1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍትኅ ሰቆቃ፤ ብሔር ብሔረሰቦችና የህዳሴው ግድብ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 5 2011

የሰው ልጅ ይህን ያኽል መከራ እና ሰቆቃ መሸከም ይችላል ወይ ያሰኛል ዘገቢ ፊልሙን ለተመለከተ። እጅግ የሚሰቀጥጡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚተርከው እና የሚያሳየው ዘገቢ ፊልም ለእይት ከቀረበ በኋላ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

https://p.dw.com/p/3A46w
Waage der Göttin Justitia
ምስል picture-alliance/dpa

«የፍትኅ ሰቆቃ» ዘጋቢ ፊልም ለእይታ ከበቃበት ምሽት ጀምሮ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ ቀጥሏል

ዘጋቢ ፊልም፤ የ1 ሰአት ከ16 ደቂቃ ከ52 ሰከንዶች ርዝመት አለው። ተጀምሮ አስኪጠናቀቅ ድረስ ለአእምሮ የሚከብዱ፤ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ የግፍ ድርጊቶች ግፉ እንደተፈጸመባቸው በሚገልጡ ሰዎች አንደበት እየተነገረ በምስል ታጅቦ ታይቷል።  በድብደባ ብዛት እግራቸው የተቆረጡ፤ መቆም ተስኗቸው እግሮቻቸው የሚንቀጠቀጡ፤ የዘር ሐረጋቸው እንዳይቀጥል ሐፍረተ ሥጋቸው የተቀጠቀጡ፤ እጅና እግራቸው የፊጥኝ ታስሮ እንጨቶችና አግዳሚዎች ላይ ተዘርግተው ውስጥ እግሮቻቸው የተገረፉ፤ ተዳክመው በተዝለፈለፉበት በአፍንጫቸው ጭራሮ እየገባ እንዲነቁ የተደረጉ፤ በአጠቃላይ ሰቅጣጭ ሰቆቃዎች እንደደረሰባቸው ሲገልጡ ይታይበታል ዘጋቢ ፊልሙ። የፍትኅ ሰቆቃ ለእይታ ከበቃበት ምሽት ጀምሮ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ ቀጥሏል።

የፍትኅ ሰቆቃ

ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው ረቡዕ ዕለት በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፉ፦ «የትናንትናው የፍትህ ሰቆቃ ዘጋቢ ፊልም የጌታቸው ሺፈራው የሰቆቃ ድምጾች መጽሐፍ ነው። ጌታቸው በጽሑፍ ያቀረበውን EBC [የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን] በዘጋቢ ፊልም ለማቅረብ መድፈሩ የሚበረታታ ነው» ብሏል።  ሙሉቀን ከጽሑፉ ጋር «የሰቆቃ ድምጾች» የተሰኘው መጽሐፍ የፊት እና የኋላ ገጽ ሽፋንንም አያይዟል።

ደራሲ እና ገጣሚ ዮሐንስ ሞላ በፌስቡክ ጽሑፉ «ባለፈው፣ወንጀለኛውን ሁሉ እንሰር ካልን፣ አንድ ከተማም አይበቃንም።ዛሬ ደግሞ፥ግፍ ሰርቶ መደበቅ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልም።ምናለ ተረቱን እንኳን ለሕዝቡ ቢተዉት?! "እነሱ" የሚባል ነገር የለም። ኢህአዴግ ነው ሁሉንም ያደረገው። ይቅር በሉን፣ "አይደገምም" ማለት አንድ ነገር ነው። "እነሱ/እኛ" ማለት ግን [ትርጉም አይሰጥም]!» ብሏል።

ጦማሪ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ የትዊተር ገጹ ላይ  በእንግሊዝኛ ባቀረበው ጽሑፉ ዘጋቢ ፊልሞች መሠራታቸው ግድ መኾኑን ገልጦ መገናኛ ብዙኃን ግን ሊጠነቀቁ የሚገባቸውን ነጥብ ጠቅሷል። የበፍቃዱ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፦ «ዘጋቢ ፊልሞች እና ተመሳሳይ ዘገባዎች ሊሠሩ ግድ ነው የሚል እምነት አለኝ። ኾኖም መገናኛ ብዙኃን ሊታቀቡ የሚገባቸው ብቸኛው ጉዳይ ጥፋተኝነትህ እስካልተረጋገጠ ድረስ ጥፋተኛ አይደለህም የሚለውን መርኃዊ መብት አለማክበራቸው ላይ ነው» ብሏል።

የበፍቃዱን የትዊተር ጽሑፍ ወደራሱ ገጽ አምጥቶ በእንግሊዝኛ አስተያየት የሰጠው ሌላኛው ጦማሪ ዘላለም ክብረት በበኩሉ፦ «ማንም አዕምሮው ጤነኛ የኾነ ሰው በአጠቃላይ በዘጋቢ ፊልም ጽንሰ ሐሳብ ላይ ሊበሳጭ አይገባም» ሲል ይንደረደራል። «ጥያቄ የሚያጭረው» ሲልም ይቀጥላል ዘላለም። «የቀረበበት ጊዜ፣ ውንጀላዊ ድምጸቱ፣ ብሎም አሁንም ድረስ ከዘለቀው ሥርዓት ይልቅ የተወሰኑ ግለሰቦች በመወንጀል የሕዝብ አመለካከትን ለመፍጠር መነሳሳቱ ነው» ሲል ጽሑፍን ደምድሟል።

Burundi, Symbolbild Folter
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

በDW የፌስቡክ ገጽ ላይ ከተሰጡ በርካታ አስተያየቶች መካከል፦ ዘ ዴ ታም በሚል የፌስቡክ ምኅጻር የቀረበ ጽሑፍ ስለዘጋቢ ፊልሙ አስፈላጊነት እንዲህ ያብራራል።  «የዚህ ዶክመንተሪ ዋነኛ አስፈላጊነት ያለፈውን ስርአት እኩይ ተግባር ማሳየት ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ቁም ነገሩ አሁን ላይ ያሉ የለውጡ አጋፋሪዎች እና በሥልጣን ላይ የሚገኙ እንዲሁም ነገ ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚፎካከሩ ፓርቲዎችም ሆኑ ግለሰቦች እነሱም ይህንን -ሰብአዊ ድርጊት ላለመድገም ትምህርት መውሰድ መቻላቸው ነው።»

ኤሊያስ ኤዞ በበኩሉ፦ «ሰብዓዊ መብት ጥሰት በአሁኑ ሰዓት ቆሟል ለማለት አይቻልም፡፡ ከድብቅ ወደ አደባባይ ወጥተዋል። በአደባባይ ጥሰት መንግሥት መች ተከላከለና ዶክመንተሪ ያሠራል? ተመሳሳይ ድርጊት እየተፈፀመ ነው። የፖለቲካ ገም ጫወታ አያወጣም» ሲል ፌስቡክ ላይ ጽፏል።

አብደረስ ቀውሲሳት፦ «በመሠረቱ አሰቃቂውን ግፍ ለሕዝብ ማቅረብ በምንም ዓይነት የፍትህ ሥርዓቱን ሊያዛባ አይችልም» ሲል ጽሑፉን ይጀምራል። ለጠቅ አድርጎም፦ «ምክንያቱም ወንጀሉ የተፈፀመው በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ነው፣ ወንጀሉም የተጋለጠው በዚሁ በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ሲሆን ጉዳዩን የሚዳኘው የፍትህ ሥርዓትም በዚሁ በኢህአዴግ አገዛዝ ሥርዓት ነው፣ ታዲያ ፍትህ እንዴት ሊዛባ ይችላልሲል አጠይቋል።

«በርግጥ በጣም የሚዘገንን እና አረመኔያዊ ድርጊት ነው ይሁን እንጅ በኔ እይታ ይህ ዘጋቢ ፊልም መታየቱ በህዝቦች መካከል በተለይም የትግራይ ተዎላጆችን ከሌሎች ብሄሮች ጋር ከማጣላት የዘለለ ፋይዳ ይኖረዋል ብየ አላሥብም» ያለው ደግሞ ኃዩ መንግሥቱ ነው።

ችሎቴ ቡልቲ ደግሞ ቀጣዩን ጽፏል። «በምንም ታዓምር የፍትህ ስርዓት አያጎድልም። ምክንያቱም ለመጭው ማስተማሪያ ነው፤ ወይንም ድርጊቱ ተፈጽሟል ወይም አልተፈጸመሞ እያልን ከምንምታታ በአንደበታቸው ምሰክርነታቸውን ገልፀዋል የድርጊቱ ባለቤቶች።»

አፍሪካን ሆርን ኢቲ የተሰኘው የትዊተር ገጽ በእንግሊዝኛ ያቀረበው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል። «መጠነ-ሰፊ የወያኔ ኢፍትኃዊ በደል የደረሰባቸው ያሳለፉትን መግለጥ ያለባቸው ሕግ ፊት ነው እንጂ፤ ከሰቆቃው በሕይወት የተረፉት ወደቤታቸው ሲመለሱ ዳግም የቀን ቅዠት በሚቀሰቀስባቸው ያለፉበትን ዳግም እንዲያስታውሱት በሚያደርግ የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልም አይደለም። በዚያ ውስጥ ፍትኅ የት ነች ሲል ጠይቋል።

ምትኩ ጋዲሳ፦ «መንግስት እንደዚ አይነት ፊልሞችን ማሳየት ሕዝቡን ማዳንና ወደፊት እንዳይደረግ የሚያስጠነቅቅ ጭምር ነው። ሕዝብ ድርጊቱ እንደሚፈፀም በፊትም ያውቃል ይህንን ማመን ደግሞ ትልቅነት ነው አስተማሪ ዘጋቢ ፊልም ነው» ሲል ሚኪያስ ሰብስቤ፦  «የዶክመንተሪውን አቀራረብ መተቸት አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ለዓመታት ለከፋ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ስቃይ የተዳረጉትን ማንጓጠጥ የለየለት ኢ-ሰብዓዊነት ነው» ብሏል።

በጥያቄ በተጠናቀቀው የከበቡሽ የትዊተር መልእክት ወደ ቀጣዩ ርእሰ-ጉዳይ እንሻገር። እንዲህ ስትል ጠይቃለች ከበቡሽ፦ «ተለውጫለው ያለው መንግስትስ ወንጀሎኞቹን ለፍርድ ከማቅረብ ባለፈ ለተጎዱትና ሕይወታቸው ላለፈው ወገኖች ምን ማድረግ ያስባል?»

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

በቀሩን ጥቂት ደቂቃዎች፦ ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ስለተከበረው «የብሔር ብሔረሰቦች ቀን» እንዲሁም የህዳሴው ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ስላወሳው የፓናል ውይይት የተሰጡ አስተያየቶችን እናቅርብላችሁ።

ብሔር ብሔረሰቦች

ባሳለፍነው ሳምንት ከቡና ማፍላት ስነ ስርዓት አንስቶ የተለያዩ አልባሳት በማሳየት እና ጭፈራዎችን በማቅረብ እስከ ሳምንቱ መገባደጃ ድረስ ስለተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ከተሰጡ አስተያየቶች ቀጣዮቹ ይገኙበታል።

ሚኪያስ ትዊተር ላይ ቀጣዩን ጽፏል። «ጭፈራ ብቻ! አንዱን ገዢ ሌላውን ተገዢ፣ አንዱን ነባር ሌላውን መጤ ... አይነት ትርክት ቀን ተሌት እየፈጠሩ፣ ምንም መንስኤውም ሆነ ውጤቱ የማይታወቅ ጠብ እያበሰሉ በዓል ማክበር። ወሬ!» ብሏል።

ሚኪያስ ከትዊተር ጽሑፉ ጋር የተለያዩ ፎቶግራፎች ያሉበት የቢቢሲ ድረ-ገጽ ጽሑፍ አያይዟል። የተለያዩ ቀለማት ያላቸው የብሔር ብሔረሰቦች አልባሳትን ያደረጉ ሰዎች ከበሮ ሲደልቁ፣ ሲጨፍሩ፣ ጥሩምባ ሲነፉ፤  ጊሌ ታጥቀው ብትር ሲወዘውዙ፣ ወዘተ ይታይበታል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ የትዊተር ገጽ ላይ ቀጣዩ ጽሑፍ ሰፍሯል። «ብሔር ብሔረሰቦች ብለን እዚህ እንጨፍራለን። በኋላ ሲገናኙ መገዳደል። ችግር እንዳለ ሁላችንም ማመን አለብን። ካመንን በኋላ እንዴት እንፈታዋለን ብሎ ማሰብ ነው። ሃቀኛ ሰዎች ከሆነን» ሲል ይነበባል።

የህዳሴ ግድብ

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከአራት ዓመታት በኋላ በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ«2022 ይጠናቀቃል» መባሉን በተመለከተ ከተሰጡ አስተያየቶች ጥቂቶችን እናሰማችሁ።  ግድቡ ያለበትን ደረጃ የሚቃኝ ውይይት ሐሙስ እለት ከተከናወነ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አብዛኞቹ በአራት ዓመት ይጠናቀቃል መባሉ ጥርጣሬ ያጫረባቸው ናቸው። መልካሙ መአዛ ትዊተር ገጹ ላይ፦ «የህዳሴው ግድብ በአራት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል ሲል ይጠይቃል። «እውነት ከሆነ ጥሩ ዜና ነው። ከእንግዲህ በተቻለ መጠን ህዝቡን መዋጮ ባትጠይቁት ጥሩ ነው» ሲል ጽፏል።

በአጭሩ፦ «አሁንም የህዳሴው ግድብ ያስጨንቀኛል» ሲል የጻፈው የማነ ኪዱ ነው፤ ትዊተር ላይ።

በምጸታዊ ጽሑፎቹ የሚታወቀው አበበ ቶላ ፈይሳ፦ «ባለፈው ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩግድቡ በዚህ አያያዙ 10 ዓመቱም አይጠናቀቅምብለውን ነበር እሁን አያያዙ ተሻሽሏል የሚያልቅበት ዓመትም ተሻሽሏል» ሲል ጽፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ