1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በአሜሪካ

እሑድ፣ ሐምሌ 22 2010

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በአሜሪካ ጉዟቸው ከኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አድርገዋል። ዋሽንግተን ከተማ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ለበርካታ አመታት የኢትዮጵያ መንግሥትን አበክረው ሲተቹ ከነበሩ የለውጥ አራማጆች ጋር የተነጋገሩት ጠቅላይ ምኒስትሩ ሎስአንጀለስ ገብተዋል

https://p.dw.com/p/32H0I
Abiy Ahmed Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri

በውይይቱ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን አስተያየት

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ለበርካታ አመታት የኢትዮጵያ መንግሥትን አበክረው ሲቃወሙ የነበሩ የለውጥ አራማጆች ከጠቅላይ ምኒስትሩ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በትናንትናው ዕለት ውይይት አድርገዋል። በተገኙባቸው መድረኮች ኢትዮጵያ ያሉባትን ችግሮች ለመፍታት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል። በህጋዊነት ተመዝግበን በኢትዮጵያ ፖለቲካ መሳተፍ እንሻለን የሚል ጥያቄ ያቀረቡ አመራሮች ስለ ብሔራዊ እርቅ እና የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት ላይ ለጠቅላይ ምኒስርትሩ ሐሳብ አቅርበዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ በአሁኑ ጉዟቸው ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ፣ የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ጭምር ተወያይተዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት በዋሽንግተን ከተማ ጠቅላይ ምኒስትሩ ያደረጓቸው ውይይቶች ስኬታማ እንደነበሩ ገልጿል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ወደ ሎሳንጀለስ እና ሜኒሶታ ጉዞ መጀመራቸውንም ገልጿል።

መክብብ ሸዋ 

እሸቴ በቀለ