1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍርድ ቤት ዉሳኔ እና የዳዳብ መጠለያ ዕጣ

ዓርብ፣ የካቲት 3 2009

የኬንያ ፍርድ ቤት መንግሥት በትልቅነቱ የሚታወቀዉን የዳዳብ የስደተኛ መጠለያ እንዳይዘጋ ወስኗል። መንግሥት መጠለያዉን የሚዘጋዉ ለሀገሪቱ ጸጥታ ቅድሚያ በመስጠት መሆኑን በመግለፅ ይግባኝ ብሏል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች፤ የኬንያዉ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና አቻቸዉ ኩቱኦ ቻ ሸሪያ የመንግሥት ዉሳኔ እንዳይፀና ተሟግተዋል።

https://p.dw.com/p/2XHa0
Kenia Das Flüchtlingslager Dadaab
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

Kenya court orderd Dadaap to stay open - MP3-Stereo

«በዚህ ወሳኝ በሆነዉ ብሔራዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ የተላለፈዉን ዉሳኔ እየገመገምነዉ ነዉ። እናም እንደ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እናከብራለን። ይህን ዉሳኔ በተመለከተም በተቻለ ፍጥነት መንግሥት ይግባኝ እንደሚል መግለፅ እንፈልጋለን።»
የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ እንደተሰማ የኬንያ መንግሥት ቃል አቀባይ ኤሪክ ኪራቲ ነበሩ ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ይህን የተናገሩት። የኬንያ ፍርድ ቤት መንግሥት ሊዘጋዉ የነበረዉ ከ200 ሺህ የሚበልጡ የሶማሊያ ተሰዳጆች የተጠለሉበትን ዳዳብ የተባለዉን በግዛቱ የሚገኝ የስደተኞች ጣቢያ እንዳይዘጋ ወስኗል። ዳኛ ጆን ማቲቮ የኬንያ የሀገር ዉስጥ ደህንነት ሚኒስትር ዳዳብ የስደኞች መጠለያን ለመዝጋት በመወሰን ስልጣናቸዉን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል ነዉ ያሉት። እሳቸዉም ሆኑ ሌሎች ባለስልጣናት ለኃላፊነታቸዉ የገቡትን ቃል በሚቃረን መልኩ የሕግን የበላይነት በመጣስ ከገደብ በላይ ስልጣናቸዉን ተጠቅመዋል ሲሉም አክለዋል። ዳኛዉ የመንግሥት ትዕዛዝ ከኬንያ ሕግም ሆነ ከዓለም አቀፍ ህጎች በተቃራኒ የሚሄድ እና አድሎ የሚያደርግ እንደሆነም አብራርተዋል። 
ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ወደ 256 ሺህ ሰዎችን ያስጠለለ፤ ሲሆን እዚያ ከሚገኙት አብዛኞቹ የሶማሊያ ዜጎች መሆናቸዉ ይነገራል። የኬንያ መንግሥት መጠለያ ጣቢያዉን ለመዝጋት ከወሰነ ጀምሮ የመብት ተሟጋቾች ተቃዉሞ ቢያሰሙም ከሶማሊያ የተሰደዱትን ወደ ሀገራቸዉ ለመመለስ እንደሚፈልግ ሲገልጽ ቆይቷል። ዳኛ ጆን ማቲቮም ተሰዳጆቹን በጅምላ ያለፍላጎታቸዉ ወደ ሀገራቸዉ ድንበር የማሻገሩ እቅድም የተመድ በጎርጎርዮሳዊዉ 1951ዓ,ም ያጸደቀዉን ድንጋጌ እንደሚጥስ ነዉ አፅንኦት የሰጡት። በዚህ ምክንያትም የመንግሥት ዉሳኔ ዜሮ እና የታገደ መሆኑን ይፋ አድርገዋል። 
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪቃ ኃላፊ ማቶኒ ዋንዬኪ ታሪካዊ ያሉትን የዳኛዉን ዉሳኔ አወድሰዋል። ዉሳኔዉ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሊጋለጡ ለሚችሉት ሩብ ሚሊየን ለሚሆኑት የሶማሊያ ተሰዳጆችም ዕለቱ ታሪካዊ መሆኑንም ገልጸዋል። ኬንያ ወደ ሶማሊያ ወታደሮቿን ካዘመተችበት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም ጀምሮ በፅንፈኛዉ ታጣቂ ቡድን አሸባብ ተደጋጋሚ ጥቃት ደርሶባታል። መንግሥት ዳዳብ የሚገኙ የሶማሊያ ፅንፈኞች ጥቃቱን ያቀናብራሉ በማለት መጠለያ ጣቢያዉ የሀገሪቱ የደህንነት ስጋት እንደሆነ ይናገራል። በዚህ ምክንያትም ባለፈዉ ታኅሳስ መጀመሪያ አካባቢ ነበር መጠለያዉን ለመዝጋት አቅዶ የነበረዉ። የተመድ በጠየቀዉ መሠረት እና ወደ ሶማሊያ በግድ እንዲመለሱ የተደረጉት ወገኖች በሚያሰሙት ተደጋጋሚ ክስ ምክንያት እስከ ፊታችን ግንቦት ወር እንዲቆይ ተወሰነ። ቀደም ሲል በዚህ መጠለያ ስፍራ 320ሺህ ተሰዳጆች ተጠልለዉ ነበር። የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንደሚለዉ ቁጥሩ የቀነሰዉ በፍላጎታቸዉ ወደ ሀገራቸዉ የተመለሱ እና ሰሜን ኬንያ ዉስጥ ወደ ሚገኘው ካኩማ የስደተኞች መጠለያ ገሚሱ በመሄዳቸዉ ነዉ። ባለፈዉ ዓመት ግንቦት ወር የኬንያ መንግሥት እጅግ በርካታ ተሰዳጆችን አስጠግቶ የቆየዉን ግዙፉን የዳዳብ መጠለያ ለመዝጋት መወሰኑን ይፋ ሲያደርግ የተመድን፣ እና ምዕራባዉያን የኬንያ መንግሥት አጋሮችን አደናግጦ ነበር። የመንግሥት ቃል አቀባይ ኤሪክ ኪራቲ ይህን ቢያነሱም መንግሥት ለዚህ ዉሳኔ የበቃበት ምክንያት ቅድሚያ ስለሚሰጠዉ የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ እንዲቀለበስ እንደሚጠይቅ በአፅንኦት ገልጸዋል።
«የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ መዘጋት በየጊዜዉ በጣም በርካታ ከሆኑ ባለድርሻ አካላት ልዩ ልዩ አስተያየት ሲያመጣ ቆይቷል። ነገር ግን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ይህ ዉሳኔ እንዲመጣ ያስገደዱት ዉሳኔዎች፤ ሁኔታዎች፣ እና ይዞታዎች አሁንም ተመሳሳይ ናቸዉ፤ እናም ምንም የተለወጠ ነገር የለም። እናም ተቀዳሚ ኃላፊነቱ የኬንያዎች ጉዳይ እንደሆነ መንግሥት የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ መነሳት እንደሚኖርበት ይሰማናል ለዚህም ነዉ ይግባኝ የምንለዉ።» 
የኬንያ መንግሥት በይግባኝ ጥያቄዉ እንደሚገፋበት ቢገልፅም ለጊዜዉ ግን የዳኛዉ ዉሳኔ በዳዳብ ለሚገኙት ተሰዳጆች እፎይታ አስገኝቷል። የመብት ተሟጋቾች የኬንያ መንግሥት ለተለያዩ አደጋዎች የተጋለጡት ስደተኞች ወደየሀገራቸዉ ከመመለስ ይልቅ አማራጭ እንዲፈልግም እየጠየቁ ነዉ።  

Flüchtinge in Dadaab Kenia
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa
Afrika Kenya Dagahaley Camp
ምስል picture-alliance/AP Photo/R. Blackwell

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ