የሶሻሊዝም ቅሪት በአፍሪቃ | ባህል | DW | 25.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የሶሻሊዝም ቅሪት በአፍሪቃ

የደቡባዊ ጀርመን ከተማ ባይሮይት በቀዝቃዛዉ የዓለም ጦርነት ዘመን አፍሪቃ አህጉር ከሶቭየት ኅብረትና ከሌሎች የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ሃገራት ጋር የነበራትን ግንኙነት የሚያንፀባርቅ ዓዉደ ርዕይን ስታሳይ ሰንብታለች።

የአፍሪቃዉ ዓለም አቀፋዊዉ ወዛደራዊነት

ከ 19ኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በዓመት አንድ ጊዜ በእዉቁ የጀርመን የረቂቅ ሙዚቃ ቀማሪ በሪቻርድ ቫግነር ስም ከፍተኛ የረቂቅ ሙዚቃ ፊስቲቫልን በማዘጋጀትዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነችዋ ከተማ በሚገኘዉ «ኤባሌባሃዉስ» በሚባለዉና በከተማዉ የሚገኘዉ ዩንቨርስቲ አካል የሆነዉ ማዕከል ሲታይ የከረመዉ ይህ አዉደ ርዕይ ከአፍሪቃ ከእስያ ከሰሜን አሜሪካና አዉሮጳ የተዉጣጡ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ተሳትፈዉበታል።


የእዉቁ ናይጀርያዊ ደራሲ የ«Chinua Achebe» ን «Things Fall Apart» የተሰኘንና ቅኝ ግዛት በአፍሪቃ ያስከተለዉን ከፍተኛ ዉድመት የሚያስቃኘዉ፤ የልበ ወለድ መጽሐፉ ርዕስን የያዘዉ ዓዉደ ርዕይ ፤ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም በአፍሪቃ አህጉር ትቶት ያለፈዉን ጠባሳ በማስቃኘቱ «Things Fall Apart» የሚለዉን ስም መያዙ ተገልጾአል። በእለቱ ዝግጅታችን ባለፈዉ ሳምንት የተጠቃለለዉና በስዕል፤ በፊልም፤ በፎቶ፤ እንዲሁም በተለያዩ ሶሻሊዝምን አንፀባሪቂ ቅርጻ ቅርጾች የተደገፈዉን ዓዉደ ርዕይ እንቃኛለን ።

Deutschland Ausstellung Things Fall Apart im Bayreuther Iwalewahaus

ለአሳ ማጥመጃ ከሶቭየት ኅብረት ለአንጎላ በስጦታ መልክ የተሰጠ፤ በአሁኑ ወቅት ሰሜናዊ ሉዋንዳ ባሕር ዳርቻ ቆሞ እየዛገ ያለ ግዙፉ መርከብ


የቀዝቃዛዉ ጦርነት አዉድማ የነበረችዉ አፍሪቃ የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለምን ካራመዱት ሃገራት በተለይም ከሶቭየት ኅብረት ጋር የመሰረተችዉ ጋብቻ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ባይዘልቅም፤ ትቶት ያለፈዉ ጠባሳ አሁንም በአፍሪቃዉያኑ ሃገራት ይታያል። በሊሳቦን ፖርቱጋልና፤ በሉዋንዳ አንጎላ እየተዘዋወረ የሚሠራዉ ወጣቱ አንጎላዊዉ ፎቶግራፍ አንሽ ኪሉዋንጂ ኪአ ሄንዳ «Kiluanji Kia Henda» በዓዉደ ርዕዩ ያቀረበዉ ሶቭየት ኅብረት ለአንጎላ በስጦታ መልክ የተሰጠችዉና፤ በአሁኑ ወቅት ሰሜናዊ ሉዋንዳ ባሕር ዳርቻ ቆሞ እየዛገ ያለ ግዙፉ የአሳ ማጥመጃ መርከብ ፎቶን ነዉ። «ካልርል ማርክስ ሉዋንዳ» የሚል ስያሜዉ አሁንም በመርከቡ ላይ እንደሚነበብ የሚጠቁመዉ የኪሉዋንጂ ሦስት ፎቶዎች በዓዉደ ርዕዩ መግብያ ላይ የሚታይና፤ የኤግዚቢሽኑ ጥቅል ማሳያ ሆኖ የተወሰደ ነዉ።

« ይህ በእግዚቢሽኑ መጀመርያ ላይ የምታዩት የኪሉዋንጂ ኪአ ሄንዳ ፎቶ ለዚህ ዓዉደ ርዕይ የተሰጠዉን «Things Fall Apart» የተሰኘዉን ስያሚና ከስሙ በስተጀርባ ለማስተላለፍ የተፈለገዉን ኃሳብ አጠቃሎ የያዘ ነዉ። ይህ የአሳ ማጥመጃ ግዙፍ መርከብ በ 1980ዎቹ ሶቭየት ኅብረት ለአንጎላ በስጦታ መልክ ያበረከተችዉና ብዙም ጥቅም ሳይሰጥ በሰሜናዊ ሉዋንዳ ባህር ጠረፍ ላይ የቆመ በመዛግ ላይ ያለ መርከብ ነዉ። የዚህ መርከብ ፎቶ ፤ እንደሚያሳየዉ ርዕዮተ ዓለሙ መፈረካከሱን ፤ እንድያም ሆኖ ግን በአፍሪቃ ከተሞች ይህን ዘመን የሚያስታዉስ ጥላ አሁንም መኖሩን ነዉ።»
በባይሮይት ዩንቨርስቲ የማስትሬት ዲግሪዉን በመስራት ላይ የሚገኘዉ ጀርመናዊ ሉካስ ሄገር በዕለቱ ዓዉደ ርዕዩን ለመመልከት ለቀረበዉ ታዳሚ ገለፃ አድርጎአል።
ከቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ለአንጎላ የተበረከተዉ ግዙፍ የአሳ ማጥመጃ መርከብ በወጣቱ አንጎላዊ ፎቶግራፍ አንሺ ተሰብሮና አሁንም ሰሜናዊ ሉዋንዳ ባህር ዳርቻ ላይ በመዛግ ላይ ያለዉ ፎቶ፤ በዓዉደ ርዕዩ የቀረበ ስዕላዊ ጥበብ ነዉ ያሉት የኤግዚቢሽን ማዕከሉ ምክትል ዳይሬክተር ናዲን ዚገርት በበኩላቸዉ፤

Deutschland Ausstellung Things Fall Apart im Bayreuther Iwalewahaus

ፓትሪስ ሉሙምባ በስዕል


« ስራዉ እጅግ ጥበባዊ ነዉ። ምክንያቱም በዚህ ፎቶግራፍ ስለተንኮታኮተዉና በርግጥም እዉን ስላልሆነዉ የአፍሪቃ ሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ህልምን ቁልጭ አድርጎ በማሳየቱ ነዉ። ይህ እየዛገ ያለ የተገነጣጠለ ግዙፍ መርከብ፤ በማኅበረሰቡ ላይ ከባድ ሽክም ያሳደረ እስካሁንም ሸክም ሆኖ ያለ፤ በሌላ በኩል ማኅበረሰቡ ያልተሳካዉን ሕልሙን በእዉን የሚያይበት ጭምርም ነዉ። »


ከረጅም የፀረ-ቅኝ ግዛት ወረራ በኋላ በጎርጎረሳዉያኑ 1975 ዓ,ም ከፖርቱጋል ቅኝ ግዛት የተላቀቀችዉ አንጎላ፤ የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለም በማራመድ ወዛደራዊ ዓለም አቀፋዊነትን እዉን ለማድረግ ሶቭየት ኅብረትን ብቻ ሳይሆን ኪዩባንም እንደ አንድ ትልቅ አርዓያ በመዉሰድ 15 ዓመታት ሶሻሊዝምን እዉን ለማድረግ ጥረት ስታደርግ መቆየትዋን ናዲን ዚገርት ተናግረዋል።
የአንጎላ የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ ከአምስት ዓመት በኋላ በጎርጎረሳዉያኑ 2007 ዓ,ም ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አንጎላ የተጓዘችዉ ደቡብ አፍሪቃዊትዋ ፎቶግራፍ አንሽ Jo Ractliffe በአንጎላ ደቡብ አፍሪቃ ድንበር ላይ የነበረዉ የምስራቅና የምዕራቡ ዓለም የዉክልና የርስ በርስ ጦርነት ትቶት ያለፈዉን ጠባሳ የሚያሳይ ፎቶግራፍን በዓዉደ ርዕዩ አቅርባለች። ከRactliffe ፎቶዎች መካከል በተለይ ታሪካዊ ግኝት የተባለለት የግንብ ላይ ጥንታዊ የፎቶ እጅ ሥራ ይገኝበታል። ፎቶግራፉ በአንጎላ ደቡብ አፍሪቃ ድንበር ላይ ለነበረዉ የዉክልና ጦርነት ሰበብ ናቸዉ የተባሉትን ግለሰቦች የፊት ጉርድ ፎቶግራፍ ምስልን የያዘና ግንብ ላይ ተቀረፀ ወይቦ የሚታይ ነዉ። በፎቶዉ የቀድሞ የሶቭየት ኅብረት መሪ ሊዮኒድ ብሬዥኔቭ፤ የአንጎላ ፀረ-ቅንኝ ግዛት መሪ ተብለዉ የሚታወቁት ፕሬዚዳንት አጉሽቲኖ ኔቶና፤ የቀድሞዉ የኪዩባ ፕሬዚደንት የፊደል ካስትሮ በአንድ ላይ ተደርድረዉ ይታያል። ሉካስ ሄገር ይህ በእጅ የተሳለዉ ምስል በ 70ዎቹ መጨረሻ ላይ መቀረፁን ገልጾአል።

Senegal Dakar Skulptur Afrikanische Renaissance Renaissance africaine

በሰሜን ኮርያ ዳካር ላይ የተገነባዉ የመዳብ ግዙፍ ሐዉልት


«በግድግዳ ላይ ምስላቸዉ ተስሎ የሚገኙት የቀድሞዎቹ የመንግስታት መሪዎችን ካስትሮ ብሬዥኔቭና ፤ኔቶን ያየ አብዛኛዉ ጀርመናዊ ለምን የነዚህ ሰዎች ምስል አንድ ላይ ሆኖ ተገኘ? ለምንስ ግድግዳ ላይ ምስላቸዉ ተሳለ ብሎ ይጠይቃል ብዬ አምናለሁ። ከዚህ የምስል ጀርባ ብዙ ታሪክን እናገኛለን። ለምሳሌ አንጎላ ከፖርቱጋል ቅኝ ግዛት ነጻ መሆንን፤ በዝያን ጊዜ በአንጎላ ከሚታየዉ የተለያዩ ጭቆናዎች ነጻ ለመሆን የሚደረግ እንቅስቃሴን፤ የአንጎላ ነጻነት ህዝባዊ ንቅናቄ ፓርቲ ማለት «MPLA » ከቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመንና ከሶቭየት ኅብረት ጋር የነበረዉን ግንኙነት እንዲሁም ከካፒታሊስቱ ዓለም ጋር የነበረዉን ሁኔታ ሁሉ ማየት ይቻላል። ሌላዉ የቀዝቃዛዉን ጦርነት ወቅት ኪዩባና ደቡብ አፍሪቃ በአንጎላ በነበረዉ ጦርነት እጃቸዉን ማስገባታቸዉም ነዉ። በዚህ ጦርነት ሶቭየት ኅብረት ከአንጎላዉ የ«MPLA» ፓርቲ ወገን በመቆም ወታደራዊ ኤኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ድጋፍን ማድረግዋ ይታወሳል። »


ከጎርጎረሳዉያኑ 1964 እስከ 1982 ዓ,ም ሶቭየት ኅብረትን የመሩት የሶቭየት ኅብረት የኮሚስት ፓርቲ ሊቀመንበር ሊዮኒድ ኤሊች ብሬዥኔቭ ለአፍሪቃዉያን መንግሥታት ያደረጉት ንግግር ነበር። ፤በደቡባዊ ጀርመን «ኤቫሌቫ ሃዉስ» በተሰኘዉ የባይሮይት ከተማ ዩንቨርስቲ አካል በሆነዉ ኤግዚቢሽን ማዕከል የታየዉን ዓዉደ ርዕይ ለመጎብኘት ወደ ማዕከሉ ዉስጥ ሲገባ ራቅ ካለ የኤግዚቢሽኑ ክፍሎች የሚሰማ ድምፅ ነዉ። ከብሬዥኔቭ ድምፅ ሌላ መፈክሮች የሶሻሊዝም ስርዓት አራማጅ መንግሥታት የአፍሪቃ ሃገራትን ሲጎበኙ ይደረግላቸዉ የነበረዉ አቀባበል ፤ ሙዚቃና በዓዉደ ርዕዩ የተለያዩ ክፍሎች የሚሰማ ድምጽ ነዉ።

Deutschland Ausstellung Things Fall Apart im Bayreuther Iwalewahaus

በግድግዳ ላይ ምስላቸዉ ተስሎ የሚገኙት የቀድሞዎቹ የመንግስታት መሪዎችን ካስትሮ ፤ ኔቶና ብሬዥኔቭ


ከኮንጎ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ከሉቡምባሺ የመጣዉ ሰዓሊ ትሺንቡምባ ካንዳ ማቱሉ፤ በዓዉደ ርዕዩ በኮንጎ በ 60 ዎቹ ዓመታት ታዋቂ ፖለቲከኛ የነበሩትን የኮንጎ የመጀመርያ ጠቅላይ ሚኒስትር የፓትሪስ ሉሙምባን ፖሊታካዊ እንቅስቃሴ የሚያንፀባርቅ ስዕልን ነዉ ያቀረበዉ። ምንም እንኳ ኮንጎ የማርኪሲዚም ሌኒሲዝም ርዕዮትን በእዉን ያላራመደች ሃገር ብትሆንም የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓትሪስ ሉሙምባ የሶሻሊዝም ፖለቲካ አቀንቃኝና በወቅቱ ከሶሻሊስት ሃገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንደነበራቸዉ ይታወቃል። የኤግዚቢሽን ማዕከሉ ምክትል ዳይሬክተር ናዲን ዚገርት፤ የቀረቡት ሁለት ስዕሎች ይላሉ፤
« ከቀረቡት ሁለት ስዕሎች መካከል አንደኛዉ ሉሙምባ ከቅኝ ግዛት ለተላቀቀዉ የኮንጎ ሕዝብ ንግግራ ሲያደርጉ ነዉ የሚያሳየዉ ። ይህ የሉሙምባ ንግግር እጅግ እጅግ ታዊቂና ታሪካዊ ነዉ። በስዕሉ ላይ ሉሙምባ ለሕዝቡ ንግግር ሲያደርጉ ከሕዝቡ በስተጀርባ የኮንጎ ቅኝ ገዢ የቤልጂየሙ ንጉስ የባልደዊን King Baudouin ምስል ይታያል። ንጉስ ባልደዊን በስዕሉ ላይ ፊታቸዉን ጭፍግግ አድርገዉ ነዉ የሚታዩት። ሁለተኛዉ ስዕል ላሉሙምባ ከሞቱ በኃላ በመሆኑ የሚታየዉ ሐዉልት ብቻ ነዉ። ሰዓሊዉ በዚህ ሁለት ስዕሎች ማሳየት የፈለገዉ የሉሙምባን የፖለቲካ ሂደትና ከሞቱ በኋላ ያለዉን ሁኔታ ነዉ»
እንደ፤ አንጎላ፤ ጋና፤ ሞዛንቢክና ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ሃገራት፤ በቀዝቃዛዉ የዓለም ጦርነት የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉትን የምስራቅ ዓለሙን ሃገራትን በመደገፍ ከካፒታሊዝሙ ዓለም ለመላቀቅ ፀረ- ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴን አድርገዋል። የኢትዮጵያ ደም እንዳለበት የሚነገረዉ የሩስያ የሥነ-ጽሁፍ አባት፤ የአሌክሳንደር ሰርጌ ቪች ፑሽኪን ሃገር ሶቭየት ኅብረት፤ ከኢትዮጵያ ወዳጅነት የጀመረችዉ ከዳግማዊ አጼ ሚንሊክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንደሆን ታሪክ ያሳያል። አጼ ኃይለስላሴም በዘመነ ስልጣናቸዉ ከአራት ጊዜ ላላነሰ ሩስያን ጎብኝተዋል። የኢትዮጵያና የሶቭየት ኅብረት

Deutschland Ausstellung Things Fall Apart im Bayreuther Iwalewahaus

ለ10ኛዉ አብዮት በዓል ከቀድሞዋ ከምስራቅ ጀርመን የተበረከተዉና በሄሪሽ ሆኒከር የተመረቀዉ የካርል ማርክስ ሐዉልት

ግንኙነት ይበልጥ በጥብቅ የተጠናቀረዉ ግን፤ ዓለም በሁለት ርዕዮተ ዓለም በተከፈለበት በቀዝቃዛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት ነዉ። የአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ከተገረሰሰና በምትኩ ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ የደርግ መንግሥት ከአሜሪካ ድግፍን ባለማግኘቱ ወደ ሩስያ ወዳጅነቱን ማጠናከሩን ጀመረ። የዚያን ጊዜዉ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ሶቭየት ኅብረትን በመጎብኘት ከወቅቱ መሪ ከሊዮኒድ ብሬዥኔቭ ጋር ከፍተኛ የወንዳጅነትን ዉልን በመፈፀም በአፍሪቃ እጅግ ከፍተኛ ጦር ሰራዊትን መገንባት ያስቻለ የጦር ሰራዊት ርዳታ ተደርጎላቸዋል። ሃገራቸዉ በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሶማልያ የደረሰባትንም ወረራ ሶቭየት ኅብረትን ጨምሮ የሶሻሊዝም መርኅን አራማጆቹ የመንና ኪዮባ ከኢትዮጵያ ጋር አጋርነታቸዉን በማሳየት ጦርነቱን ድል አድረገዋል። ሶቭየት ኅብረት ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ርዳታን ብቻ ሳይሆን የማርክሲስት ርእዮተ ዓለምን በማስፋፋት በኪነ-ጥበብና ሥነ-ጥበብረገደ ከፍተኛ ተፅኖን አድርጋለች። ሶቭየት ኅብረት ለሌሎች የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለምን ለሚከተሉ አፍሪቃ ሃገራት የነጻ ትምህርት እድልን እንደምትሰጠዉ ሁሉ ከኢትዮጵያ በሽዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በየዓመቱ ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት የነጻ ትምህርት እድልን በማግኘት ይጓዙ ነበር።


« ኮንጎን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ታዋቂዉ የኮንጎ ፖለቲከኛ ገና ስልጣን ከመያዛቸዉ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በጎርጎረሳዉያኑ 1961 ዓ,ም መጀመርያ ላይ በመገደላቸዉ፤ ሉሙምባ በሕይወት ዘመናቸዉ ላደረጉት የፀረ-ቅኝ ግዛትና ፀረ-ኤንፒሪያሊዝም ትግል ማስታወሻ እንዲሆን ሲባል፣ ሞስኮ የሚገኘዉ «የሕዝብ ወዳጅነት ዩንቨርስቲ » በስማቸዉ «ፓትሪስ ሉሙምባ ዩንቨርስቲ» ተብሎ ተሰየመ። በዚህ ዩንቨርስቲ በተለይ ከአፍሪቃ ከእስያና ከደቡብ አሜሪካ የመጡ እጅግ በርካታ ተማሪዎች ተመርቀዋል።»
በወቅቱ የዩንቨርስቲዉ የትምህርቱ ስርዓት እንዲሁም በተቋሙ የነበሩት አፍሪቃዉያን ተማሪዎች ሁኔታ ሁለት ገጽታ ያለዉ ነበር፤ ይላሉ ዚገርት በመቀጠል፤

Deutschland Ausstellung Things Fall Apart im Bayreuther Iwalewahaus

የቀድሞዉ ምስራቅ ጀርመን መሪ ኤሪሽ ሆኒከር በ1970ዎቹ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ የተከበረዉን 10ኛ የአብዮት በዓል በማስመልከት ያደረጉትን ጉብኝት በጋዜጣ ዘገባ


«በመጀመርያ ሶቭየት ኅብረት ይህን ዩንቨርስቲ በሉሙምባ ስም መሰየሟ በአፍሪቃዉያኑ ሃገራት የምታራምደዉን ወዛደራዊ ዓለማቀፋዊነትና የወንድማማችነት መርህን ለማጠናከር ስትል ነበር። በሌላ በኩል ለትምህርት የመጡት ወደ ሶቭየት ኅብረት የመጡት ተማሪዎች ሶቭየት ኅብረት ከመጡ በኋላ በማኅበረሰቡ ተቀባይነትን አለማግኘታቸዉ ነበር። በሃገሪቱ የዘር ጥላቻ ይታይ ነበር። ይህን ተከትሎ በዩንቨርስቲዉ የነበሩት የዉጭ ሃገር ተማሪዎች በሃገራችን ሌላ አማራጭ በማጣታችን ነዉ ወደዚህ የመጣነዉ ሲሉ ንቅናቄ መጀመራቸዉ ተዘግቦአል።»
በቀድሞ ጊዜ በሶቭየት ኅብረት የነበሩ አፍሪቃዉያን ተማሪዎች ፤በሞስኮ ክሪምሊን ቀዩ አደባባይ፤ እንዲሁም በፓትሪስ ሉሙምባ ዩንቨርስቲ መግብያ ላይ የተነስዋቸዉ ፎቶግራፎች ፤ በዓዉደ ርዕዩ ለእይታ የቀረቡ ናቸዉ። ሌላዉ በቀድሞ ጊዜ በርካታ አፍሪቃዉያን ተማሪዎች ሞስኮ ዉስጥ መሞታቸዉና ፤ የሞቱበት ምክንያት አለመጣራቱን የሚያሳይ ዘገባም ይገኛል። ለምሳሌ አንድ የጋና ተወላጅ መንገድ ላይ በበረዶ ላይ ሞቶ መገኘቱን በተመለከ ፖሊስ ሟቹ ምናልባትም በመጠጥ ምክንያት መንገድ ላይ በቅዝቃዜ መሞቱን ፤ አልያም በዘር ጥላቻ ተገድሎ ሊሆን ይችላል የሚል መላምት የሰጠበት የፖሊስ መግለጫም ይገኛል። ከቀረቡት መረጃ ፎቶዉች አስገራሚዉ ግን ይላሉ የኤግዚቢሽን ማዕከሉ ምክትል ዳይሬክተር ናዲን ዚገርት፤


« በዓዉደ ርዕዩ ከቀረቡት ፎቶግራፎች መካከል አስገራሚ በ 1950ዎቹ መገባደጃ ከስታሊን ዘመነ መንግስት በኋላ የመጀመርያ የተባለ በሞስኮ ላይ የተደረገዉ የተቃዉሞ ሰልፍን የሚያሳየዉ ፎቶግራፍ ይገኝበታል። ይህ ፎቶ ለመጀመርያ ጊዜ መብትን በግልጽ በመጠየቅና ቅሬታን በማስተጋባት ሰልፈኞች በሞስኮ አደባባይ የወጡበት የመጀመርያ ንቅናቄን በማሳየቱ ታሪካዊ ያደርገዋል።»

Deutschland Ausstellung Things Fall Apart im Bayreuther Iwalewahaus

ዋጋዱጉ የፊልም ማዕከል የሶሻሊዝም ፕሮፖጋንዳ ማሳያም ነበር


ሶቭየት ኅብረት ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ያላትን ተሰሚነት በማገናዘብ የቭላድሚር ኤሊች ሌኒን ሐዉልትን በስጦታ አበርክታ አዲስ አበባ በሚገኘዉ የአፍሪቃ ኅብረት መሰብሰብያ አዳራሽ ፊት ለፊት እንዲቆም ተደርጎም ነበር። ይህ የሆነዉ አፍሪቃ ወደ ሶሻሊዝሙ ዓለም እንድትገባ ለመገፋፋት የተደረገ እንቅስቃሴ ነበር። ይህ ሐዉልት ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አገዛዝ መገርሰስ ጋር ተያይዞ ተነቅሎ መዉደቁም ይታወቃል። በሌላ በኩል የቀድሞ የምስራቅ ጀርመን መንግሥት ያሠራዉና በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ዩንቨርስቲ ቆሞ የሚገኘዉ የካርል ማርክስ ሐዉልት በፎቶግራፍ መልክ በዓዉደ ርዕዩ የቀረበ የሶሻሊዝሙ ርዕዮተ ዓለም ቅሪት ነዉ። የባይሮይት ዩንቨርስቲ የማስትሪት ዲህሪዉን በመስራት ላይ የሚገኘዉ ጀርመናዊዉ ሉካስ ሄገር የቀድሞዉ ምስራቅ ጀርመን መሪ ኤሪሽ ሆኒከር በ1970ዎቹ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ የተከበረዉን 10ኛ የአብዮት በዓል በማስመልከት ያደረጉትን ጉብኝትን በተመለከተ ያካሄደዉ ጥናት፤ የፎቶግራፎችና የጋዜጦች ስብስብ ሌላዉ የዓዉደ ርዕዩ አካል ነበር።


« በመጀመርያ በኢትዮጵያ ስለነበረዉ ቀይ ሽብር ጉዳይ ያየሁት በጋዜጣ ላይ በስዕል መልክ ነዉ። ከዝያ የኤሪሽ ሆኒከርና የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ፎቶ አገኘሁ። እዚሁ ጋዜጣ ላይ የካርል ማርክስ መታሰብያ ኃዉልትንም አየሁ። በዝያን ጊዜ ምሥራቅ ጀርመን ዉስጥ የወጣዉ ዘገባ ኤሪሽ ሆኒከር ለአስረኛዉ የኢትዮጵያ አብዮት በዓል አዲስ አበባ ላይ ሲገኙ ይህንን የካርል ማርክስ ሐዉልትን መመረቃቸዉን ያሳያል። በምስራቅ ጀርመን ስለኢትዮጵያ የወጣዉ ዘገባ ጥሩ ሆኖ በመቅረቡ በኢትዮጵያ ምንም አይነት ችግር መኖሩ አይታይም። ሁለቱ ሃገራት የሰመረ ግንኙነትም ተጠቅሶአል። በሌላ በኩል የኤሪሽ ሆኒከር የኢትዮጵያን ጉብኝት አስመልቶ በምዕራብ ጀርመን ስለኢትዮጵያ የወጣዉ ታሪክ ከምስራቅ ጀርመኑ የተለየ መሆኑ ነበር። በዘገባዉ መሰረት በሃገሪቱ ስለተከሰተዉ አስከፊ ረሃብ፤ አሰቃቂ ዉ የቀይ ሽብር ታሪክ የቀረበበት ተፃራሪ ታሪክ ነዉ። »
በዚህ ሁለት ጀርመኖች ብቻ በሁለት ርዕዮተ ዓለም ተከፍሎ የነበረዉን ዓለም ቁልጭ አድርጎ ማየት ይቻላል ሲል ሉካስ ሄገር ተናግሮል።

Deutschland Ausstellung Things Fall Apart im Bayreuther Iwalewahaus

በቀድሞ ጊዜ አፍሪቃዉያን ተማሪዎች በሞስኮ ቀዩ አደባባይ ላይ


በዓዉደ ርዕዩ እንደተመለከተዉ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የሶሻሊስት አመራር ዘመን 10ኛዉ የአብዮት በዓል በድምቀት ሲከበር የወዛደራዊ ዓለማቀፋዊነት፤ የወንድማማችነት መገለጫ ስጦታ ከምስራቅ ጀርመን ብቻ ሳይሆን ከሰሜን ኮርያም ግዙፍ ስጦታ ተበርክቶዋል። ይኸዉም አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋ የሚገኘዉ ግዙፉ የትግላችን ሐዉልት ነዉ። ሰሜን ኮርያ በአፍሪቃ ሃገራት ስለአቆመቻቸዉ የተለያዩ ሐዉልቶች ላይ ጥናት የሚያደርገዉ የደቡብ ኮርያዉ ተመራማሪ ዋንጆን ቼ«Onejoon Che» የተለያዩ ስራዎች በፎቶግራፍ ተደግፈዉ በዓዉደ ርዕዩ ላይ ቀርበዋል። ዋንቼን ቼ በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት በተለይ በሴኔጋል፤ ናሚቢያና ቦትስዋና ዉስጥ በሰሜን ኮርያ የተሰሩ የቀድሞ የፖለቲካ ባስልጣን ምስል ያለበት የመዳብ ግዙፍ ኃዉልቶችን፤ እንዲሁም የቀድሞ አልያም አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙ የአፍሪቃ ፕሬዚዳንት ምስል ያሉበት ግዙፍ ኃዉልቶች ጎብኝቶአል፤ ሃዉልቱን በተመለከተ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ያላቸዉን አስተያየትም አሰብስቦአል። በዓዉደ ርዕዩ ላይ በፎቶ እና በአነስተኛ ቅርጽ መልክ ከቀረቡት ምስሎች መካከል፤የአዲስ አበባዉ ድላችን ሐዉልት ፤ ዊንድ ሁክ ናሚቢያ ላይ የፀረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ እንዲታሰብበት የቆመዉ የጀግኖች መታሰብያ ይገኛል። ሰሜን ኮርያ ለመጀመርያ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ የገነባችዉ ትግላችን የተሰኘዉ ኃዉልት ከአዲስ አበባ በኋላ በአፍሪቃ ከ20 በላይ ሃገራት ዉስጥ መገንባቱም ተገልፆአል።


«ይህንን እጅግ ግዙፍ ሐዉልት ፕሬዚዳንት ዋዴ ዳካር ላይ አስገንብተዉታል። በቦትስዋና መዲና ጋቦሮኔ ላይ የተገነባዉ «Three Dikgosi Monument» የተሰኘዉ ግዙፉ የመዳብ ኃዉልት እንዲሁም ናሚቢያ ላይ ቆሞ የሚገኘዉ ስም ዓልባዉ ወታደር/የነጻነት ሐዉልት የተሰኙት ተጠቃሽ ናቸዉ። እነዚህን ሐዉልቶች ስንመለከት የሚያስገርዉ ነገር የሰሜን ኮርያዉ የሶሻሊዝም ነፀብራቅ ፤ ወይም የሶሻሊዝሙ ነባራዊነት አፍሪቃ አህጉር ላይ እስከ አሁኑ ጊዜ ቆሞ የሚገኝ ከሶሻሊዝሙ ርዕዮተ ዓለም የተገኘ ዉርስ መሆኑ ነዉ። ሌላዉ አስገራሚ ነገር ደግሞ ይኸዉ ሐዉልት በብዙ የአፍሪቃ ሃገራት መንግሥታት አሁንም መወደዱ ነዉ።»

Deutschland Ausstellung Things Fall Apart im Bayreuther Iwalewahaus

በደቡባዊ ጀርመን ባይሮይት ከተማ «ኤቫሌቫሃዉስ» የእግዚቢሽን ማዕከል


ዩጎዝላቪያ በወቅቱ ምስራቁና የምዕራቡ ዓለም የሚያካሂዱትን አይነት ፖሊቲካ ሳይሆን የገለልተኛ ሃገራት ፖለቲካን በማራመድ የራስዋን ወገንተኛ ሃገራት በማሰባሰብ ትንቀሳቀስ እንደነበርና ከነዚህ ሃገራት መካከል ደግሞ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ኢትዮጵያ አንድዋ መሆንዋን የሚያሳይ ፎቶ መኖሩን ዚገርት ተናግረዋል።


የአፍሪቃ ፊልም መዲና ዋጋዱጉ በሶሻሊዝሙ ርዕዮተ ዓለም ዘመን በማሊዉ ወታደራዊ መኮንን ቶማስ ሳንካራ ትዕዛዝ የሶቭየት ኅብረት የፕሮፖጋንዳ ፊልሞች የሚታይበት መድረክም እንደነበር በቀረብዉ ዓዉደ ርዕይ ታይቶአል። በኢትዮጵያ የነበረዉን የቀይ ሽብር አብዮት በተመለከተ በፕሮፊሰር ሃይሌ ገሪማ የተሰራዉ «ጤዛ ፊልም ጨምሮ ሁለት በኢትዮጵያዉያን የተሰሩ ዘጋቢ ፊልሞች ታይተዋል። በለንደን ሲታይ ከርሞ በጀርመኑ መድረክ ወደ አራት ወራት የሆነዉና ወደ ቡዳፔስት ሃንጋሪ ለመጓዝ ዝግጅት ላይ ያለዉ የአፍሪቃ ሶሻሊዝምንና በአህጉሪቱ ትቶት ስላለፈዉ ጠባሳ የሚተርከዉ ዓዉደ ርዕይ በጎተ ተቋም በኩል በአፍሪቃ ሃገራት እንዲቀርብ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቶአል።


አዜብ ታደሰ


አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic