1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሬዚዳንት ባይደን ዓመታዊ ንግግር

ዓርብ፣ የካቲት 29 2016

የዩናይትድስቴትስ ጦር በጋዛ ጊዜያዊ ወደብ ሊገነባ መሆኑን ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን አስታወቁ። ፕሬዚደንት ባይደን፣ ትናንት ምሽት በሃገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተገኝተው ለታችኛውና ላይኛው ምክር ቤት ባደረጉት ዓመታዊ ንግግራቸው፣የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/ኔቶን/ የበለጠ ጠንካራ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4dJpA
የፕሬዚዳንት ባይደን ዓመታዊ ንግግር
የፕሬዚዳንት ባይደን ዓመታዊ ንግግርምስል CHIP SOMODEVILLA/AFP/Getty Images

የፕሬዚዳንት ባይደን ዓመታዊ ንግግር

የባይደን ዓመታዊ ንግግር

የዩናይትድስቴትስ ጦር በጋዛ ጊዜያዊ ወደብ ሊገነባ መሆኑን ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን አስታወቁ።  ፕሬዚደንት ባይደን፣  ትናንት ምሽት በሃገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተገኝተው ለታችኛውና ላይኛው ምክር ቤት ባደረጉት ዓመታዊ ንግግራቸው፣የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/ኔቶን/ የበለጠ ጠንካራ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።  
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት 

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በተለምዶ በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዓመታዊ ንግግር ወይንም ስቴት ኦቭ ዘ ዩኒየን ወደ ኇላ የሚነሳ ጉዳይ ነው።ይሁንና ባይደን የሥልጣን ዘመናቸው ዓለም አቀፍ ውጥረት የሰፈነበት እንደመሆኑ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፕሬዚዳንት እስከመባል አድርሷቸዋል። በመካከለኛው ምስራቅ እና በአውሮፓ የሚካሄዱ ጦርነቶችን ለማስቆም ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ጆሴፍ ባይደን፣ ባለፉት አምስት ወራት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት ለእስራኤልና ፍልስጤማውያን ብቻ ሳይሆን በዚህ በአሜሪካም ብዙዎችን ያሳዘነ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በጦርነቱ ከሠላሳ ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጠቀሱት ፕሬዝደንቱ ከማንም በላይ ሴቶችና ህፃናት ክፉኛ መጉዳታቸውን አመልክተዋል። ባይደን ተጨማሪ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ የመግባት አስፈላጊነትን ሲናገሩ፣በጋዛ ምግብ፣ ውሃና መድኃኒት ወደ ወደብ እንዲገባ የሚያስችል ጊዜያዊ የባህር በር የዩናይትድስቴትስ ጦር ሊገነባ መሆኑን አስታውቀዋል።ዕርዳታውን ከባህር አውርዶ የባህር ዳር ዳርቻ ላይ የሚወስድ መንገድም ይመቻቻል።

የኔቶ መጠናከርና የስዊዲን አዲስ አባልነት 

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/ኔቶ/ን የበለጠ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው የጠቆሙት ጆሴፍ ባይደን፣ኔቶን በይፋ የተቀላቀለችውንና በኮንግረሱ አድራሻ የተገኙትን የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር እንኳን ደህና መጡ በማለት ተቀብለዋቸዋል። " አሜሪካ የኔቶ መሥራች ሃገር ናት፤ ጦርነትን ለመከላከልና ሰላም ለማስጠበቅ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመሰረተ የዲሞክራቲክ አገሮች ወታደራዊ ጥምረት ነው።ዛሬ ኔቶን ከምንጊዜውም በላይ ጠንካራ እያደረግነው ነው።ፊንላንድን ባለፈው ዓመት ወደ ጥምረቱ ተቀብለናታል፣ ዛሬ ጠዋት ደግሞ ስዊዲን ተቀላቅላለች።

ዩክሬንና ሩሲያ

በሩሲያና ዩክሬን መኻል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አስመልክቶ ፕሬዝደንቱ ሲናገሩ፣ዩክሬናውያን የሚፈልጉትን የጦር መሳሪያ በመስጠት ቭላዲሚር ፑቲንን ለማስቆም ወደ ኋላ እንደማይሉ በድጋሚ አረጋግጠዋል። "ለረጅም ጊዜ የማውቀው ፕሬዚዳንት ባይደን ያለኝ መልዕክት ቀላል ነው፤ ወደ ኋላ አንልም።" ባይደን በቀጣዩ ምርጫ ተፎካካሪያቸው እንደሚሆኑ የሚጠበቁት፣የቀድሞውን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን በስም ሳይጠቅሱ፣ ለሩሲያው ፕሬዝደንት  ይታዘዛሉ ሲሉ ወቀሰዋቸዋል።

የፕሬዚዳንት ባይደን ዓመታዊ ንግግር
የፕሬዚዳንት ባይደን ዓመታዊ ንግግርምስል ANDREW CABALLERO-REYNOLDS/AFP

የድንበር ደኅንነት ሕግ

ሪፐብሊካኖች የሁለትዮሽ የድንበር ደህንነት  ህግን አይደግፉም በማለት የነቀፉት ፕሬዚዳንቱ፣የፍልሰተኞች ረቂቅ ሕግን እንዲያጸድቁላቸው ጥሪ አቅርበዋል። በድንበር አቋርጠው ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ፍልሰተኞችን በተመለከተ የተለሳለሱ ናቸው ተብለው የሚወቀሱት ባይደን፣  ረቂቅ ሕጉ በድንበር አከባቢ ስርአት እንዲሰፍን የሚረዳ መሆኑን አስታውቀዋል።  ባይደን፣በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በተለይ መኻከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የተሰራውንና የተገኘውን ዉጤት በማንሳት፣በነጩ ቤተ መንግስት ለሁለተኛ ስልጣን ዘመን ለመወዳደር በተዘጋጁበት በአሁኑ ወቅት መራጮችን ለማሳመን የሚያስችላቸው ጠንካራ ንግግር አድርገዋል። ፕሬዚዳንቱ በግብርና በተዋልዶ መብቶች ላይ ያላቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል። ከፕሬዚዳንቱ ንግግር አስቀድሞ፣ ተቃዋሚዎ ሰልፈኞች፣በጋዛ የተኩስ አቁም ጥሪ ለማሰማት ከነጩ ቤተመንግስት ውጪ ተሰብስበው ነበር።

የሪፐብሊካኑ ምላሽ

በሪፐብሊካኑ በኩል ለፕሬዚደንቱ ንግግር ምላሽ የሰጡት የአላባማ ግዛት ሲናተር ካቲ ብሪት በበኩላቸው፣ባይደን የአሜሪካ ቤተሰቦች የሚያጋጥማቸው ጉዳዮችን እንደማይረዱ በመግለጽ ተችተዋል። "የአሜሪካ የስኬት ዕልም ለብዙ ቤተሰቦች ወደ ቅዠትነት ተለውጧል። እውነተኛው የህብረታችን ያልተለወጠ ሁኔታ፣የሚጀምረውና የሚያበቃው በዚህ ነው።"  በመካከለኛው ምስራቅ አሜሪካውያን ጥቃት ላይ ናቸው ያሉት ሴናተር ብሪት፣ፕሬዚዳንት ባይደን ትክክለኛ አመራር እየሰጡ አለመሆናቸውን አስርድተዋል። ወጣቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ለወደፊቱ ግን ተስፋ እንዳላቸው ነው በዚሁ ንግግራቸው ያመለከቱት። አሜሪካ አሁን በአስቸጋሪ ሁኔታ  ብትገኝም ወደፊት የተሻለ ጊዜ ይመጣል በማለት።

 

ታሪኩ ኃይሉ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ