1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 19፣2016 የዓለም ዜና

Negash Mohammedሐሙስ፣ መጋቢት 19 2016

-የትግራይና የአማራ ክልላዊ መስተዳድሮች የቃላት እሰጥ አገባ አገርሽቷል።የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ባለፈዉ ሳምንት የአማራ ክልል «በኃይል የያዛቸዉን የትግራይ ሥፍራዎች የአማራ እንደሆኑ በማስተማሪያ መፅሐፍ አትሟል በማለት ወቅሶ ነበር።የአማራ ክልል ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ የትግራይ ክልልን መግለጫ አሳሳች፣ካሐዲና ጠብ ጫርነትን የተሸከመ» በማለት ነቅፎታል።-የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አል ሸባብ ማዕከላዊ ሶማሊያ ዉስጥ በሁለት አካባቢዎች በከፈተዉ ጥቃት 53 የመንግስት ወታደሮችን መግደሉን አስታወቀ።የሶማሊያ መንግስት ባለስጣናት ወታደሮች መገደላቸዉን ቢያምኑም ብዛቱን አልጠቀሱም።

https://p.dw.com/p/4eEZy

 

ባሕርዳር-የአማራ ክልል ምላሽ ለትግራይ ወቀሳ

የትግራይና የአማራ ክልሎች የቃላት እንኪያ ሠላንቲያ እንደ-አዲስ አገርሽቷል።የአማራ ክልላዊ መንግስት ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር «ሐገሪቱን ከቋሚ ቀዉስ የሚዳርጉ» ካላቸዉ ተግባራት እንዲቆጠብ አሳስቧል።የትግራይ ጊዚያዊ ክልላዊ መንግስት ባለፈዉ ሳምንት የአማራ ክልል በኃይል የተቆጣጠራቸውን “የትግራይ አካባቢዎች በትምህርት ስርዓቱ አካትቷል” በማለት  ድርጊቱን ኮንኖ በአስቸኳይ እርማት እንዲደረግበት ጠይቆ ነበር፡፡የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግስት «ሆን ብሎ የጠብ ጫሪነት ድርጊት ይፈፅማል» በማለትም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከስሷል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዛሬ ባወጣው አፀፋ መግለጫ “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከመፈረሙ በፊት በስራ ላይ የዋሉ  መጽሐፍትን ምክንያት በማድረግ---

በአማራ ክልል ላይ ጥቃት ለመፈፀም የማይመለስ የጠብ ጫሪነት መግለጫ ነው” በማለት አጣጥሎ ነቅፎታል።

መግለጫዉ አክሎም “ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር---- ከአጓጉል የካርታ ፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጣና የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር እንመክራለን” ብሏል፡፡

“በአማራ ክልል የመማሪያ መጽሐፍት ላይ የተሳሳተ ካርታ ተሰርቷል ሲል የትግራይ ክልል ያወጣውን መግለጫም፣ የአማራ ክልላዊ መንግስት « ወደ አማራ ክልል ተካትተዋል ያላቸው አካባቢ፣ የህዝቦችን ታሪካዊ ዕውነትን፣ ተጨባጭ ማስረጃን እና ነባራዊ ሐቅን የካደ፣ አሳሳሰችና የጠባ ጫሪነት ፍላጎትን የተሸከመ ነው» በማለት ተቃዉሞታል።

መግለጫው፣ ሰሞኑን የትግራይ ኃይሎች ራያ አላማጣ ቀበሌዎች በነዋሪዎች ላይ ግድያና ወከባ አድርሰዋል ሲልም የትግራይ ክልልን ከስሷል።የባሕርዳሩ ወኪላችን ዓለምነዉ መኮንን እንደዘገበዉ የአማራ ክልል በፅሑፍ ሥላወጣዉ ረምጅም መግለጫ የአማራም ሆነ የትግራይ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎችን  አስተያት ለማካተት ያደረገዉ ሙከራ አልተሳካለትም።

 

ባሕርዳር-የሰሜን ጎጃም ዞን ግጭት ያስከተለዉ ችግር

 

አዲስ በተመሠረተዉ በሰሜን ጎጃም ዞን የሚደረገዉ ግጭት የአካባቢዉን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ማወኩን የዞኑ አስተዳዳሪ አስታወቁ።የሰሜን ጎጃም ዞን  አስተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ «ወቅታዊ የሠላም እጦት» ባሉት ግጭት ምክንያት የዞኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምግባራትን ተደናቅፈዋል።በተለይ ዞኑ ዉስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እስካሁን አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም።

አቶ አሰፋ አክለዉ እንዳሉት የአውራ ጎዳናዎች ግንባታ ተቋርጠዋል፤ መድኃኒቶችንና የሕክምና ቁሳቁሶችን ማዘዋወር አልተቻለም፤ የዞኑ የአደረጃጀት መዋቅሩም ጫና ተፈጥሮበታል።ዘንድሮ በይፋ ሥራ የጀመረዉ ሰሜን ጎጃም ዞን 10 ወረዳዎችን ያስተናብራል።የዞኑ አስተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን እንዳሉት በአብዛኞቹ የዞኑ ወረዳዎች አንፃራዊ ሰላም እየተፈጠረ በመሆኑ የተቋረጡ ስራዎችን ለማስጀመር ተዘጋጅተዋል።የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ በቅርቡ እንዳስታወቀዉ በክልሉ ዘንድሮ ከተመዘገቡ 6.2 ሚሊዮን ተማሪዎች 2.6 ሚሊዮኑ እስካሁን አይማሩም።

 

ሞቃዲሾ-አሸባብ ከ50 በላይ ወታደር ገደልኩ አለ

 

የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ባለፈዉ ማክሰኞ ማታ በሁለት ሥፍራዎች በከፈተዉ ጥቃት 53 የመንግስት ወታደሮች መግደሉን አስታወቀ።ከሁለቱ ጥቃቶች የመጀመሪያዉ የተሰነዘረዉ ማዕከላዊ ሶማሊያ ዉስጥ በሚገኝ በአንድ የጦር ሠፈር ላይ ነዉ።ሁለተኛዉ ጥቃትም እዚያዉ ማዕከላዊ ሶማሊያ  ሐራድሕሬ በተባለዉ ከተማ ላይ በሠፈረዉ የመንግስት ወታደሮች ላይ ያነጣጠረ ነበር።የሶማሊያ መንግስት ጦር ሐራድሬን ከአሸባብ ዕጅ ያስለቀቀዉ በቅርቡ ነበር።አሸባብ እንደሚለዉ በሁለቱ ጥቃቶች 53 ወታደሮች ተገድለዋል።የጀርመኑ ዜና አገልግሎት DPA በሥም ያልጠቀሰዉ የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚንስቴር አንድ ቃል አቀባይ በጥቃቱ  «ከሁለታችንም ወገን በደረዘን የሚቆጠሩ ተዋጊዎች ተገድለዋል» ከማለት ሌላ ትክክለኛዉን ቁጥር አልተናገረም።

 

ካይሮ-የእስራኤልና የፍልስጤም ታጣቂዎች ዉጊያ

 

የእስራኤል ጦርና ጋዛ ዉስጥ የሸመቁት የፍልስጤም ታጣቂዎች አል ሺፋ በተባለዉ ሆስፒታል አጠገብ በቅርብ ርቀት ሲዋጉ ነዉ የዋሉት።የእስራኤል ጦር ካንድ ሳምንት በፊት የወረረዉን የአል ሺፋ ሆስፒታል ሕንፃን ዛሬም እየተቆጣጠረ መሆኑን አስታዉቋል።ሮይተርስ ዜና አገልግሎት እንደዘገበዉ የእስራኤል ጦር ሆስፒታሉን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ 200 ታጣቂዎችን መግደሉን አስታዉቋልም።የጋዛ የጤና ሚንስቴር ግን የእስራኤል ጦር ቁስለኞችና በሽተኞችን ሕክምና በማያገኙበት በሆስፒታሉ የአስተዳደር ቢሮዎች ዉስጥ በማገቱ ቢያንስ አምስት «በሽተኞች ሞተዋል» ብሏል። እስራኤልና ምዕራባዉያን መንግስታት ባሸባሪነት የፈረጇቸዉ ሐማስና እስላዊ ጂሐድ ዛሬ እንዳስታዉት ታጣቂዎቻቸዉ አል ሺፋ ሆስፒታል አጠገብ ከእስራኤል ወታደሮችና ታንኮች ጋር እየተዋጉ ነዉ።የፍልስጤም ባለስልጣናት እንደሚሉት የእስራኤል ጦር ጋዛን ዉስጥ የገደላቸዉ ፍልስጤማዉያን ቁጥር ከ32 ሺሕ 500 በልጧል።ሐማስ ባለፈዉ መስከረም እስራኤልን ወርሮ 1140 ሰዎች ገድሏል።ካገታቸዉ ሰዎች 130ዉ አሁንም አልተለቀቁም።

 

ዤኔቭ-የሐይቲ ወንበዴዎች የሚገድሉት ሰዉ ቁጥር እየጨመረ ነዉ

የሐይቲ ወርሮ በሎች የሚገድሉት ሰዉ ቁጥርና የሚያጠፉት ሐብት መጠን እየበረከተ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።የድርጅቱ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ፅሕፈት ቤት እንዳስታወቀዉ ወርሮ በሎቹ የሚያደርሱት ግድያና ጥቃት ሐገሪቱን እንደ ማዕበል እየነወጣት ነዉ።ከካረቢክ አካባቢ ሐገራት እጅግ የደኸየችዉ ሐይቲ የፖለቲካ ግጭት፣ ግድያ፣ የአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎች ጠብ፣ የተፈጥሮ መቅሰፍትና በሽታ በየጊዜዉ በርካታ ሕዝብ ይፈጅባታል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ እጅግ የከፋዉ ሙስና፣ሕገ ወጥነትና የአስተዳደር ብልሹነት ደግሞ ሐገሪቱን ለወርሮበሎች  ጥቃትና ዘረፋ አጋልጧታል።የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አርየል ሔንሪይ ሥልጣን እንዲለቁ የሚፈልጉ የተለያዩ የወርሮ በላ ቡድናት በከፈቱት የተቀናጀ ጥቃት በግሪጎሪያኑ አምና ከ4,450 በላይ ሰዎች ገድለዋል።ካለፈዉ ጥር ወዲሕ ደግሞ ከ1550 በላይ ሰዉ ገድለዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲስ የሽግግር መንግስት ሲመሰረት ሥልጣን ለመልቀቅ ቃል ገብተዋል።

 

ኪቭ-የዩክሬን ጥያቄ፣ የሩሲያ ማስጠንቀቂያ

ምዕራባዉያን መንግስታት ለዩክሬን ጦር ኃይል ተጨማሪ የአየር መከላከያ እንዲሰጡት ዩክሬን በድጋሚ ጠየቀች።የሩሲያ ጦር ባለፈዉ አርብ በከፈተዉ መጠነ-ሠፊ የሚሳዬል ጥቃት በርካታ የዩክሬንን የሐይል ማመንጫ ተቋማትን አዉድሟል።በጥቃቱ የኃይል ማመንጫ ግድብና የኤሌክትሪክ መስመሮች ወድመዋል።ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ መብራት አጥቷል።ዛሬ በተሰየመዉ የዩክሬንና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተካፈሉት የዩክሬን መከላከያ ሚንስትር ሩስቶም ኡሜሮቭ ጦራቸዉ የአርቡን ዓይነት ጥቃት መከላከል እንዲችል ምዕራባዉያን መንግስታት ተጨማሪ የዓየር መከላከያ መሳሪያ ሊያስታጥቁት ይገባል።የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ትናንት ለጦር አዛዦቻቸዉ እንደነገሩት ግን  ምዕራባዉያን መንግስታት በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን F16ን የመሰለ ተጨማሪ ጦር መሳሪያ ከሰጠች የሩሲያ ጦር ኢላማ እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል።

«ኤፍ 16ን ለዩክሬን ሥለማስታጠቅ እየተወራና አብራሪዎች እየሰለጠኑ መሆኑም እየተነገረ ነዉ።ከማንም በላይ የምታዉቁ ይመስለኛል።ለዩክሬን  ኤፍ 16 ቢሰጧት የጦር ግንባሩን ሁኔታ አይለዉጠዉም።ልክ ታንኮቻቸዉን ብረት ለብስ ተሽከርካሪዎቻቸዉንና ሚሳዬል ማወንጨፊያዎቻቸዉን እንዳወድምናቸዉ ሁሉ አዉሮፕላኖቻቸዉንም እናወድማቸዋለን።

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
Mittelmeer | Asylreform in der EU
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።