1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥንቃቄ የሚያሻዉ የፕላስቲክ አወጋገድ

ማክሰኞ፣ ጥር 16 2009

በባህር እና ዉቅያኖስ ዉስጥ በዘፈቀደ በሚጣለዉ ፕላስቲክ ምክንያት በዉኃ ዉስጥ የሚኖሩ እንስሳት ህይወት እየጠፋ፤ ከባህር የሚገኙ ፍጥረታትን አዘዉትረዉ የሚመገቡ ወገኖች ጤናም እየተቃወሰ መሆኑ መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከ10 እስከ 20 ሚሊየን ቶን የሚሆን ፕላስቲክ የዓለማችንን የዉኃ አካላት ለብክለት ዳርጓል።

https://p.dw.com/p/2WKHU
Müll am Strand Bombay
ምስል dapd

ጥንቃቄ የሚያሻዉ የፕላስቲክ አወጋገድ

 

በየዓመቱ 300 ሚሊየን ቶን ፕላስቲክ ሥራ ላይ እንደሚዉል ያዉቁ ይሆን? ተፈላጊነቱ ከጨመረ መመረቱ መልካም ነዉ ሊባል ይችላል። ጥናቶች የሚያሳዩት ግን ከዚህ ሁሉ ሥራ ላይ ከዋለዉ የፕላስቲክ መጠን 14 በመቶዉ ብቻ ነዉ ዳግም በሌላ መልኩ ተሠርቶ ጥቅም መስጠት የቻለዉ። በዚህ ምክንያትም በየዓመቱ ለፕላስቲክ የወጣዉ ከ80 እስከ 120 ቢሊየን ዶላር በየቦታዉ ባክኖ የሚቀር ነዉ። ለእሱ የወጣዉ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን 32 ከመቶ የሚሆነዉ ባህር ዉስጥ የተጣለዉ ወይም መሬት ላይ የወደቀዉ ፕላስቲክም ባጠቃላይ ወደ ስነምህዳሩ ገብቶ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደሚቆይ መረጃዎች ያስረዳሉ። ይህ ደግሞ በመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2050 ባህር ዉስጥ ከዓሣዎች ይልቅ በዝቶ የሚገኘዉ  የፕላስቲክ ጠርሙስ እና መሰል የተጣለ የፕላስቲክ ዘር ነዉ። ከዚህ ስጋት ተነስቶ የተቀረጸዉ አዲሱ የፕላስቲክ ምርቶችን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋልና ለማስወገድ ያቀደዉ መርሃግብር፤ የፕላስቲክ ምርቶችን ከሥሪታቸዉ እስከ አወጋገዳቸዉ ተገቢዉ ጥንቃቄ እና ክትትል እንዲደረግባቸዉ አልሟል። ይህን ዕቅድ የሚያንቀሳቅሰዉ ኤለን ማካርተር ተቋም ዕቅዱን ተግባራሚ ለማድረግ የሚጠቀምባቸዉን  መንገዶች በዚህ መልኩ ይገልጻል፤

«አዲሱ የፕላስቲክ ኤኮኖሚ ሊሠራ ወደሚችል ስልት ለመድረስ እየተንቀሳቀሰ ነዉ። ይኸዉም አሁን ያለዉን ዉሰድ፣ ሥራ ፣ አስወግድ የሚል የኤኮኖሚ አሠራር፤  የፕላስቲክ ምርትን ወደ ደጋግሞ ሥራ ላይ ማዋል ወደሚያስችለዉ ስልት ያሸጋግራል።»

ተቋሙ ያካሄደዉ ጥናት እንደሚያመለክተዉ የፕላስቲክ ምርት በዋጋዉም ሆነ በክብደቱ ቅለት የተነሳ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ጥቅም ላይ የመዋል መጠኑ በበ20 እጅ እጥፍ ጨምሯል። በቀጣይ 20 ዓመታትም ይኸዉ መጠን በእጥፍ ከፍ እንደሚልም ጠቁሟል። ዛሬ በየዕለቱ እያንዳንዳችን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የፕላስቲክ ምርትን ሳንጠቀም አንዉልም። ፕላስቲኩን መጠቀሙን እንጂ እንዴት መወገድ እንዳለበት ብዙም የሚጨነቅ የለም። ለዚህም በየመንገዱ ወድቀዉ የሚታዩትን፤ እንዲሁም በባህር እና ዉቅያኖሱ ዳርቻ በብዛት የሚንሳፈፉትን የፕላስቲክ ቁሳቁሶች መመልከቱ በቂ ነዉ። የኤለን ማካርተር ተቋም መሥራች ኤለን ማካርተር ተቋማቸዉ ይህን ጉዳይ በቅርበት ሲያጠና የደረሰበትን በአንድ ወቅት እንዲህ ገልፀዉታል።

«የደረስንበት ባጠቃላይ ፕላስቲክን ስንመለከት 300 ሚሊየን ቶን በየዓመቱ ሥራ ላይ ይዉላል፤ ከእዚህ መካከል ደግሞ 78 ሚሊየን ቶን የሚሆነዉ ለማሸጊያ የሚዉለዉ ፕላስቲክ ነዉ። እዚህ ሁሉ ዉስጥ ታዲያ 14 በመቶዉ ብቻ ነዉ ዳግም ሥራ ላይ መዋል ከቻለዉ የፕላስቲክ ምርት ዉስጥ የተገኘዉ። ካጠቃላዩ ደግሞ 10 በመቶዉ ብቻ ነዉ እንደገና ሥራ ላይ እንዲዉል የሚደረገዉ። ፕላስቲክ ባለዉ የመመረዝ ባህሪ ምክንያትም ከዚያ ሁሉ 5 በመቶዉ ብቻ ነዉ ለጥቅም የሚዉለዉ። በዚህ ምክንያትም እጅግ በርካታ ፕላስቲክ ነዉ እንዲሁ የምንተወዉ። ፕላስቲክን ስናስብ ባለፉት 70 እና 60 ዓመታት የተሠሩት እና አገልግሎት ላይ የዋሉ እያንዳንዳቸዉ ምርቶች ዛሬም አሉ።»

በዚህም ምክንያት ገዝፈዉ የሚታዩት ብቻ ሳይሆኑ ከዘመን ብዛት የተሰባበሩ እና የተበጣጠሱትን የፕላስቲክ ዉዳቂዎች ጨምሮ በየሜዳዉ እና በየዉኃዉ አካል ዉስጥ ከሚገባዉ በላይ መገኘት መቻላቸዉንም ያብራራሉ። ስለዚህ ፕላስቲክ በመሬት እና በባህር ላይ ያስከተለዉን ዉስብስብ እንከን ለማስተካከል የተጣመረና ዘርፈ ብዙ ስልትን መከተል ብሎም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያሻም ያሳስባሉ። የተለያዩ ሃገራት የፕላስቲክ እቃ መያዣዎች ጥቅም ላይ እንዳይዉሉ ለማድረግ በየበኩላቸዉ ሙከራዎች እና ርምጃዎችን እየወሰዱ ነዉ።

ፕላስቲክ የዕቃ መያዣዎች እገዳ በአፍሪቃ

Indonesien Plastiktüten in einem Supermarkt in Jakarta
ምስል picture-alliance/dpa/M. Dirham

 በሀገር ደረጃ ሩዋንዳ ይህን ጠንካራ ርምጃ ስትወስድ የመጀመሪያዋ መሆኗ ነዉ የሚነገርላት። የዛሬ 5 ዓመት ሩዋንዳ በአካባቢ ተፈጥሮ እና በኤኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለዉ በሚለዉ ቁጥር ያለ አቋሟ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ስትወስን በሀገሪቱ ለዚህ አማራጭ የሚሆን ምርት የሚያቀርብ አካል አልነበራትም። የሩዋንዳ መንግሥት ከሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባካሄዱት ጥናት ላይ ተመርኩዘዉ የወሰኑት ይህ እገዳ ምንም እንኳን ለትንሿ አፍሪቃዊት ሀገር ሙገሳን ቢያስገኝላትም፤ ጭለማን ተገን ያደረገ የፕላስቲክ ኮንትሮባንድ ንግድ መፍጠሩ ተሰምቷል። ከጎረቤት ኮንጎ ወደ ሩዋንዳ በሕገወጥ መንገድ የሚገባ ፌስታል እስከ 30 ዶላር እንደሚሸጥ ነዉ የተነገረዉ። ለኮንትሮባንድ ነጋዴዎቹ ዋጋዉ የሚያማልል ቢመስልም እገዳዉን አብዛኛዉ ሕዝብ የሚደግፈዉ በመሆኑ ተጋልጠዉ የተያዙት በአስከፊዉ የኪጋሊ እስር ቤት ከስድስት ወር ላላነሰ የእስራት ቅጣት ሲጋለጡ በመታየቱ ፍራሃትን አንግሶባቸዋል። ሩዋንዳ ሙሉ ለሙሉ ፌስታልን ለማገዷ አስቀድማ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2004ዓ,ም ነዉ እቃ ገዝተዉ መያዣ ለሚፈልጉ ጠቀም ያለ ዋጋ ለፕላስቲክ ከረጢቱ እንዲከፍሉ የወሰነችዉ። ካሜሮንም ተመሳሳይ ርምጃ ነዉ የወሰደችዉ። በዚህም ምክንያት ወደገበያ ጎራ ሲሉ አስቀድመዉ መያዣዎን ይዘዉ መሄድ ይኖርብዎታል።

ካሳየችዉ ስኬት በመነሳት ሩዋንዳ በዚህ ረገድ ብዙ ቢወራላትም በርከት ያሉ የአፍሪቃ ሃገራትም የፕላስቲክ የዕቃ መያዣ ከረጢቶችን ከሞላ ጎደል ሲያግዱ ታይተዋል። ትንሽቷ የቀይ ባህር ዳርቻ ሀገር ኤርትራ ከ12ዓመት በፊት ነዉ ፌስታልን ያገደችዉ። ኬንያ ፌስታል ማምረትንም ሆነ ከዉጭ ማስገባትን በይፋ ያገደችዉ የዛሬ ስድስት ዓመት ነዉ። ደቡብ አፍሪቃ ስሱን ፌስታል ሙሉ በሙሉ አግዳ ወፍራም የእቃ መያዣ ፕላስቲኮች ላይ ቀረጥ ጥላለች። እናም ብዙዎች እንደሚስማሙበት አፍሪቃ ቀስ በቀስ ከፌስታል ራሷን ለማለያየት ጠንከር ያለ ሙከር ከጀመረች ሰነባብታለች።

ባለፈዉ ዓመት መጋቢት ወር እጅግ የሳሱ ፌስታሎችን የሚያመርቱም ሆነ ወደ ሀገር ዉስጥ የሚያስገቡትን ለመቅጣት መዘጋጀቷን ያሳወቀችዉ ኢትዮጵያም የፕላስቲክ እቃ መያዣዎች ላይ ገደብ ለመጣል መዘጋጀቷ ተነግሯል። አንድ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ባለስልጣንን የጠቀሰ ዘገባ እንደሚያመለክተዉ የሀገሪቱን ገበያ የሞላዉ ዉፍረቱ ከ0,03 ሚሊ ሜትር ያነሰ ፌስታል ነዉ። የሐገሪቱ ሕግ ግን እንዲህ ያለዉን ፌስታል ማምረትም ሆነ ከዉጭ ሀገር ማስገባትን ያግዳል። እንደዘገባዉ በአንድ ጥናት ከተቃኙት በሀገሪቱ ከሚገኙ 21 ፋብሪካዎች 14ቱ በዓመት 8 ሺህ ቶን እንዲህ ዓይነት ፌስታል ያመርታሉ።

አፍሪቃን ከፕላስቲክ ምርቶች ለመላቀቅ ከገፋፋት ምክንያቶች መካከል በተለይ በእንስሳት ላይ የሚያደርሰዉ ከፍተኛ ጉዳት ይጠቀሳል። ተፈጥሮ ላይ የሚያተኩረዉ ዓለም አቀፉ ተቋም ዎርልድ ዋይድ ፈንድ ፎር ኔቸር እንደሚለዉ፤ ሞሪታንያ ዉስጥ ብቻ በዋና ከተማዋ ብቻ ከ70 በመቶ የሚበልጡት ከብቶች  ፌስታል በመብላት ያልቃሉ። ለምሳሌነት ሞሪታኒያ ትጠቀስ እንጂ ይህ ችግር የበርካታ አፍሪቃ ሃገራት ዋና ጉዳይ ነዉ። በሌላ በኩልም በየዓመቱ ከ100 ሺህ የሚበልጡ አሳነባሪዎች፣ ጉማሬዊች እና ኤሊዎች ዉኃ ዉስጥ የሚያገኑትን ፕላስቲክ በመብላት ወይም በእሱዉ በመጠላለፍ ምክንያት እንደሚሞቱ ድርጅቱ አመልክቷል። 

የፕላስቲክ እቃ መያዣ መጠቀም ፈፅሞ እንዲቀር የሚጠይቁ በርካታ ጽሑፎች ከተለያዩ ወገኖች በየጊዜዉ እየቀረቡ ነዉ።  ባለፈዉ ዓመት የወጣ አንድ ጽሑፍ ምዕራቡ ዓለም በዚህ ረገድ ከአፍሪቃ መማር እንደሚገባዉ ነዉ ያሳሰበዉ። ጽሑፉ እንደሚለዉ በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ፌስታል መጠቀምን ካገዱ 10 ዓመታት ተቆጥረዋል። የአዉሮጳ እና የሰሜን አሜሪካ ሃገራት ደግሞ  ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ጉድጉድ ማለት የጀመሩት በቅርቡ ነዉ። የፈረንሳይ ብሔራዊ ምክር ቤት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015 ግንቦት ወር ነዉ በማንኛዉም መገበያያ ስፍራ ፌስታል መጠቀምን የሚከልክል ሕግ ያፀደቀዉ። ተግባራዊ የሆነዉ ግን ባለፈዉ ዓመት ታኅሳስ መጨረሻ ላይ ነበር። የአዉሮጳ ኅብረትም ከፈረንሳይ ምክር ቤት አንድ ወር ቀደም ብሎ የፕላስቲክ ከረጢቶችን አጠቃቀም የሚገድብ መመሪያ አጽድቋል። በዚህ መሠረትም አባል ሃገራቱ በሙሉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2025ዓ,ም ለእቃ መያዣነት የሚዉለዉን የፕላስቲክ ከረጢት አጠቃቀም 80 በመቶ እንዲቀንሱ ጠይቋል።

አዲሱ የፕላስቲክ አወጋገድ እቅድ

Bangladesch Dhaka Plastikflaschen Müll
ምስል Getty Images/AFP/M.Uz Zaman

እዚህ ጀርመን በርከት ያሉ የምግብ ሸቀጣሸጥ መሸጫ ገበያዎችም ሆኑ የልብስ መደብሮች ፕላስቲክ መያዣዎችን ጠቅም ባሉ የዩሮ ሽርፍራሪ ሳንቲሞች መሸጥ ከጀመሩ ሰንብተዋል። ይህም ከዚህ ቀደም ለገበያተኛዉ እንደ ማስታወቂያ የየገበያ አዳራሹን ስምና አርማ የያዙ ላስቲኮችን በነፃ ይሰጥ የነበረዉን የለወጠ አሰራር ነዉ። የላስቲክ ከረጢቶቹ በሳንቲም ስለሚገዙም በቀላሉ በየሜዳዉ አይጣሉም። የወረቀት እቃ መያዣዎች ከባድ ነገሮችን መሸከም ባያስችሉም ዋጋቸዉ ቀላል አይደለም። ከኅብረቱ አባል ሃገራት ጣሊያን ቀደም ብላ የዛሬ 4 ዓመት ነዉ በሕግ ደንግጋ የፕላስቲክ እቃ መያዣ አጠቃቀም ላይ ገደብ የጣለችዉ። ከአትላንቲክ ማዶ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ በከተማ እና በግዛት ደረጃ ይህን ርምጃ መዉሰድ መጀመሯ ይነገርላታል። ሰሞኑን ዳቮስ ስዊትዘርላንድ በተካሄደዉ የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ላይ የተገኙ ግዙፍ የዓለማችን ኩባንያዎች የፕላስቲክ አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያሳስበዉን አዲሱን በፕላስቲክ ምርት ላይ የተጀመረዉን ዘመቻ እንደሚደግፉ አሳዉቀዋል። ኮካ ኮላ፣ ዳኖን እና ዶዉ ኬሚካልን ጨምሮ በርከት ያሉ ታዋቂ ኩባንያዎች 70 በመቶ የሚሆነዉን የፕላስቲክ ምርት በአግባቡ ደጋግግሞ መጠቀምን የሚያበረታታዉን ዕቅድ ተቀብለዋል። የምግብ እና የንፅሕና መጠበቂያ ኬሚካሎችን የሚያቀርበዉ ዩኒሌቨር በመጪዉ 8 እና ዘጠኝ ዓመታት ዉስጥ ምርቶቹን የሚያቀርብባቸዉ ፕላስቲኮች ዳግም ጥቅም መዋል የሚችሉ፣ እንደገና በሌላ መልኩ ሊመረቱ የሚችሉ ወይም ደግሞ ሲወገዱ በቀላሉ ሊበሰብሱ የሚችሉ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚሠራ ቃል ገብቷል። ጥንቃቄ የጎደለዉ የፕላስቲክ ምርቶች አወጋገድ በአካባቢ እና በሰዎች ብሎም በእንስሳት ጤና ላይ ያስከተለዉን አደጋ ካስተዋሉ እርስዎም በግልዎ በሚያደርጉት ጥንቃቄ የበኩልዎን መልካም አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላሉ። ዛሬዉኑ ይጀምሩት።

 ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ