1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጤፍ ባለቤትነት መብትን ለማስመለስ 

ማክሰኞ፣ ግንቦት 14 2010

በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ለዘመናት  በምግብነት የሚያገለግለዉ  ጤፍ አሁን አሁን በተለያዩ አገሮች መታወቅ ጀምሯል። መታወቁ ባይከፋም ጤፍን ለማስተዋወቅ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ያደረገ አንድ የኔዘርላንድ ኩባንያ በተለያዩ የአዉሮጳ ሀገሮች የጤፍ ባለቤትነት መብት ማግኘቱ ግን ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።

https://p.dw.com/p/2y8J9
Bildergalerie Äthiopien Teff
ምስል DW/J. Jeffrey

Attorney General to sue Dutch company over teff patent - MP3-Stereo

 ይህንን የባለቤትነት መብት ለማስመለስ በዓለም ዓቀፍ ፍርድ ቤት ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱን  የሳይንስና የቴክኖሎጅ ሚንስቴር ከሰሞኑ ገልጿል። ሚንስትር መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎችን የማማከር ሂደትና ለክሱ የሚረዱ ማስረጃዎችን አጠናቆ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዉክልና መስጠቱን አመልክቷል። 
የኢትዮጵያ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሚንስቴር እንደገለጸዉ ዓለም ዓቀፍ የጤናና የምግብ አዘገጃጀት በምህጻሩ /HPFI/ የተባለዉ  የኔዘርላንድ ኩባንያ ጤፍን ለአዉሮጳ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅና ምርምር ለማድረግ እንዲሁም ከጤፍ የሚገኘዉን ጥቅም ተጋሪ ለመሆን ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ተቋም ጋር ከ12 ዓመታት በፊት ውሱን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ ነበር። ይሁን እንጅ ኩባንያዉ ውሎ አድሮ ከስምምነት ሰነዱ ውጭ ጤፍን በባለቤትነት ማስመዝገብ በመጀመሩ ይህንን ድርጊት እንዲያቆም በኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ዉጤት ባለመገኘቱ ሀገሪቱ ኩባንያዉን በሕግ ለመጠየቅ መገደዷን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ይከናወናል ብለን የተወሰኑ እንቅስቃሴወችን ጀምረን ነበር።ነገር ግን ከዚያ «ሳይድ» የምናናግረዉ  ያን ያህል «ሪስፖንድ»የሚያደርግ  አካል ማግኜት ስላልቻልን ዶክመንቶቹን ሁሉ ጨርሰን አሁን ለጠቅላይ አቃቬ ህግ ፤ሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር የሚመራዉ«ናሽናል ቲም» አለ።የዉጭ ጉዳይ ፣የጠቅላይ አቃቬ ህግ ፣የግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት፣የኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት ፅ/ቤትና የብዝሃ-ህይወት ኢንሲቲቲዩት እነዚህ ያሉበት «ናሽናል ኮሚቴ»አለ።ያ ኮሚቴ ጥናቱን ጨርሶ ለጠቅላይ አቃቬ ህግ አስተላልፏል።»ካሉ በኋላ «ማናቸዉንም ኢንፎርሜሽኖች ለጠቅላይ አቃቬ ህግ በደብዳቤ አስረክበናል«ብለዋል።
በተደረገዉ  የስምምነት ሰነድ አማካኝነትም ለምርምርና በአዉሮፓ  ተጠቃሚዎች በሚያመች መልኩ  ምግብ አዘጋጅቶ እንዲያስተዋዉቅ  14 ኩንታል ጤፍ ኩባንያዉ ከኢትዮጵያ መውሰዱን ሚንስትሩ ይናገራሉ። ይህ ከሆነ ከጎርጎሮሳዊው 2007 ዓ,ም ወዲህ ግን «ኩባንያዉ በኪሳራ ምክንያት ተዘጋ» በሚል ውሉን የተፈራረሙት ሰዎች ራሳቸዉ ሌላ ኩባንያ በመመስረትና ውሉን ለአዲሱ ኩባንያ እንዲተላለፍ በማድረግ  የባለቤትነት መብቱን ሕጋዊ ለማስመሰል እየጣሩ መሆኑንም አብራርተዋል። በዚህ የተነሳም ሀገሪቱ በአዉሮጳ ገበያ ከጤፍ ታገኝ የነበረዉን ጥቅም ማስጠበቅ አልተቻለም።«ከዚህ ቀደም በተፈረመዉ ዉል ላይ የዚህ ጥቅም ተጋሪ እንድትሆን ለማድረግ አልተቻለም። ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመዉ ድርጅት የለም»ሲሉ ነዉ ያብራሩት።
ኩባንያዉ በኔዘርላንድ፣በጣሊያን፣በጀርመን፣በታላቋ ብሪታንያና በኦስትሪያ የጤፍ ዱቄትንና ከጤፍ የሚሰሩ ምግቦችን በተመለከተ የባላቤትነት መብት ያለዉ ሲሆን ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያዉያን ነጋዴዎች በአዉሮፓ ገበያ ከጤፍ የተሰሩ ምርቶችን እንዳያስገቡ ኩባንያዉ እየከለከለ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታት ከአራት ዓመት በፊትም በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር በተሰጠ ትዕዛዝና አዲስ አበባ በሚገኘዉ የኔዘርላንድ ኤምባሲ ትብብር አዉሮጳዉያን አማካሪዎችን በማስመጣት ጥናት በመደረጉ ጉዳዩ  በሕግ ቢታይ ሀገሪቱ መብቷን የምታስከብርና የምታሸንፍ መሆኗ ቢረጋገጥም እስካሁን ድረስ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ነዉ የገለፁት። ያም ቢሆን ኩባንያዉ ለመነጋገር ፈቃደኛ ባለመሆኑ  የረባ መልስ አልተገኘም ነዉ ያሉት።
የስምምነቱ ማዕቀፍ ከጤፍ የሚሰሩ ምግቦችን ማስተዋወቅና ምርምርን  መሠረት ያደረገ ስለነበር  ኩባንያዉ ባልተጠበቀ ሁኔታ የባለቤትነት መብት ማንሳቱ እና አሁን የተፈጠሩት ችግሮችን  ታሳቢ ያደረገ አልነበረም የሚሉት ሚንስትሩ ያም ሆኖ ግን  የኩባንያዉ ድርጊት ወንጀል መሆኑን ነዉ የተናገሩት።
ድርጅቱ ከአዉሮፓ ሃገራት በተጨማሪ በአሜሪካና በጃፓን ጤፍን በባለቤትነት ለማስመዝገብ  የተንቀሳቀሰ ቢሆንም የየሃገራቱ የአእምሯዊ መብት ጽሕፈት ቤቶች የኢትጵያ መሆኑን በመገንዘባቸዉ መከልከሉንም ገልፀዋል። በዚህ መንገድ  የአዉሮጳ ኅብረት የድርጅቱን የባለቤትነት ዕዉቅና መንፈግ ሲገባዉ ይህንን አለማድረጉ የሚያሳዝን ቢሆንም ይህንን በአሜሪካና በጃፓን ኩባንያዉ ባለቤትነት የተነፈገበትን ሕጋዊ ሁኔታ እንደማስረጃ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሚንስትሩ ጨምረዉ አመልክተዋል።

Bildergalerie Äthiopien Teff
ምስል DW/J. Jeffrey
Bildergalerie Äthiopien Teff
ምስል DW/J. Jeffrey
Landwirtschaft Äthiopien Dreschen von Hirse
ምስል Getty Images/AFP/S. Gemechu


ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሰ