1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላም የሚያደፈርሱ አካላትን አስጠነቀቁ

እሑድ፣ ነሐሴ 13 2010

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ “አካላዊ ጥቃቶች፤ ግድያዎች፤ የንብረት ውድመቶችና መፈናቀሎችን” መንግስታቸው ከእንግዲህ ወዲያ እንደማይታገስ አስጠነቀቁ። መንግስት የህዝብን ፀጥታ በሚያደፈርሱ እና ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ የተገኘ አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

https://p.dw.com/p/33ONK
Äthiopien Abiy Ahmed OPDO
ምስል Abdulbasit Abdulsemed

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ “አካላዊ ጥቃቶች፤ ግድያዎች፤ የንብረት ውድመቶችና መፈናቀሎችን” መንግስታቸው ከእንግዲህ ወዲያ እንደማይታገስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስጠነቀቁ። መንግስት የህዝብን ፀጥታ በሚያደፈርሱ እና ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩ ህገ-ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ የተገኘ አሊያም የተባበረ አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በላኩት የጽሁፍ መግለጫ ነው። መግለጫው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንትናው ዕለት የመከላከያ ሰራዊት ያሰለጠናቸውን መኮንኖች ባስመረቀበት መርኃ-ግብር ላይ ካደረጉት ንግግር ይዘት ጋር ተመሳሳይነት አለው። ከሰሞኑ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የጸጥታ መደፍረስ የዳሰሰው መግለጫ መንግስታቸው ሊወስደው ያሰበውን እርምጃም ጠቁሟል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው መግለጫቸው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በጥቂት ግለሰቦች እና አካላት በአመዛኙ የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ግድያዎች በዘፈቀደና በስሜት እየተፈጸሙ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል። እንዲህ ያሉ ተግባራት “የሕዝቡን ሰላም፤ ነፃነት እና የኑሮ ዋስትና ከመሰረቱ እያናጉ ናቸው” ብለዋል። “ለሕግ ተገዥነትን ወደ ጎን የማድረግ ትልቅ ዝንባሌ በኢትዮጵያ እየታየ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም “ለሕግ የበላይነት ትልቅ ፈተና የሆነ ጉዳይ ነው” ሲሉ አክለዋል።

“በስሜትና በጥላቻ የሚወሰዱ እርምጃዎች፣ ሕግን ወደ ራስ ፍላጎት እና ስሜት በመውስድ በመንጋ የሚሰጡ ስርአት አልባ ፍርዶችም” ሌላው ትልቁ ፈተና እንደሆነም አንስተዋል። በመንጋ የሚሰጡ የፍትህ እርምጃዎች በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ምኒስትሩ ድርጊቶቹ “በአንድ ክልል፣ ብሔር፣ ቋንቋ ወይም ሃይማኖት የተወሰኑ” አለመሆናቸውንም ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንደ አገር ለመቀጠል አሳሳቢ ናቸው” ያሏቸው እኒህን መሰል እንቅስቃሴዎች “የዜጎችን ደህንነትና የአገሪቱን ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ይገኛሉ” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሒውማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ ተቋማት በአገሪቱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች እና ኹከቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን ጠቁመው አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚያሻቸው ገልጸው ነበር። 

Äthiopien Unruhen in Shashemene
ምስል Privat

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች የምሥራቅ አፍሪቃ ቢሮ ኃላፊ ማርያ ቡርኔት በነሐሴ ወር ብቻ በድሬዳዋ፣ ሻሸመኔ፣ ቴፒ እና ከተሞች በተፈጸሙ የደቦ ጥቃቶች በትንሹ 15 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው ነበር። ኃላፊዋ በዚህ ሳምንት ለንባብ ባበቁት ዘገባቸው የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ግድያዎችን የፈጸሙ ግለሰቦችን ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመንጋ ፍትህ የሚፈጸሙ ግድያዎች እና ጥቃቶች በፍጥነት መታረም እንዳለባቸው መንግስታቸው በጥብቅ እንደሚያምን በዛሬው መግለጫ ግልጽ አድርገዋል። “እንደ ሀገር መውደቅም ሆነ ወደ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አሰራሮች መመለስ ልንቀበለው የማንችለውና ለምርጫም የማይቀርብ የከሰረ አካሄድ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መፍትሄ ያሉትንም ጠቁመዋል።  

“የዜጎችን መብት እና ነፃነት ለማረጋገጥና የአካል፣ የህይወትና የኑሮ ዋስትናቸውን ለማስጠበቅ ብቸኛው መሳርያ ሕግና ሕገ-መንግስታዊ ስርአትን በሙሉ አቅም ማስከበር ነው” ብለዋል። የሕግ የበላይነት መከበር “የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም የመንግሥት የፀጥታ አካላትና ባለሥልጣናት በሙሉ አቅም እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል። የሕግ የበላይነት በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ሲጣስ በተባባሪነት- ዝምታም ሆነ በድርጊት አሊያም በቸልታ እንዳይመለከቱም አሳስበዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረዘም ባለው መግለጫቸው ማገባደጃ ላይ ማንነታቸው በግልጽ ላልጠቀሷቸው አካላት መልዕክት አስተላልፈዋል። “የግልና የቡድን ጥቅሞቻችሁን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማስጠበቅ እየቻላችሁ በተለያዩ ወንጀሎችና ሰላምን የማደፍረስ እኩይ ተግባራት ላይ ለመሰማራት የምታስቡ አካላት ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ አሳስባለሁ” ብለዋል። ሆኖም ከዚህ በተቃራኒው የሚጓዙ ከሆነ ግን መንግስት ህግን ተከትሎ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። 

ተስፋለም ወልደየስ 

እሸቴ በቀለ