1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥምቀት በዓል አከባበር በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ

ቅዳሜ፣ ጥር 11 2011

የተለያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስትያናት በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ የጥምቀትን በዓል በድምቀት አክብረዋል። የአራት አድባራት ታቦታት ከክብር ማደሪያቸው ቤተመቅደስ ግሪስሃይም ወደሚገኘው አዳራሽ አምርተዋል። ካህናት፣ የሰንበት ትምሕርት ቤት ተማሪዎች እና ምዕመናንም በቅዳሴ በማሕሌት እና በዝማሬ ምሥጋና አቅርበዋል

https://p.dw.com/p/3BqWG
Deutschland äthiopisches Epiphanie-Fest in Frankfurt am Main
ምስል DW/E. Fekade

ከዚህ ቀደም የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በዓሉን በጋራ አክብረዋል

ኢየሱስ ክርስቶስ በ 30 ዓመቱ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውሰው ጥምቀት በአገራችን ከ 2ሺህ ዓመት በላይ በጾም በቅዳሴ በምህላ በዝማሬ እና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ሥርዓት በብሔራዊ እና በአደባባይ ሲከበር የኖረ ታላቅ ዓውደ አመት ነው:: የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ዳራው በተጨማሪ በተለይም በገጠሩ የአገራችን ክፍል ኮበሌዎች እና ኮረዳዎች ታቦታት በክብር በሚያርፉባቸው አደባባዮች ከየመንደሩ ተሰባስበው "ሎሚ ጣልባት በደረቷ የጨዋልጅ ነች መሰረቷ " በሚሉ ጭፈራዎች እና ጨዋታዎች የወደፊት የትዳር አጋሮቻቸውን የሚያጩበት መልካም አጋጣሚ ተደርጎ ስለሚቆጠር አከባበሩን በአገራችን የበለጠ ደማቅ እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል:: በኢትዮጵያ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማንያን ዘንድ የየአብያተ ክርስትያናቱ ታቦተ ሕግ ከማደሪያው ቤተመቅደስ ወጥቶ በተከተረ ወራጅ ውሃ ዳር በሚዘጋጅለት ቦታ በክብር ካረፈ በኋላ በልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ ሥርዓት እና የዕምነቱ ተከታዮችን በማጥመቅ በልዩ ሁኔታ ሲከበር የኖረ አውደ ዓመት ነው::ይህ በዓል በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማም ዘንድሮ ግሪስ ሃይም ኧርነስት ቪስ ጎዳና በሚገኘው ሰፊ አዳራሽ ከወትሮው ደመቅ ባለ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እየተከበረ ይገኛል።

ከ 28 ዓመታት በኋላ ለሁለት ተከፋፍሎ የቆየው ሲኖዶስ በቅርቡ ዳግም መዋሃዱን ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ 4 አብያተ ክርስትያናት ማለትም የምሳካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ደብረ ፀሐይ ቅድስተ ማርያም እና ደብረ ኃይል ቅዱስ ዑራኤል ወቅዱስ ያሬድ አብያተ ክርስትያናት በህብረት ባዘጋጁት በዚህ ልዩ የበአል መስተንግዶ የካህናት የምዕመናን እና ከየአድባራቱ የመጡ የሰንት ትምህርት ቤት መዘምራን ቅዳሴ ምስጋና ዝማሬ እና ዕልልታ ለዝግጅቱ ተጨማሪ ውበት እና ድምቀትን እንደሰጠው ለማስተዋል ችለናል:: ከጀርመን የተለያዩ ከተሞች እና አጎራባች አገራት የመጡ አያሌ የእምነቱ ተከታዮችም የሥነ ሥርዓቱ ተካፋይ ሆነዋል:: የጀርመን እና አካባቢው ማለትም የስዊትዘርላንድ ኦስትሪያ ጀርመን እና ኔዘርላንድስ አገራት አገረ ስብከት ዋና አስተዳዳሪ እና ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዲዮናስዮስም በአሉን ምክንያት በማድረግ ለዕምነቱ ተከታዮች ብሎም ለመላው ኢትዮጵያውያን ሰላም እና ፍቅር ተመኝተው ከእርስ በእርስ ጥላቻ እና ግጭት እንዲርቁ መንፈሳዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል:: ብጹዕ ሊቀ ጳጳሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ፈለገ ዮርዳኖስ ወርዶ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበት ሃይማኖታዊ ተምሳሌት ሲያስረዱም ወንዙ ከመነሻው አንድ ሆኖ እንደሚፈስ መሃል ላይ ግን ለሁለት ከተከፈለ በኋላ መጨረሻ ላይ እንደገና እንደሚገናኝ በመግለጽ የሰው ልጅም በግብሩ ምክንያት አሕዛብ እና ሕዝብ ተብሎ ለሁለት ተከፍሎ ከቆየ በኋላ በጥምቀት አንድ ሊሆን ችሏል ብለዋል:: እናም በዓሉ የሰላም እና የአንድነት በዓል እንደመሆኑ መላው ሕዝባችን ከጥላቻ ከእርስ በእርስ ግጭት እና ከልዩነት ርቆ በፍቅር በአንድነት እና በመከባበር ሊኖር እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

Äthiopien Epiphanie-Fest in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የምሳካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተክርስትያን ዋና አስተዳዳሪ እንዲሁም የጀርመን እና አካባቢው አገራት አገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነወርቅ ውቤ በበኩላቸው የሰው ልጅ አዳም በፈጸመው ሃጢአት እና በተላለፈው ሕግ ምክንያት ከነበረበት ፈተና ተወልዶ ተጠምቆ እና ደሙን አፍሶ ነጻ የወጣበት በዓል መሆኑን በማስታወስ ጥምቀትን ስናከብር አቅመ ደካሞችን እና የተቸገሩ ወገኖችንም መርዳት እና ማስታወስ ይገባል ብለዋል::  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ለአገሪቱ አንድነት ሰላም እና እድገት ለብዙ ሺህ ዘመናት አያሌ አስተዋጽዖ ማድረጓን የጠቆሙት የሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ መጋቢ አዲስ አባ ስብሃት ለአብም አሁንም ተከፋፍሎ የቆየው ሲኖዶስ መዋሃዱ ይህንኑ በጎ አገልግሎቷን ይበልጥ እንድታጠናክር ይረዳታል ነው ያሉት:: የደብረ ፀሐይ ቅድስተ ማርያም ዋና አስተዳዳሪ አባ ሲራክም በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን ግጭት እና የሕዝቦች መፈናቀል በየተኛውም ዕምነት የማይደገፍ መሆኑን ገልጸው የማኅበረሰቡን ሥነምግባር በማነጽም ይሁን ሁሉም ሃይማኖቶች እና ሕዝቦች ተከባብረው የሚኖሩባትን አገር በመገንባት ረገድ ከዕምነት አባቶች እና ከመንግሥት ሃላፊዎች ብዙ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል:: የፍራንክፈርቱ የጥምቀት ኃይማኖታዊ ክብረ በዓል ሌላው አዘጋጅ የደብረ ኃይል ቅዱስ ዑራኤል ወቅዱስ ያሬድ ቤተክርስትያን ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ጠበብት ተክሌ ሲራክም ተከታዩን ስለ ሰላም እና ፍቅር አስፈላጊነት አጠር ያለ መንፈሳዊ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

Deutschland äthiopisches Epiphanie-Fest in Frankfurt am Main
ምስል DW/E. Fekade

የተለያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስትያናት በሕብረት እያከበሩት የሚገኘው የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በፍራንክፈርት ከተማ የኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳሆን የውጭ ዜጎችንም ትኩረት ለመሳብ ችሏል:: በዛሬው ዕለት በዓሉ በቅዳሴ በምስጋና እና በዝማሬ የተዘከረ ሲሆን በነገው ዕለት ደግሞ እንደ አውሮፓውያኑ የሰዓት አቆጣጠር ከጧቱ 10 ሰዓት ጀመሮ ሃይማኖታዊው የጥምቀት ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ ታቦተ ህጉን ወደ ክብር ማደሪያው መቅደስ የሽኝት ፕሮግራም በማካሄድ ዝግጅቱ እንደሚጠናቀቅ ከመርሃ ግብሩ ለመረዳት ችለናል። 
እንዳልካቸው ፈቃደ
እሸቴ በቀለ