1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚንሥትሩ 1ኛ ዓመት የሥልጣን ዘመንና እስክንድር

ዓርብ፣ መጋቢት 27 2011

በዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት መሰናዶዋችን የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ አንደኛ ዓመት የሥልጣን ዘመንን በተመለከተ የተሰጡ አስተያየቶችን ቃኝተናል። እንዲሁም በአዲስ አበባ ጉዳይ ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋች እስንድር ነጋ የሰጠው መግለጫን በሚመለከት የተሰዘነዘሩ አስተያየቶችንም አሰባስበናል።

https://p.dw.com/p/3GGmm
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ወደ ከፍተኛው ሥልጣን መንበሩ ከመጡ አንደኛ ዓመታቸውን ያስቆጠሩበት ንግግራቸውን በዚሁ ሳምንት አሰምተዋል። በሚሊኒየም አዳራሽ በተከናወነው ስነስርዓት ጠቅላይ ሚንሥትሩ ያሰሙትን ንግግር ተከትሎ በርካቶች የድጋፍ እና የተቃውሞ አስተያየቶቻቸውን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ገልጠዋል። ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ «የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ)» በሚል በራስ ሆቴል እንዳይሰጥ የተከለከለውን መግለጫ እና ማብራሪያ በዚሁ ሳምንት ሰጥቷል።  በኹለቱም ርእሰ-ጉዳዮች ላይ አስተያየቶቹን በስፋት ቃኝተን አሰባስበናል።

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የአንድ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውን በተመለከተው የዝክር መርኃ-ግብር ንግግር ካሰሙ በኋላ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ድጋፍ እና ነቀፌታ አሰምተዋል። መርኃ ግብሩ አዲስ አበባ በሚገኘው ሚሊኒየም አዳራሽ  በዚሁ ሳምንት ሲከናወን፤ ጠቅላይ ሚንሥትሩ ባሰሙት ንግግር ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፤ በፓለቲካ፣ በማኅበራዊ ዘርፎች ተገኙ ያሏቸውን ለውጦች ዘርዝረዋል። በንግግራቸው ተደምመው አድናቆት የቸሩ የመኖራቸውን ያኽል፤ ውሳኔ ላይ መወላወል ይታይባቸዋል የሚሉ አስተያየቶች ተበራክተዋል።  

«በሁለት ተቃራኒ ጫፎች ተሰክተው ያሉ የአሀዳዊነትና የብዘኃነት አቋሞችን ተራ በተራ እያስደሰቱ መጓዝ ሩቅ አያስኬድም። ደግሞም የአቋም መለኪያ ሊሆኑ የሚችሉት ሀገራዊና ክልላዊ ጥያቄዎች መች ተነኩ?» የሚል አስተያየት በፌስቡክ ገጹ ያሰፈረው ገዳ ኤም ቱፋ ነው። ጃጌማ አበበ የሚባል የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ በአጭሩ ወጣዩን አስተያየት ሰጥቷል። «በአፍ አንደኛ በተግባር/በአፈጻጸም/ ዜሮ» የሚል።

«የተገኘውን ሰላምና ነፃነትን ተቻችለን ተከባብረን ካላቆየነው የጠላነውን ያሳለፍነውን ችግርና መከራ መናፈቃችን አይቀርም። ሊሆን ብሎም ሊታሰብ የማይችል ከአራት ዐሥርተ-ዓመታት ከሃገራቸው እርቀው ለነበሩ ነገር ግን በመንግስት ጫና እና ፖለቲካ ሰበብ ሰዎችን ወደ ሃገራቸው ማብቃት፤ ግፍና በደል በእስር የተሰቃዩትን የነፃነት አየር ማሳየት፤ ከዚህ በላይ ምን አለ?» ሲል አድናቆቱን የቸረው ማneኲሳ አዲስ ነው። ጠቅላይ ሚንሥትሩም በሚሌኒየሙ ንግግራቸው ለተሠሩ ሥራዎች ዕውቅና መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በለውጡ ሂደት የደገፏቸውንም አመስግነዋል።  ሕዝብ ጠብቆ ላላከናወኗቸው ጉዳዮችም ይቅርታ ጠይቀዋል።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed Rückblick auf die einjährige Millennium Hall
ምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ንግግር ቀልባቸውን ከገዛቸው አድማጮች መካከል አንዱ የኾነው ያስ ያስር፦ «ጠቅላይ ሚስትሩ የተናገሩት ልብ የሚነካ ነው፤ ግን ግልፀኝነት በጣም ይቀራል» ሲል በፌስቡክ ገጹ ጽፏል። ለምን እንዲያ እንዳለ አብነት ጠቅሶም ያብራራል፦ «ለምሳሌ ጌድዮ ከጉጂ፤ ቅማንትና ትግራይ ከጎንደር፤ አማራ ከኦሮሚያና ከሱማሌ ክልል፤ በተጨማሪም ከቡራዮ ከለጋ ጣፎ ከሰበታ ኢትዮጵያውያን ሲንገላቱ ጠንከር ያለ አቋም አልወሰዱም» ብሏል።

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ያስተላለፈትን መልዕክት አስመልክቶ የጻፈው ሙሉጌታ ካሣ ንግግራቸውን፦ «ደስ የሚባል ነዉ» ሲል ገልጦታል። ድጋፉን በመግለጥም፦ ወደፊት ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያላቸውን ነጥቦች ዘርዝሯል። «1ኛ የሕግ የበላይነት በሁሉም የሥራ መስክ ይከበር። 2ኛ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸዉ የሚል የመለየት ሥራ ይሥራ። 3ኛ የለዉጥ ደጋፊ ማነዉ የሚለዉን የመለየት ሥራ ይስራ» በማለት በአራተኛ ደረጃ፦ «ያጨበጨበለት ሁሉ የወደደዉ እንዳይመሥለዉ። አመሠግናለሁ» ሲል ጽሑፉን አጠናቋል።

ክንፈ ሐዱሽ ጠንከር ያለ ተቃውሞውን በትዊተር ገጹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲህ ሲል አስፍሯል። «ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ተቋማትን እና እሴቶችን በመላ በሚባል ደረጃ አጥፍተዋል። የቀዳሚዎቻቸውን ስኬት በማጣጣል የብዙኃኑን ስሜት ለመያዝ ይጥራሉ።»

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ በሚሌኒየሙ ንግግራቸው፦ «ዘመም ያለችውን ሀገሬን ማቅናት እንጂ ከዚያ የተለየ ሸፍጥም ሆነ ተግባር የለኝም» ብለዋል።  ይኽን አባባላቸውን ያካተተው ንግግራቸው በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተንሸራሽሯል።

«ምንም እንኳ ችግሮችንና መሰናክል ቢኖሩ አሑንም ተስፋችን አልተሟጠጠም። ይህን ስል ግን የአገራችን ለዓመታት እየተዘራ የነበረ መርዝ በአንዴ ካልተስተካከለ የሚል እምነት የለኝም። ግዜ እንደሚያስፈልግና ከባድ ሥራ እንደሚጠይቅ እገነዘባለሁ። ነገር ግን የእስካሁኑን አካሔድ ይፈተዋል የሚል እምነት የለኝም። በተለየ አካሄድና የመሪነት ሚና ሊያሳዩን ይገበዋታል እሚል እምነት አለኝ። ፈጣሪ ይርዳዎት!! ኢትዮጵያ ለዛለለም ትኑር!»  የጋብዞ ካሣሁን መልእክት ነው።

ከጋብዞ ፍጹም ተቃራኒ የኾነ አስተያየት በፌስቡክ ገጹ የጻፈው ሞላ ወዳጆ ፦ «በ27 ዓመት የተሠራ ሥራ በአንድ ዓመት ወድማል፤ ለውጥ የለም ነውጥ ግን አለ» ብሏል። «አሁን የትኛው ክልል ነው ወደ ሌላ ክልል ሂዶ መስራት የሚችለው» ሲል ይጠይቅና «አይቻልም» ሲል ይመልሳል።

«ለዉጥ አለ ማለት ይከብደኛል። ሰላም ያጡና የተፈናቀሉት ይመስክሩ» የሁምቦ አበላ አጭር አስተያየት ነው።

«ጥያቄ አለኝ» ሲል የሚንደረደረው ደግሞ ጥላሁን ጽጌ ነው በትዊተር ጽሑፉ። «የለገጣፎና ሰበታ ተፈናቃዮች ሕገወጥ የሚለው ታርጋ እንደተለጠፈባቸው ሊቀሩ ነው ማለት ነው?» ሲልም ጥያቄውን ያቀርባል።«ሰፋሪዎች የሚለው ቃል መገለጫቸው ሆኖ ሜዳ ላይ እንደተበተኑ ሊቀሩ ነው? ሊለመድ ነው…?» ሲልም ጽሑፉን በጥያቄ ይቋጫል።

Kombobild Eskinder Nega und Jawar Mohammed

ሌላው በሳምንቱ ዐቢይ መነጋገሪያ ኾኖ የቆየየው የአዲስ አበባ ሕዝብ ወክሎናል በሚል በጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ አስተባባሪነት የተቋቋመው «የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ)» ጉዳይ ነው። እስክንድር እና የምክር ቤቱ አባላት ባለፈው ሳምንት በራስ ሆቴል ሊሰጡት የነበረው መግለጫ መከልከሉ በተመለከተ በዚሁ ሳምንት በእስክንድር ነጋ ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥተዋል። ባለፈው ሳምንት መግለጫ እንዳይሰጡ በፖሊስ ሲከለከሉ የሚያሳዩ በድብቅ መቀረጻቸው የተነገረላቸው የተንቀሳቃሽ ምስሎች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭተዋል።  

ዳዊት ያዴታ በፌስቡክ ጽሑፉ፦ «በአንድ አዳራሽ የተሰበሰቡ ሰዎች ስለወከሉኝ "ባለ አደራ ነኝ" ማለት ከተቻለ በስልጣን ላይ ያለዉን አስተዳር ሕጋዊ አይደለም ማለት እንዴት ይቻላል?» ሲል በመጠየቅ ስለ «የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት» ጽፏል።

እዮስያስ ዜና በተቃራኒው ባሰፈረው ጽሑፉ፦ «እራሱን የባለአደራ ምክር ቤት ብሎ የሰየመ አካል የለም። ታስፈልጉናላችሁ ብሎ የሰየማቸው ነዋሪው ህዝብ እንጅ እነሱ በራሳቸው ራሳቸውን አልወከሉም» በማለት የመገናኛ አውታሮች እና ሰው አስተካክሎ እንዲጽፍ ጠይቋል።

የመብት ተሟጋቹ ጃዋር መሐመድ በፌስቡክ ገጹ ስለ አዲስ አበባ «ባለአደራ ምክር ቤት»  ጽሑፍ አያይዟል። በቀይ ቀለም መደብ የተጻፈው ጃዋር ያያዘው ጽሑፍ በትምህርተ ጥቅስ የተቀመጠ ሲኾን፤ ተናጋሪው ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እንደኾኑ ይጠቅሳል። ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል። «ባለአዳራ ምናምን የሚባለው ነገር ለኔ ትክክል አይመስለኝም። አቶ ታከለ ይሄን የማሸጋገር ሂደት በሚመለከት በትክክል ያልሠራው ነገር አለ ከተባለ ሂስ ማቅረብ ጥሩ ነው» ይላል ጃዋር ያያዘው ጽሑፍ።

ተስፋ ዓለም የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ክልከላው በተመለከተ ተቃውሞውን እንዲህ ገልጧል። «ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሊሰጥ የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ መታገድን በተመለከተ ፊት ለፊት የምናውቀው የአገራችን መሪዎች ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳልተከለከለ ቢናገሩም ድብቁ እና በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላትን እንደፈለገው በሚያዘው ስውሩ ኃይል በተላለፈ ትእዛዝ በሚመስል መልኩ ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳይካሄድ መደረጉን መገመት ይቻላል» ብሏል።

ክልከላውንም ሕገ-ወጥ ድርጊት ነው በማለት፦ «ይህ ሕገወጥ ድርጊት ወደ ከፋ ችግር ከመሸጋገሩ በፊት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ የሕግ የበላይነት እና የዜጎች መብት እና ደህንነት እንዲጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ አሳስባለሁ» ሲል ጽሑፉን ቋጭቷል።

አሸናፊ ካቤታ አጠር ባለው ጥያቄው፦ «ማን አደራ ሰጠው?» ሲል፤ ዜዶ ጊ፦ «እስክንድር ምርጡ የኢትዮጵያውያን ወኪል ነው !! ዘረኞች አትንጫጩ» ብሏል። የኹለቱም አስተያየት የሰፈረው በፌስቡክ ነው።

ሳምሶን ይመር በትዊተር ገጹ፦ «የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ እግዚአብሔር የሰጠውን ትዕግስት እና ጥንካሬ የምገልፅበት ቃላት ያጥረኛል። ድል ለዲሞክራሲ»  ሲል አድናቆቱን ገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ