1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርባ እና ወገብ ሕመም ምንነት

ማክሰኞ፣ ጥር 7 2011

በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች ስለ ወገብ እና የጀርባ ሕመም ችግር ሲናገሩ መስማት እየተለመደ መጥቷል። በተለይም ከዚህ ህመም ጋር በተገናኘ የዲስክ መንሸራተት ችግር ሲባል እንሰማለን፤ በእርግጥ ይህ የጤና ችግር ምንድነው? አስቀድሞ ሊደረግ የሚገባ ጥንቃቄስ አለ? ሕክምናውስ ምን ይመከራል?

https://p.dw.com/p/3BXDn
DW Fit&gesund Bandscheibe
ምስል HR

«የዲስክ መንሸራተት ምንድነው?»

አጥንት እና መገጣጠሚያ ላይ የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮችን በሚመለከት የሕክምና ዘርፍ በጀርመን ሀገር ድሬዝደን ከተማ ለረዥም ዓመታት በከፍተኛ ሃኪምነት በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶክተር ውብታየ ዱሬሳ ተክሌ፤ ስለጀርባ ህመም ሲያብራሩልኝ አዲስ መኪና እና ያገለገለ መኪናን በምሳሌነት በመጥቀስ ነበር። አዲስ መኪና ለተወሰኑ ዓመታት ያለምንም ቴክኒካዊ እንከን ፈልሰስ ብሎ የመሽከርከሩን ያህል ዓመታት ሲያስቆጥር ግን ለጥገና መወሰድ እንደሚኖርበት ያስታውሳሉ። የሰዎች አካልም በዚህ መልኩ ሲታይ፤ ቁመናን ደግፎ የሚይዘው የጀርባ አጥንት፤ ከጊዜ እና አገልግሎት ብዛት በአንድ ወቅት ላይ እንከን ሊገጥመው ግድ መሆኑንም አንስተውልኛል። እርግጥ ነው የጀርባ እና ወገብ ሕመም የግድ ዕድሜ ጠብቆ የሚመጣ ላይሆን ይችላል። በተለይ በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች እንዲህ ካለው ህመም ጋር በተገናኘ ስለዲስክ መንሸራተት ሲናገሩ ይሰማል፤ ምን ማለት ይሆን? ወደዚያ ዝርዝር ከመዝለቃችን በፊት ግን ዶክተር ውብታየ የጀርባ አጥንታችንን ተፈጥሮ እንዲህ ያብራራሉ።

Symbolbild Medizintechnik
ምስል picture-alliance/dpa/H. Wiedl

«የጀርባ አጥንታችን ከጭንቅላታችን ጋር የሚያያዝ ነው፤ እሱም ወደ ሠላሳ ሁለት፣ ወደ ሠላሳ ሦስት አጥንቶች አሉ። አጥንቱም በመሀሉ ላይ ክፍተት አለው። አጥንቶቹ አንድ ላይ ተገናኝተው ተደራርበው ያሉ ናቸው ከጭንቅላት እታች ድረስ። በመሀላቸው ያለው ባዶ ቦታ አንድ ቱቦ ይፈጥራል። ቱቦው የሕብለሰረሰር ፤ ጭንቅላታችን ከአንጎል ጋር የተያያዘው ክፍል ሕብለሰረሰር የሚወርድበት መስመር ነው። ያም ለእሱ መከላከያው ነው ከጉዳት መጠበቂያው ነው ይሄ አጥንቱ። እና እነዚህ ከሠላሳ ሁለት እስከ ሠላሳ ሦስት የሚሆኑት የጀርባ አጥንቶች እርስርበርሳቸው ተደራርበው ሲቀመጡ በመሀላቸው ላይ እርበርሳቸው እንዳይፈጫጩ እንደትራስ የሚያገለግል አለ። ይሄም በስስ ስሮች እንደ ክብ ሆኖ የሠራ ሲሆን መሃሉ ላይ ደግሞ ጠብ ያለ ፈሳሽ ነገር አለ።»

ይህ ችግር እውነትም ተከስቷል ለማለት ይላሉ የዘርፉ ከፍተኛ ህክምና ባለሙያ፤ ዲስኩ ወይም እሳቸው በገለፁት መንገድ ደግሞ የጀርባ አጥንቶች እንዳይፋተጉ እንደትራስ የሚያገለግለው ለስላሳ ነገር ተንሸራቷል ለማለት ትክክለኛ ምልክቶቹ ወሳኝ ናቸው። 

Tod durch Kekse Flash-Galerie
ምስል Fotolia/ArTo

«ጀርባን ብቻ የሚያምም ከሆነ ብዙውን ጊዜ ይሄ የዲስክ መንሸራተት አይደለም፤ የጀርባ አጥንቶች መገናኛ ላይ ያለ ችግር ሊሆን ይችላል። አጥንት ጋር የሚያያዙ የጡንቻ መጨረሻዎች ወይም መያያያዣዎች ሊሆኑ ይችላሉ። እና የዲስክ መንሸራተት ብዙውን ጊዜ የሚመጣው ተለቅ ባሉ ሰዎች፤ በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ ወይም ለአቅመ አዳም በደረሱ ሰዎች ላይ ነው የሚመጣው። »

በዕድሜ ምክንያት ሊያጋጥም የሚችለው የጀርባ ሕመም እንዳለ ሆኖ ከባድ ዕቃ በምናነሳበት ጊዜ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልገን የሚያሳስቡት ዶክተር ውብታየ ቅጥ ያጣ ውፍረትም ሌላው መዘዝ መሆኑን ያነሳሉ። ይህ ብቻ አይደለም ዕድሜ ሳይገፋ የወገብ እና የጀርባ ህመም ሊያስከትል የሚችሉ ምክንያቶችንም ከዚህ ጋር እንደሚገኛኙም ይናገራሉ። ዶክተር ውብታየ ዱሬሳ ተክሌ በጀርመን ሀገር ድሬዝደን ከተማ ከፍተኛ የአጥንት ህክምና መስጪያ መንግሥታዊ ሀኪም ቤት የሚያገለግሉ የዘርፉ የቀዶ ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ