1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥላቻ አዘል ንግግር በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ መስከረም 11 2011

የኢትዮጵያ መንግስት «የሰዎችን የግል መብትና የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮችን» እንደ ምክንያት በማስቀመጥ በተለያዩ ጊዜያት ማህበራዊ  መገናኛ ዘዴዎችን በመዝጋቱ የተለያዩ የመብት ተሟጋች ግለሰቦችና ተቋማት ትችታቸዉን ሲሰነዝሩ እንደነበር ይታወሳል። መንግስት ያስቀመጠዉን ቀይ መስመር አልፈዉ የተገኙም ሲታሰሩና ሲሰደዱ ነበር።  

https://p.dw.com/p/35Itt
Symbolbild Facebook Zensur Sperre (Getty Images/AFP/I. Kodikara)
ምስል AFP/Getty Images

ጥላቻ አዘል ንግግር በማህበራዊ መገናኛ

ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን መንግስት ሃሳብን በነፃ ማንሸራሸርና መረጃ መለዋወጥን እካያሔደ ያለዉ የለዉጥ አካል መሆኑን አሳዉቆ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መድረኮችን ክፍት አድርጓል። ርምጃዉም ብዙ ወጣቶች፣ አክቲቭስቶች፣ ፖለትከኞች እንድሁም የተለያየ ፍላጎት ያላቸዉን ሰዎችና ተቋማት ወደ መድረኩ እንዲቀላቀሉ ጋብዟል። በዚህ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መድረኮች ላይ ገንቢ ዉይይቶች ቢኖሩም  የግለሰብና የቡድን መብትና ማንነት የሚዘልፉ ይዘቶችም ይታዩበታል።

በጉራጌ ዞን በቡታ ጅራ ነዋሪ የሆነዉ ወጣት ሬድዋን ከድር  ከዚሕ ቀደም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየቱን በመፃፉ ሶስት ወር ታስሮ መለቀቁን ይናገራል።  አሁን ግን መንግስት ዛቻዉንና ማስፈራራቱን ትቶ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መድረኮችን ክፍት ካደረገ ወድህ ሁሉም የተሰማዉን ሃሳብ እየገለፀበት እንደሚገኝ ይጠቅሳል።

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ላይ የሚደረጉ ጥላቻ አዘል ንግግሮች፤ ግለሰብን ወይም ቡድንን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በአካል ጉዳተኝነትና በፆታ ለይቶ ጥቃት መፈፀም መሆንኑን ጥናታዊ ፅሁፎች ያመለክታሉ። ይህ ጥቃትም የፅሁፍ፣ የፎቶዎች፣ የተንቀሳቃሽ ምስል እንድሁም የተለያዩ ይዘቶች የያዙ እንደሆነም ጥናቶቹ ያስቀምጣሉ።

የጎንደር ነዋሪ ምህረት እንደሻዉ ላለፉት 27 ዓመታት በአፈና ዉስጥ የነበረ ማህበረሰብ መብቱንና ግዴታዉን እንዲያዉቅ መንግስት ጎን ለጎን  ካላስተማረ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች «መዝለፍን እንደ መበት እንደሚቆጥሩት» ይናገራል።

ወጣቶች የሚያሰራጩት የፁሁፍ፣ የፎቶና የተንቀሳቃሽ ምስል ይዘቶች መልዕክቱ ሌላ የማህበረሰብ ክፍልን ሊጎዳ እንደሚችል ማሰብ እንዳለባቸዉ ምህረት ይመክራል። የወጣቶች በዘለፋ ንግግር የሚሳተፉትን ማጋለጥና እንዲቆጠቡ ማሳሰብ እንዳለባቸዉም አክሎበታል።

የቡታጅራዉ ነዋሪ ወጣት ሬዱዋን ከድር  ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃምዎች ከስሜት ነፃ መሆን እንዳለባቸዉ ያሳስባል።

«በአካል በሰዉ ፊት አንድን ነገር የማትለዉ ከሆነ በድረገፆች ላይም መፃፍ የለብህም» የሚል አባባል ለወጣቱ ጠቃሚ መሆኑን ደግሞ የኢንፎርሜሼን ቴክኖሎጅ ባለሙያ ማርቆስ ለማ ለDW ይናገራል።

ጥላቻ አዘል ይዘቶች ከግለሰብም አልፎ ከሚዲያ ተቋማት በማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሲያሰራጩ ይታያል። የምድያ ተቋሞች የጥላቻ አዘል ይዘቶች የፀዳ መረጃ ለመስጠት ምን ማድረግ እንዳለባቸዉም ማርቆስ ምክሩን እንደምከተለዉ ለግሰዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የጸደቀዉ የኢትዮጵያ የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ከኮምፕዉተር ጀርባ ሆኖ በሰዎች ነፃነትና ክብር ላይ የሚፈፀም ወንጀል እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል። በዚህ አዋጅ ከተደነገጉት አንዱ አንቀፅም እንደምከተለዉ ይነበባል፣ «ማንኛውም ሰው ሆነ ብሎ፣ የኮምፒዩተር ሥርዓትን በመጠቀም በሚያሰራጨው ጽሁፍ፣ ንግግር፣ ቪዲዮ ወይም ስዕል አማካኝነት በሌላ ሰው ወይም በተጎጂው ቤተሰቦች ላይ ከባድ ጉዳት ወይም አደጋ ለማድረስ በማሰብ ያስፈራራ ወይም የዛተ እንደሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም እንደወንጀሉ ከባድነት ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል» ይላል።

ጥላቻን የሚያባብሱ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መልዕክቶችን ለመመርመርና ለመጠቀም እንዲሁም ከወንጀል ለመዳን ተጠቃሚዎች ቴክኖሎጂ ያመጣዉን ዉጤት እንደት መጠቀም እንዳለባቸዉ የቴክኖሎጅዉ ባለሙያዉ ማርቆስ ይናገራል። 
 

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ