1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ገደብ ያጣው ወደ የአዲስ አበባ የሚደረግ ፍልሰት

ረቡዕ፣ መጋቢት 6 2015

በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣው ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች የሚደረግ መጠነሰፊ ፍልሰት ከተማዋን ከማጨናነቅም ባለፈ የአገልግሎት አሰጣጥ መስተጋብሩ ላይ የከፋ አደጋ እንደሚደቅን ተገለጸ፡፡ ፍልሰቱ ኑሮን ከማናርም ባለፈ ለፀጥታና ደህንነት ስጋትም ነው ተብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/4Oj5V
Äthiopien Addis Abeba | Hauptstadt will Migration  minimieren
ምስል Seyoum Getu/DW

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወደ ከተማዋ የሚደረገዉ ፍልሰት ለከተማዋ የፀጥታ ስጋት መሆን ተናግረዋል

በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣው ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች የሚደረግ መጠነሰፊ ፍልሰት ከተማዋን ከማጨናነቅም ባለፈ የአገልግሎት አሰጣጥ መስተጋብሩ ላይ የከፋ አደጋ እንደሚደቅን ተገለጸ፡፡ ፍልሰቱ ኑሮን ከማናርም ባለፈ ለፀጥታና ደህንነት ስጋትም ነው ተብሏል፡፡

“አዲስ አበባ ላይ እንደምትመለከተው ሰው ከአቅሟ በላይ ከተማዋን አጨናንቆአት መፈናፈኛ የለም፡፡ አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጆች ጭምር ስራ ትተው እዚህ ናቸው፡፡ ህጻን ሽማግሌ የለም በርካታ ህዝብ እዚህ መጥተው አንዳንዱ በልመና ተሰማርተዋል፡፡አንዳንዱም በንጥቅያ ላይ የየተሰማሩ አይጠፉም፡፡ ሰው ወደዚህ ስፈልስ ራሱ የግንዛቤ ችግር ያለ ይመስላል፡፡ ይሄ ገንዘብ ሚታፈስበት ከተማ አይደለም፡፡”

Äthiopien Addis Abeba | Hauptstadt will Migration  minimieren
አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወልደው ያደጉት የ70 ኣመት አዛውንት ካዩትና ከተዘቡት ምልከታቸው ለዶቼ ቬለ የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ አቶ ጌታቸው አበራ የተባሉት እኚህ የእድሜ ባለፀጋ ከፍተኛ እና ከቁጥጥር ውጪ በሚመስለው የአዲስ አበባው ፍልሰት አሁንም ስጋታቸውን ሲገልጹ፡ “የቤት ኪራይ አሁን እንደምትመለከተው አይቀመስም፡፡ ለእግር መረገጫ ብቻ የምትሆን ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆነች አነስተኛ ክፍል ከ5000 ብር በታች ማግኘት ዘበት እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ ካለው የኑሮ ውድነት ከምግብ ፍጆታ መናር ጋር ስታነሳው ችግሩን አስከፊ ያደርገዋል፡፡ ሰው ያለስራ ከአቅም በላይ ከተማዋን አጨናንቋት ስቸገር ወደ ንጥቂያ ይገባል፡፡ ልመናም እንደምታየው ከአቅም በላይ ነው፡፡ ሰጥተም አትዘልቀውም፡፡ ገንዘቡም አቅም አጣ” ብለዋል፡፡

በመዲናዋ አዲስ አበባ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት አለመረጋጋቱ ሰፍቶ በተስተዋለበት ባለፉት 3 ዓመታት ፍልሰቱ አይሎ ነው የታየው፡፡ በተለይም በየጎዳናው ህጻናትን ይዘው የሚለምኑ ከተለያዩ የአገሪቱ አቅጣጫ የጎረፉ ዜጎችም አሁን አሁን የከተማዋ መገለጫ እየሆኑ ነው፡፡ በከተማዋ ከትራንስፖርት ጀምሮ የሚሰጡ አገልግሎቶችም ካለው የሰፋ ፍላጎት ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም እየሆነ የመጣ መስሏል፡፡

የፖለቲካል ኢኮኖሚው ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በዚህ ላይ በሰጡን አስተያየት የዚህ ችግር መንስኤው ሁለት ናቸው፡፡ “አንደኛው የስራ እድል ፈጠራ ሲሆን ሌላኛው የደህንነት ዋስትና ፍላጋ ነው የሚመስለው፡፡ አዲስ አበባን ከአቅሟ በላይ ሊያፈነዳት የደረሰው ፍልሰት ከነዚህ ሁለት ምክኒያቶች ውጪ ሊሆን አይችልም” ብለዋል፡፡

Äthiopien Addis Abeba | Hauptstadt will Migration  minimieren
አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

የሰዎች ወደ ከተማ መፍለስ በመደበኛ ሁኔታ የሚኖረው ማህበራዊ ፋይዳ ብኖርም አሁን ላይ ወደ አዲስ አበባ እየተደረገ ያለው ፍልሰት ግን ፍጹም ጤናማ ያልሆነም ነው ሲሉ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል፡፡ “የአሁኑ የአዲስ አበባ መጨናነቅ በሚታይ መልኩ በቀድሞው መደበኛ ነዋሪ ላይ አስከፊ ኑሮ ውድነት እና የተለያዩ አገልግሎቶች መጨናነቅን አስከትሏል፡፡ ይህ ደግሞ ለነባሩም ሆነ ለአዲስ መጪው ነዋሪ የማይመች ነገርን ይፈጥራል፡፡ የሚፈጠረው የአገልግሎት መጨናነቅ የዋጋ ንረትን ያስከትላል፡፡ ከተማዋም ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲያስፈልጋትና ከተሞች ያለ አግባብ እንዲለጠጡ በማድረግ ማህበራዊ አገልግሎት መስተጋብሩ ላይ አላስፈላጊ ጫናን ይፈጥራል” ብለዋልም፡፡

ለችግሩ ዘላቂ ያሉት መፍትሄን ሲያስቀምጡም፡ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል ላይ በትኩረት መስራት እልባት ይሆናል ነው ያሉት፡፡ በተለይም ኢንቨስትመንትን በኢትዮጵያ ገጠር ክፍል ማስፋፋት የስራ እድልና ከተሜነት በዚያው እንዲዳረስ በማድረግ መሰረታዊ የሰው ልጅ መገልገያዎች በዚያው እንዲዳረስ እንደሚረዳም አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን ትናንት ማካሄድ ሲጀምር የ2015 ዓ.ም. የመጀመሪያ መንፈቀ-ዓመት የስራ ክንውን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለይም ከመጠነ ሰፊው ወደ ከተማዋ ከሚደረግ ፍልሰት ጋር አያይዘው በሰጡት ማብራሪያ ፍልሰቱ የከተማዋ የፀጥታ ስጋትም ወደ መሆን መሸጋገሩን አመልክተዋል፡፡ ከንቲባ አዳነች በተለይም “ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግስትን በመጣል በኃይል ስልጣን ለመቆጣጠር ያለመም ነው” በማለት ስጋቱን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

 

ስዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ