟቸው ንግግሮች የትኛው ይበልጥ ትኩረታቸውን እንደሳበው ተጠይቀው ሲመልሱ፦ «እንደሚመስለኝ ወደ ዲሞክራሲ ጎዳና የሚደረገው ጉዞ፤ በ2020 ለሚካሄደው ምርጫ የተያዘው ዕቅድ፤ በፍትኅ ስርዓቱ የተጀመረው ለውጥ፤ እንዲሁም የጭቆና መሣሪያ የነበሩት እንደ የጸረ ሽብር ሕግ፣ የመገናኛ አውታር ሕግ የመሰሉ ከባድ ሕግጋት ላይ ለውጥ እና አዲስ ሕግጋት መኖሩ ትኩረት ስቧል። እናም ሌላው ካለፉት ረዥም ጊዜያት አንስቶ አንድም ጋዜጠኛ እስር ላይ አለመኾኑ ሲመስለኝ በደንብ ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው» ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚንሥትሩ፦ ስለ እርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ ስለ ድንበር እና ማንነት ኮሚሽን ምሥረታ በውይይቱ ወቅት መናገራቸውን አምባሳደር ብሪታ ቫገነር ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ፦ «ሀገሪቱ ባለችበት እንድትቀጥል እንደሚፈልጉ፣ ነገሮችን ከልብ መቀየር እንደሚሹ፣ እርቀ ሰላም  ወርዶ እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲሰርጽ በመሥራት » ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኝነታቸው በውይይቱ ወቅት ካደረጉት ንግግር መገመት እንደሚቻል አምባሳደሯ ጠቁመዋል። ከንግግሩ በኋላም አምባሳደሮቹ ከተሰበሰቡበት ወጣ ብለው ሻሂ ቡና እያሉ ከጠቅላይ ሚንሥትሩ ጋር ዘና  በማለት ንግግራቸውን መቀጠላቸውን አምባሳደሯ ገልጠዋል። 

የጠቅላይ ሚንሥትሩ ጽ/ቤት በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮቹ እንደገለጠው ከኾነ አምባሳደሮቹ አዲሱ አስተዳደርን አወድሰዋል። ከጀርመን አምባሳደር ሪታ ቫገነርን ጋር በጀርመንኛ ቋንቋ በስልክ ከተደረገው ቃለ መጠይቅ ላይ የተቀነጨበ ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ