1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያልተፈታው የሐረር የውኃ ችግር

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2011

ሐረር ዛሬም የውኃ አቅርቦት ችግር እያማረራት ነው። ውኃ ካገኙ ወር እንዳለፋቸው የሚናገሩ የከተማዋ ነዋሪዎች አሉ። ነዋሪዎቹ የውኃ ችግሩን የከበደ ያደረገባቸው ደግሞ የሰማይ ጠልም ማለትም ዝናብም አለመዝነቡ እንደሆነም ነው የሚናገሩት።

https://p.dw.com/p/3AGE0
Äthiopien Trockenheit - Warten auf Wasser in Harare
ምስል DW/M. Teklu

ነዋሪዎች የቧምቧ ሆነ የዝናብ ውኃ ካገኙ መሰንበታቸውን ይናገራሉ

ንፁሕ የመጠጥ ውኃን ለኅብረተሰቡ በአግባቡ ማሰራጨት ፈተና በሆነባት ሐረር - ነዋሪዎቿ ዛሬም የዕለት ተዕለት ኑሮን በአስቸጋሪ መንገድ መኖር ግድ ብሏቸዋል ። ሐረር ዛሬም የውኃ አቅርቦት ችግር እያማመራት ነው። ውኃ ካገኙ ወር እንዳለፋቸው የሚናገሩ የከተማዋ ነዋሪዎች አሉ። ነዋሪዎቹ የውኃ ችግሩን የከበደ ያደረገባቸው ደግሞ የሰማይ ጠልም ማለትም ዝናብም አለመዝነቡ እንደሆነም ነው የሚናገሩት።ድሬደዋ ፣ በኦሮሚያ ክልል ሀረማያ አካባቢ የሚገኘው ኢፈ ባቲና በክልሉ ድንበር ላይ የሚገኘው የረርን ጨምሮ በሦስት የውኃ መገኛ አካባቢዎች ላይ የተመሰረተው አቅርቦት እና ስርጭት ካጋጠመው እክል ሙሉ በሙሉ መላቀቅ አለመቻሉም ነገሩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል። እንደ ነዋሪዎች አስተያየት አካባቢዎችን በዞን ከፋፍሎ በሚተገበረው የከተማዋ የውኃ ስርጭት ከአንድ ወር ባነሰ ግዜ ውኃን ማግኝት ብዙም የሚታሰብ አይደለም ፤

« ወር አልፎናል እኛ አካባቢ ውኃ ከመጣ፤ አሁን አላየንም ባለፈው የዛሬ ስንት ግዜ ተዘጋ ባለን አጋጣሚ ቀዳን ከዛ ጠፋ  እግዚአብሔር እንዳለው ነው እንግዲህ ውኃውም ጠፍቷል ዝናቡም ጠፍቷል ሁለቱም አንድ ላይ እንዴት እንደምንሆን አናውቅም»

Äthiopien Trockenheit - Warten auf Wasser in Harare
ምስል DW/M. Teklu

« በአንድ ወር መጣ ያኔም በደንብ አልቀዳንም ከሁለት ቀን በላይ እሷም እየተቆራረጠ ነው የሚወርደው ። አሁን እራሱ አንድ ወር ይሆነዋል አናገኝም። ደካማ አለ፣ በሽተኛ አለ ፤ እኔ አሁን በሽተኛ ነኝ የዲስክ ችግር አለብኝ። ውኃ ከጠፋ የት ሄጄ ነው የምቀዳው? የትኛው ወንዝ ሄጄ ነው የምቀዳው?  የሰው ልጅ ያለ ውኃ አይኖር?!»

ከሌላ አካባቢ በጀሪካን ውኃ ቀድተው ሲመለሱ አግኝተን ያነጋገርናቸው ወ/ሮ ቀለሟ በየዕለቱ ውኃ ፍለጋ ከተማረሩ ነዋሪዎች አንዷናቸው ፡፡

« ሁሌ መዞር ጀሪካን መሸከም በጣም ነው የመረረን፤ እውነት!  ልጆቹ ተማረው አሁን አልቀዳልሽም አሉኝ ጭራሽ። ስለዚህ እኔ ራሴ ገባሁበት ፤ ምን ይባላል ይሄ?»

 የሐረር ነዋሪዎች የከፋ ደረጃ ላይ ለደርሰውና ፈተና ውስጥ ለከተታቸው ችግር መንግሥት አስፈላጊውን መፍትሄ እንዲያበጅለት ጠይቀዋል።  የክልሉ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወለደ አብዶሽ እንደሚሉት ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ከሆኑ ምክንያቶች ቀዳሚው የየረር ውኃ መስመር ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት በማቆሙ ነው።  

Äthiopien Trockenheit - Warten auf Wasser in Harare
ምስል DW/M. Teklu

« የኤረርን በምንመለከትበት ጊዜ ዋናው መንስዔ እዛ አካባቢ ያሉ የኅብረተሰብ አካላት ያቀረቡት ችግር፤ ያነሷቸው ጥያቄዎች ናቸው ። አንደኛው በትክክለኛው መንገድ የቀረበ እና መፍትሄ አንዲሰጥ ያቀረቡት የዚህ የካሣ ጥያቄ ነው።  ካሣውም ምንድነው  ከሁለት አመት በፊት የተከፈለን ካሣ አነስተኛ ነው እሱ ሪቫይዝ ተደርጎ ሊከፈለን ይገባል ነው ። ሁለተኛው ደግሞ ምንም ምክንያት የሌለው ኤየር ሪሊዝ ቫልቭ እየሰበሩ ለእርሻ የማጠጣት ሁኔታ አለ ፡፡ ከስድስት ወር በላይ ለማስታመም ሞክረን ነበር በኛ በኩል።»

ኃላፊው ባነሱት ምክንያት በአሁን ሰዓት አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠው የየረር ውኃ ፕሮጀክት 280 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ የተደረገበትና አንድ አመት ግዜን እንኳን አገልግሎት ያልሰጠ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ይህን ያክል ወጪ ወጥቶበት የተሰራው ፕሮጀክት  የገጠመው ችግር ለወራት ቢዘልቅም ዛሬም ድረስ መፍትሄ አላገኘም።  በቅርቡ አንድ ኮሚቴ ተዋቅሮ ለካሣ ጥያቄው መፍትሄ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ከዚያ በተጨማሪ ሕግ የማስከበር ሥራ መስራትም ያስፈልጋልም ብለዋል። በሐረር ንፁሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ ከተፈጠረው ከዚህ ችግር ባለፈ የቱቦዎች በጨው መደፈን ሌላኛው በስርጭት ላይ የተጋረጠ ተግዳሮት ነው ፡፡ ባለስልጣኑ ለችግሮቹ ደረጃ በደረጃ መፍትሄ ለመስጠት እየሠራሁ ነው ቢልም ችግሩ ዛሬም እንዳለ ነው።

መሳይ ተክሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ