1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ ጋምቢያ ነዋሪዎች የጃሜህን መመለስ ይናፍቃሉ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 4 2010

የጋምቢያው ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው ሀገሪቱን ለ22 ዓመታት ከመሩት ያህያ ጃሜህ እጅ የመሪነቱን ስልጣኑን ፈልቅቀው ከወሰዱ አንድ ዓመት አለፈ፡፡ ሆኖም የምዕራብ አፍሪካዊቷ ትንሽይቱ ሀገር ዜጎች አሁንም በየብሔራቸው ተቧድነው እንደተከፋፈሉ አሉ፡፡ ጃሜህን የሚደግፉቱ፤ የቀድሞው መሪ ወደ ሀገራቸው በክብር እንዲመለሱ ይሻሉ፡፡

https://p.dw.com/p/2xYPp
Kombobild Gambia Yahya Jammeh Adama Barrow

የምዕራብ ጋምቢያ ነዋሪዎች የጃሜህን መመለስ ይናፍቃሉ

ከአንድ ዓመት በፊት ከስልጣናቸው የተፈነገሉት የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዝዳንት ያህያ ጃሜህ ጨካኝ እና ከ21ኛው ክፍለ ዘመን አምባገነኖች መካከል እንደ አንዱ ተደርገው ሲቆጠሩ ቆይተዋል፡፡ ስለእርሳቸው ምንም ይባል ምን በትውልድ ስፍራቸው ፎኒ ካንሳላ ላሉ ነዋሪዎች ግን ሰውየው በጣሙኑ የሚናፈቁ ሆነዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ከጃሜህ ስልጣን መልቀቅ በኋላ ህይወት ከቀን ወደ ቀን መራር እየሆነባቸው እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ 

ከጆላ ብሄር የሚመዙት ጃሜህ በቁጥር አነስተኛ ለሆኑት የብሔራቸው ሰዎች መከታ ነበሩ፡፡ የዛሬን አያደርገውና ውሃ እና ኤሌክትሪክ ሳይቀር በነጻ እንዲቀርብላቸው ያደርጉ ነበር፡፡ በሀገሪቱ ምዕራባዊ ጠረፍ ላለው የፎኒ ክልል ጃሜህ ዘመናዊ የመገበያያ ቦታም ገንብተዋል፡፡ በዚያ እንደ ኡሚ ሲሴይ ያሉ የአካባቢው ሴቶች የሚሸጧቸውን ምግቦች የሚያቆዩባቸው ማቀዘቀዣዎች ተዘጋጅተውላቸዋል፡፡ የፎኒ ካንሳላ ነዋሪዋ ኡሚ ነገሮች እንደድሮው እንዳልሆኑ ለዶይቼ ቬለው ዘጋቢ ነግረውታል፡፡ 

Oumie Ceesay
ምስል DW/F. Muvunyi

“ፕሬዝዳንታችን ከለቀቁ በኋላ በምንም ደስተኛ አይደለንም፡፡ ደስተኛ ያልሆንበት ምክንያት ኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ጥሩ አይደለም፡፡ በየጊዜው ይጠፋል፡፡ እንደምታዩት እኔ አሳ የምሸጥ ነኝ፡፡ አሳዎቻችን የምናቀዘቅዝበት በቂ ኤሌክትሪክ የለንም፡፡ ውሃ የለም፡፡ ሁሉም ነገር መጥፎ ነው የሆነው” ይላሉ ኡሚ።

አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የማስታወቂያ ሚኒስትር ለሆኑት ዴምባ አሊ ጃዎ ግን የነዋሪዋ አባባል አይዋጥላቸውም፡፡ “በአካባቢው የውሃ እና ኤሌክትሪክ አቅርቦት አልተቋረጠም” የሚሉት ሚኒስትሩ “ተቃውሞ የሚያሰሙት ለአገልግሎቱ ክፈሉ በመባላቸው ነው” ይላሉ፡፡

“ፕሬዝዳንት ጃሜህ ስልጣን ላይ በነበሩ ወቅት ለተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ፍትሃዊ ያልሆነ ጥቅም ይሰጡ ነበር፡፡ ይህ ለተቀረው የሀገሪቱ ህዝብ አግባብ አልነበረም፡፡ አንድ የተወሰነ መንደር የውሃ እና ኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን በመንግስት ወጪ ያለምንም ክፍያ ሲያገኝ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ጭርሱኑ የኤሌክትሪክ ብርሃን እንኳ አልነበራቸውም፡፡ ያ ፍትሃዊነት የጎደለው አሰራር ነው፡፡ መንግስት አሁን የሀገሪቱን ሀብት በእኩል ለማዳረስ እያሞከረ ነው፡፡”
በጋምቢያ በጎርጎሮሳዊው ታህሳስ 2016 በተደረገው ምርጫ ጃሜህ በከበርቴው አዳማ ባሮው ሲሸነፉ ስልጣናቸውን ላለመልቀቅ በብርቱ አንገራግረው ነበር፡፡ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ባሮው በጋምቢያ ጎረቤት ሴኔጋል ተጠልለው አዲሱን መንግስታቸውን ለመመስረት ሲጥሩ በመዲናዋ ባንጁል “ማንም አይነካኝም” ብለው የተቀመጡትን ጃሜህን የየሀገራቱ መሪዎች ሲያግባቧቸው ቆይተዋል፡፡

Gambias Informationsminister Demba Ali Jawo
ምስል DW/F. Muvunyi

የፖለቲካ ውጥረቱን በውይይት ለመፍታት ሲሞክር የነበረው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ጃሜህን በጦር ኃይል ከስልጣን ለማውረድ ወታደሮች ሲልክ ነገሮች ተቀየሩ፡፡ ያኔ አሻፈረኝ ያሉት ጃሜህ ጋምቢያን ለቀቅው ለመውጣት ተስማሙ፡፡ ፕሬዝዳንቱ እሺታቸውን የገለጹት ዳጎስ ያለ ገንዘባቸውን እና ቅንጡ መኪናዎቻቸውን ወደ ተሰደዱባት ኤኳቶሪያል ጊኒ ለመውሰድ ያቀረቡት መደራደሪያ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው፡፡

ጃሜህ ጋምቢያን ከለቀቁ ከአንድ ዓመት በኋላም ግን APRC የተሰኘው ፓርቲያቸው ደጋፊዎች የእርሳቸው ምስል የታተሙባቸው ካኔቴራዎች እና ልብሶችን አድርገው መታየታቸውን ቀጥለዋል፡፡ “አላህ ከፈቀደ ለቢሊዮን ዓመታት እንኳ መሪ መሆን እችላለሁ” ይሉ የነበሩት የጃሜህ አይነት ቀልብ ያዥ ተተኪ ለማግኘት ፓርቲያቸው ተስኖታል፡፡ 

የAPRC ፓርቲ ምስሶ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሆኑት የ49 ዓመቱ ሙሳ አሙል ናያሲ ከስልጣናቸው ለተባረሩት የጋምቢያ ፕሬዝዳንት በግልጽ ድጋፋቸውን ከሚያሳዩት መካከል ናቸው፡፡ የጋምቢያ የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ናያሲ በጃሜህ ዘመነ መንግስት የመሬት ጉዳዮችን የሚመለከተው መስሪያ ቤትን በሚኒስትርነት ይመሩ ነበር፡፡ ናያሲ እንደ ፎኒ ካንሳላ ነዋሪዎች ሁሉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በክብር ወደ ሀገራቸው እንደሚለሱ ይሻሉ፡፡

“ማንም ጋምቢያዊ ያላሰበውን ትልቅ ልማት ለሀገሪቱ አምጥተዋል፡፡ ምንም ይሁን ለሀገራቸው ብዙ ነገሮች አድርገዋልና። የመመለስ እና እንደማንኛውም ተራ ዜጋ ሁሉ በሀገሪቱ የመቆየት መብት ለሲጣቸው ይገባል”  ይላሉ ናያሲ፡፡ 

Musa Amul Nyassi, Abgeordneter im gambischen Parlament
ምስል DW/F. Muvunyi

አንድ ነገር ርግጥ ነው፡፡ ሀሳብን በነጻነት በመግለጽ ረገድ ጋምቢያ ተለውጣለች፡፡ በርካታ ዜጓቿ በጃሜህ ጊዜ እንደነበረው ለህይወታቸው ሳይሰጉ፣ ያለፍርሃት የተሰማቸውን መናገር ጀምረዋል፡፡ ሆኖም ከህዝቧ አንድ ሶስተኛው አሁንም በቀን ከአንድ ዶላር በታች ከሚያገኙ እና ከድህነት ወለል በታች የሚመደቡ ናቸው፡፡ በድህነት የሚኖረው አብዛኛው ህዝቧ በገጠር የሚኖር ነው፡፡ 

ስድሳ በመቶ ህዝቧ ህይወቱ በግብርና ላይ በተመሰረተባት ጋምቢያ የዝናብ መዛባት፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት እና በየጊዜው የሚዋዥቀው የምግብ ዋጋ መጀመሪያውኑም ለተከፋፈለችው ሀገር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል፡፡ በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው ህዝብ የጃሜህን ዳግም መምጣት ለመናፈቁ አንዱ ምክንያት የኑሮው ሁኔታ ነው፡፡

የጃሜህ ደጋፊዎች እና የፓርቲያቸው አባላት የቀድሞው ፕሬዝዳንት “ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸሙም” በሚል አይከራከሩም፡፡ ነገር ግን ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ተወስዶ፣ እርሳቸውንም በተከሳሽ ሳጥን ቆመው ማየት አይፈልጉም፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የጃሜህን ደጋፊዎች ኢላማ አድርጓል ሲሉ ይወነጅላሉ፡፡ የምክር ቤት አባሉ ናያሲም የዚህ ሀሳብ ተጋሪ ናቸው፡፡

“አንድን ፖለቲካ ፓርቲ ሁሌም ቢሆን ጨምድደህ፣ አባላቱን እያሰርክ፣ ወድ ፍርድ ቤት እየወሰድህ እና እያንገላታህ ልትቆይ አትችልም፡፡ አሁን ካለው መንግስት ጋር ሁሌም ቢሆን ያለን ልዩነት በዚህ ላይ ነው” ሲሉ ይወቅሳሉ ናያሲ። 

Junge mit T-Shirt von gambischem Ex-Präsident Yahya Jammeh
ምስል DW/F. Muvunyi

አዲሱ የአዳማ ባሮው መንግስት በበኩሉ የጃሜህ ደጋፊዎች “የውጭ አማጽያንን በቤታቸው በማስጠለል ሀገሪቱን ለማተራመስ እየሞከሩ ነው” ሲል ይከሳል፡፡ ደጋፊዎቹን በተመለከተም የተሰላ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ የቀድሞውን መሪ ደጋፊዎች ልብ ለማሸነፍ የፈለጉ የመሰሉት ፕሬዝዳንት ባሮው የካቢኔ አባላቶቻቸውን አስከትለው የጃሜህ ጠንካራ ይዞታዎች ናቸው የሚባሉ ቦታዎችን በቅርቡ ጎብኝተዋል፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አሊ ጃዎ ተስፋ ይታያቸዋል፡፡

“ጊዜ በሄደ ቁጥር ህዝቡ ጃሜህ እንደሄዱ እና ወደዚህች ሀገርም በመሪነት ዳግም ላይመለሱ እንደሚችሉ እየተረዳ ይመጣል የሚል ተስፋ አለን” ይላሉ ሚኒስትሩ።   

ጃሜህ በእርግጥም ወደ ኢኮቶሪያል ጊኒ ሄደዋል፡፡ በፎኒ ካንሳላ ክልል ባሉ ነዋሪዎች ልብ ግን አሁንም እንደነገሱ አሉ፡፡  

ፍሬድ ሙቬዩኒ/ ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ