1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሬዝዳንት የኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝትና የአቶ አብዲ መሀሙድ ዑመር ንግግር

ዓርብ፣ ሐምሌ 6 2010

በዚህ ሳምንት አበይት ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መሥተዳር አቶ አብዲ ሙሀመድ ዑመር ንግግር እና ደብረ ማርቆስ ዉስጥ የተከሰተዉ ተቃውሞ ይገኙበታል።

https://p.dw.com/p/31QOM
Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት:- የፕሬዝዳንት የኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝትና የአቶ አብዲ መሀሙድ ዑመር ንግግር

ሲጠበቅ የነበረው የኤርትራ ፕሬዝዳንት የኢያስ አፈወርቂ የአዲስ አበባ ጉብኝት ዛሬ ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገፃቸው እንዳሰፈሩት የ72 አመቱ ኢሳያስ አፈወርቂ በጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በቀረበላቸው ግብዣ መሠረት ለሶስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ነገ ኢትዮጵያ ይገባሉ። አቶ ፍጹም የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት እና ግንኙነት እንደሚያጠናክር እምነታቸውን ገልጸዋል።  አብይ እና ኢሳያስ በዕለተ እሁድ በሚሊኒየም አዳራሽ ንግግር እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን 25,000 ሰዎች መርኃ-ግብሩን ይታደማሉ ተብሏል። ማሕሙድ አህመድ፤ ዓሊ ቢራ፤ ንዋይ ደበበ፤ ፀጋዬ እሸቱ፤ አረጋኸኝ ወራሽ፤ ሀጫሉ ሁንዴሳ፤ አብርሐም ገ/መድህን፤ ታደለ ገመቹ፤ ቀመር የሱፍ፤ ጌታቸው ሀይለማርያምን የመሳሰሉ ድምፃውያን ሥራቸውን ያቀርባሉ ተብሏል። አዲስ አበባ ስታዲዮም አጠገብ የሚገኘው እና ለበርካታ አመታት ተዘግቶ የቆየው የኤርትራ ኤምባሲ እድሳት እየተደረገለት መሆኑን የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ሲዘዋወሩ ታይተዋል።የፕሬዝደንት ኢሳያስ ጉብኝ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘንድ የተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮችን እየመዘዘ መወያያ ሆኖ ይታያል። 

ከዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው አቤል ዋበላ "ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ የት ነው ያለው? የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ የመረጠው ዝምታ አልገባኝም፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለዚህ እልባት ሳያበጁ የኢትዮጵያን ምድር አይረግጡም ብዬ ተስፋ አደርጋለኹ" የሚል አስተያየት በፌስ ቡክ ገፁ አስፍሯል። ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ የተቃዋሚ ፖለቲከኛው የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ወንድም እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባልደረባ ነበሩ። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የሚያበሩት ተዋጊ የጦር አውሮፕላን ኤርትራ ግዛት ውስጥ ወድቆ ከተማረኩ በኋላ ያሉበት ሥፍራ በግልፅ አይታወቅም። አቤል እንደተመኘው የኤርትራ መንግሥት የጦር አውሮፕላን አብራሪው ስላሉበት ሁኔታ ለኢትዮጵያ መረጃ ስለመስጠቱም የተሰማ ነገር የለም። 

Issaias Afewerki, Präsident von Eritrea
ምስል picture-alliance/dpa

አማኑኤል ተስፋዬ በትዊተር "አምባገነኑ ኢሳያስ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው። መቼም ከዚህ መንግሥት፤ ማንም ሞቅ አድርገን እንድን ቀበላቸው ጠይቆ በራሱ መቀለጃ አይሆንም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በአብይ ባቡር ላይ በመሳፈር ፤ ያለፈ ጥፋታቸውን ለመፋቅ ከሚሞክሩት ከአብዲ ኢሌ (አብዲ መሐመድ ዑመርን ማለታቸዉ) የተለዩ አይደሉም" የሚል አስተያየት አለው። 

የኤርትራ መድሕን ግንባር ዜናውን በዶይቼ ቬለ የፌስቡክ ገፅ ካጋራነው በኋላ "ኢሳያስ ሥልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ ሰላም እና መረጋጋት የለም። በመጀመሪያ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር መታረቅ አለባቸው" የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ኢብን አሕመድ ዘ-አገምጃይ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው "በዶ/ር አብይ አቀባበል ወቅት ያየነው በጣም ደስ የሚል በፍቅር ና በስነ-ስርዓት የታጀበው የኤርትራውያን አቀባበል እንደግመዋለን እንጂ የበለጠ ማድረግ አንችልም። ምክንያቱም ከኤርትራውያን ጋር በፍቅር አቻ መሆን እንጂ መብለጥ የሚቻል አይመስልም" ሲሉ ፅፈዋል። 

አብዱረሕማን አሕመዲን በበኩላቸው በኢሳያስ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ የገባቸው ይመስላል። በግል የፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሯት አጠር ያለች ፅሁፍ "የዶ/ር ዓብይ የሰላምና የፍቅር መንገድ ተስማምቶስኛል። ግን.... ግን..... ሊስተዋል የሚገባው ነገር አለ። የሻዕብያ ባህሪ ሲታይ ኢህአፓን ሸውዷል፣ ወያኔን ደጋግሞ ሸውዷል፣ ኢህአዴግን ሸውዷል..... መለስን ሸውዷል። አሁን ደግሞ ዐብይን ላለማታለሉ ምን ዋስትና አለ? አንዳንዶች በሂደት የማይለወጥ ነገር ስለሌለ ኢሳያስም ይለወጣል ትሉኛላችሁ። እኔ ይህንን አምኖ ለመቀበል ይከብደኛል። ለዘመናት አብሮት ከኖረው ባህሪ በአንድ ጀንበር ፣ በስተርጅና ይለውጣል ብየ ለመቀበል የሆኑ ነገሮችን ማየት እፈልጋለሁ" ብለዋል። 

President Isaias Afwerki &  Prime Minister Abiy Ahmed in Asmera
ምስል Yemane G. Meskel

ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መሥተዳድር አቶ አብዲ መሀሙድ ዑመር የሰጡት አስተያየት ነበር። ርዕሰ-መስተዳድሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ ባለፉት 100 ቀናት ስኬታማ ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸው ድጋፋቸውን ቸረዋቸዋል። አወዛጋቢው ጉዳይ ግን ስለ ቀድሞው የኢትዮጵያ የስለላ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ የተናገሯቸው ጉዳዮች ሆነዋል። አቶ አብዲ መሀሙድ ዑመር ይኸን አስተያየት የሰጡበት ምክንያት በግልፅ ባይታወቅም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች የየራሳቸውን ትንታኔዎች አቅርበዋል። ጀማል ዲሬ ኻሊፍ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መሥተዳድር አወዛጋቢውን አስተያየት የሰጡባቸው ሁለት ምክንያቶች እንዳሉ ያምናሉ። "ጌታቸው አሰፋ በመንግስት ላይ መንግስት የነበረ፣ ለብዙ ሰው ሞትና መከራ የዳረገ በለውጥ ሀይሎች ዘንድ እጅግ የማይውደድ፣ ለውጡን ለመቀልበስ አልያም ለማዝገም ከሚፍጨረጨሩ የቀድሞ የወያኔ በለሥልጣናት አንዱ መሆናቸውን አቶ አብድ እሌይ በደንብ ያውቃል። ስለዚህ ለመደመር ጌታቸውን ማጥቃት" የመጀመሪያው ምክንያት አድርገው አቅርበውታል። 
ጦማሪ ዳንኤል ብርሐነ ንግግሩን ተመልክቶ የግሉን አስተያየት አስፍሯል። "የንግግራቸው ፍሬ ነገር በአዲስ አበባ የሚገኙ የአብዲ ተቀናቃኞች የተደራጁት በጌታቸው አሰፋ ነው የሚል ነው" ያለው ዳንኤል ርዕሰ-መሥተዳድሩ "አዲስ አበባ ያለውን ሀይል እሱ ነው ያደራጀው"  የምትል ሐሳባቸውን በማስረጃነት ጠቅሷል። ዳንኤል በፌስቡክ ገፁ እንደፃፈው ዋናው መልዕክት ይኸው ጉዳይ ነው። ዳንኤል "ከዚያ ባለፈ አብዲ ስለ ጌታቸው ሲያማርሩ የመጀመሪያቸው አይደለም። በሶማሌ ክልል ቴሌቭዥን እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2013/14 ተመሳሳይ ነገር ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ስለዚህ የከረመ ግለሰባዊ አለመግባባት ነው። ምን አልባት ጌታቸው ምላሻቸውን ይፋ አድርገው የሳምንቱን አጀንዳ ይሰጡን ይሆናል" ሲል ሐሳቡን አጋርቷል። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ሳሙኤል በዛብህ በበኩሉ "አብዲ ኢሌ ጋዜጠኞች ሰብስቦ ኑዛዜዉን በማሰማቱ ብቻ ከህግ ሊያመልጥ አይችልም፤ አይገባምም....አንድ ሚሊየን ያህል ኦሮሞዎችን እድሜያቸውን ሙሉ ከኖሩበት ሀገራቸዉ በግፍ ያባረረ፤ በርካቶችን በጭካኔ የገደለ የሰወረና ለአካል ጉዳት የዳረገ አረመኔ፤ አብረዉት ህዝብን ሲያሳድዱ የኖሩ የጭካኔና የግፍ ተባባሪ ጓደኞቹን ስላጋለጠ (ስላማ) ብቻ በህግ ከመዳኘት መቼም ሊያመልጥ አይችልም...." ሲል ኮምጨጭ ያለ ትችቱን በፌስቡክ አጋርቷል።  ደቻሳ አንገቻ ታደሰ  ደግሞ "ወዳጄ ፍሬቻ ሳያሳዩ መታጠፍ ይሉሃል ይሄ ነው ፡፡ የአብዲ ኢሌን ገራሚ U-Turn የመጨረሻ ወድጄዋለው፤ እነዛ በሱ ዙሪያ ሲያሽቃብጡ የነበሩ "ጋዜጠኛ /ብሎገር / " ገለመሌ ምን ብለው ይሆን?" ሲሉ ጠይቀዋል። 
መሰንበት አሰፋ  "አብዲ መሀሙድ ዑመር ጥፋታቸውን መናዘዛቸው እና ለጠቅላይ ምኒስትሩ የማሻሻያ ሒደት ድጋፋቸውን መግለፃቸው መልካም ነው። ይሁንና የነበርንበትን እና ያለንበት ፖለቲካዊ ቀውስ ጥልቀት ያጋለጠ ነው" ባይ ናቸው። 

የደብረ ማርቆስ ተቃውሞ እና ኹከት 

ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ አራት ቀን 2010 ዓ.ም. ከኢሕአዴግ ጉምቱ ሹማምንቱ አንዱ የሆኑት አቶ በረከት ስምዖን በደብረ ማርቆስ ከተማ ታይተዋል የሚል ወሬ በመሰማቱ ተቃውሞ እና ኹከት ተቀስቅሶ ነበር። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን በፌስቡክ ገፃቸው እንዳሰፈሩት በዕለቱ በተፈጠረው ኹከት ሶስት ሆቴሎች ፤ ሁለት የፋይናንስ ተቋማት፤  አንድ መኖሪያ ቤት እና አስር ተሽከርካሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። 2 ሰዎች ደግሞ ተጎድተው ሆስፒታል ነበሩ። አቶ ንጉሱ "እንዲህ ዓይነት ግርግር በሌሎች አካባቢዎችም እንዲስፋፋ ከፍተኛ ዘመቻ እየተደረገ መሆኑን የሚያሳዩ ተጨባጭ መረጃዎች እየደረሱን ሲሆን ምንም መነሻ በሌለው የሀሰት መረጃ ራሳችንን በራሳችን ከማጥፋት እንድንቆጠብ እና ማንኛውም የክልላችን ነዋሪ ክልላችን የብጥብጥ ማዕከል እንዳይሆን በምናደርገው ጥረት እንዲያግዘን ጥሪ እናስተላልፋለን" ብለዋል። 

አዲስ አይን የተባለ መፅሔት ግን "አቶ በረከት ስምዖን በደብረ ማርቆስ ጎዛምን ሆቴል ታግተዋል ተብሎ የተሰራጨው ወሬ ሃሰት መሆኑን ለአቶ በረከት ስምዖን በመደወል ለማረጋገጥ ችለናል"  የሚል መረጃ በፌስቡክ አሰራጭቷል። መጽሔቱ አቶ በረከት እየሳቁ "ይህ የተለመደ በሬ ወለደ ነው" የሚል ምላሽ እንደሰጡት ገልጿል።

የመረጃው እውነተኛነት አለመረጋገጥ እንዲሁም ተቃዋሚዎች ወስደውታል የተባለው ዕርምጃ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። የከተማዋ ወጣቶች እንዲህ አይነት እርምጃ ሊወስዱ አይገባም የሚሉም አልጠፉም። ብአዴን እና ኢሕአዴግን አጥብቆ የሚተቸው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ስለ ኩነቱ "ዛሬ በጠዋቱ የደብረማርቆስ ሕዝብ አንድ ሆቴል ከበበ፣ መኪና ያዘ፣ እቃ ያዘ፣ ሹፌሩን ፈትሾ መረጃ አስተላለፈ። በዚህ ሁሉ ወቅት ፖሊስ ሆቴሉ ውስጥ አንድ አካል እንዳለ አስመሰለ። ወይንም አደረገ። በረከት አዲስ አበባ እንዳለ የሚናገሩ አሉ። ሕዝብ ደግሞ ደብረማርቆስ ነው ብሎ ከብቦ ውለዋል!ምን አልባት ይህ ሴራ ይሆናል" የሚል ግምቱን አስፍሯል። 

የቀድሞው የአቶ በረከት የትግል ባልደረባ አቶ ያሬድ ጥበቡ ስለጉዳዩ የተፃፈ መረጃ ፌስቡክ ላይ ማንበባቸውን ፅፈው የሚከተለውን ብለዋል። "ባለፈው ሳምንት በረከት ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ ለውጡን ለማኮላሸት የሚያደርገውን ሩጫ አቁሞ በፈቃዱ ከፓርቲ መሪነቱ እንዲወርድ ጠይቄ ነበር ። ለጥያቄዬም መነሻ የሆነኝ፣ ከማምነው ምንጭ በረከት የቅማንትን ጉዳይ ለማጦዝ እየሠራ መሆኑን ሰምቼ ስለነበር ነው ። ዛሬ በደረሰበት ጥቃት ደስተኛ አይደለሁም ። ይህ የለውጥ ሂደት ከግቡ ሊደርስ የሚችለው፣ በሥርአቱ ውስጥ የቆዩት ጎምቱዎች ፍርሃት እስካልተሰማቸውና፣ ያጋበሱትን ንብረትና የሠሩትን ወንጀል የሚከታተልና የሚያሳድድ ስሜት እስከሌለና ሂሳብ የማወራረድ ግፊት እስከሌለ ድረስ ነው። እንደ በረከትና ህላዌ ያሉት ጎምቱዎች ደግሞ ይቅርታ መጠየቅ የሚያስገድዳቸው ወንጀል ሊኖር ቢችልም፣ ንብረት በህገወጥ መንገድ በማጋበስና በማሸሽ ስማቸው ሲነሳ አልሰማሁም። አንድም ነባሩን ሥርአት ለማስቀጠል የሚደክሙት በእርጅና ዘመን ለመጦሪያ የሚሆን ሃብት ያልያዙና፣ ለውጡ ድንገት ከተፍ ያለባቸው በመሆኑ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። በእርጅና ዘመናቸው ተንከባክቦ ሊይዛቸው፣ ሊያሳክማቸው ይችል የነበረው ሥርአት ድንገት ሲፈርስ ባዶነት ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ" የሚል ሐሳባቸውን አጋርተዋል። 
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ