1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንጽህና መጠበቂያዋ "ብርቄ" ባልዲ

ዓርብ፣ መስከረም 21 2014

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ድረስ በርካታ ሴት ተማሪዎች በወር አበባ መቀበያ እጦት ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው እንደሚገኙ ችግሩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ይናገራሉ። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በዚህ ዓመት ሶስት ያገባኛል የሚሉ አካላት «አበባ አየሽ ወይ? የሚል የንፅህና መጠበቂያ የማዳረስ ዘመቻ ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/418ra
Birke Äthiopien, Ethiopia, Birke, Jegnit, I care
ምስል icare_power_period

ሴት ተማሪዎች በወር አበባቸው የተነሳ ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ለማበረታታት እና ለማገዝ በሚል ሶስት ጉዳዮ ያገባኛል ያሉ አስተባባሪዎች «አበባ አየሽ ወይ?» የሚል እንቅስቃሴ ጀምረዋል። አለማቸው በዚህ በተያዘው 2014 ዓ.ም በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ለሚገኙ 50,000 ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያዎችን ማቅረብ ነው። የንጽህና መጠበቂያዋ ብርቄ ትባላለች። « ውስጧ ሳሙና፣ ፊሽካ፣ 4 የወር አበባ መቀበያ እና ፓንት ይዛለች» ትላለች ሚካል ማሞ።  ሚካል ከዚህ እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች አንዷ ስትሆን የአደይ የሚታጠብ የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ መስራች ናት። የተለያዩ ቀለማት ያላት የብርቄ ፕላስቲክ ባልዲ ውስጥ ፊሽካ መክተት ያስፈለገበት ምክንያት « እህቶቻችን ለመፀዳዳት በሚወጡበት ሰዓት ጾታዊ ትንኮሳ እንዳይደርስባቸው፣ አውሬ እና የተለያዩ ጥቃቶችን በጩኸት ለማባረር ነው» የምትለው መልሶ መጠቀም የሚችል የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ መስራች ሚካል  የወር አበባ መቀበያ ሞዴስ ችግር በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ብቻ ሳይሆን በከተማ ውስጥም በሰፊው እንዳለ ታስረዳለች።  ስለሆነም እነዚህን የንፅህና መጠበቂያዎች እስካሁን በማረሚያ ቤቶች፣ ተፈናቃዮች በሚገኙበት እና በትምህርት ቤቶች እንዳከፋፈሉ ወጣቷ ለዶይቸ ቬለ ገልፃለች። 

 Birke Äthiopien waschbare Binden
ምስል M.Mamo

ሴት ተማሪዎች እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ሳይቸገሩ በወር አበባ ጊዜ ሊጠቀሙበት የሚችሉት የንፅህና መጠበቂያ ፓኬጅ ማለትም የአንድ ብርቄ ባልዲ ዋጋ 5 ዶላር ወይም 220 ብር ገደማ ነው። አስተባባሪዎቹ እስካሁን ከማህበረሰቡ እያገኙ ያሉትም ድጋፍ አስደሳች እንደሆነ ይናገራሉ። ከብርቄ መስራቾች አንዱ የሆነው የጀግኒት እንቅስቃሴ አስተባባሪ እና የበጎ ፍቃድ አምባሳደር የሆነችው አርቲስት ፀደኒያ ገብረ ማርቆስ ለረዢም ጊዜያት በተለይ ከዚህ ከንጽህና መጠበቂያ እጦት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ እየሰራች ትገኛለች። በዚህ ስራዋ የታዘበችው አንዱ ነገር በርካታ ሴቶች በወር አበባ መቀበያ እጦት ምክንያት መሠረታዊ ከሆነው የትምህርት ገበታቸው እየተስተጓጎሉ መሆኑን ነው። ስለሆነም ሴት ልጆች በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ እና የበታችነት ስሜት እንዳይሰማቸው ከማህበረሰቡ ባሻገር መንግሥት በዋናነት ሊሰራባቸው የሚችሉ በርካታ ነገሮች አሉ ትላለች። « የንፅህና መጠበቂያ እና ለንፅህና መጠበቂያ የሚውሉ ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ መሆን አለባቸው። » ስትል የምታሳስበው ጸደንያ ይህም እስኪሆን ድረስ «የንፅህና መጠበቂያ ለሴት ተማሪዎች ልክ እንደ ደንብ ልብስ መሰጠት አለበት»።

«ባለፈው ዓመት አንድ ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውሉ የወር አበባ መቀበያዎችን ነበር ስናሰራጭ የነበረው» የምትለው አርቲስት ፀደንያ » ከዋጋ እና አካባቢን ከመበከል አኳያ አዋጪ ሆኖ ስላልተገኘ ዘንድሮ ትኩረታቸውን ታጥቦ አገልግሎት ላይ የሚውሉ የንፅህና መጠበቂያዎች ላይ እንዳደረጉ ለዶይቸ ቬለ አስረድታለች። ሌላው ደግሞ መገልገያዎችን ከመለገስ ባሻገር የማነቃቃት ስራ ላይ እየተሰራ እንደሆነም ገልፃልናለች።  አርቲስት ጸደንያ እንደምትለው ከሆነ  ኢትዮጵያ ውስጥ በወር አበባቸው የተነሳ ከ 30 እስከ 50 ቀናት ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩ ሴት ተማሪዎች አሁንም ድረስ አሉ። « ወደ ኋላ ሴቶች ለምን ቀሩ ብለን ስንጠይቅ ከጀርባቸው ያለቸውን ጉዳዮች ሁሉ ማሰብ ያስፈልጋል።» ስትልም ፀደንያ የታዘበችውን ትናገራለች።
የ I CARE ንቅናቄ አስተባባሪ ማህሌት ዘለቀ እና የጀግኒት ንቅናቄ መስራች ማራኪ ተስፋዬ የንጽህና መጠበቂያ መገልገያዎችን የያዘችው የብርቄ ባልዲ መስራቾች ናቸው። ማህሌት ብርቄን እንዴት እንደመሠረቱ ስታስረዳ የእሷ እና የማራኪ አላማ አንድ አይነት ሆኖ ስላገኙት እና ላለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ነገር ሲሰሩ ስለነበር በጋራ ብርቄን ለማዘጋጀት ወስነዋል። የንጽህና መጠበቂያዋን ብርቄ ያሉበት ምክንያት ደግሞ « የወር አበባ መቀበያ ብርቃችን ስለሆነ ነው። 75 በመቶ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ሴቶች የወር አበባ መቀበያ ማግኘት ካልቻሉ ብርቅ ስለሆነ ነው። » በማለት 

Äthiopien Artist Tsedenya Gebremarkos
ምስል privat
Birke Äthiopien, Ethiopia, Birke, Jegnit, I care
ምስል icare_power_period

የወር አበባ መቀበያዎች የቅንጦር እቃዎች ናቸው።» ትላለች ማህሌት። እስካሁን  በአካል ተገናኝተው የማያውቁት እነዚህ ባለራዕይ ወጣቶች በአሁኑ ሰዓት ሁለቱም  ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይገኛሉ። ይህም ዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ ለጋሾች ጋር ይበልጥ ለመስራት እድሉን አስፍቶላቸዋል። ቻይና ሀገር ዓለም አቀፍ ንግድ እና ኢኮኖሚ ያጠናችው ማህሌት በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ጊዜዋን ለመሰረተችው  I CARE ንቅናቄ ስራ እያዋለች ትገኛለች።  የወር አበባ መቀበያ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን በርካታ ጉዳዮ ይመለከተናል የሚሉ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ዘመቻ ቢያደርጉም እስካሁም በመንግስት ደረጃ ዋጋ አለመተመኑ ነጋዴው በሚፈልገው ዋጋ እንዲሸጥ አድርጓል የምትለው I CARE ንቅናቄ አስተባባሪ ማህሌት እንደሷ ቢሆን የወር አበባ መቀበያ አቅም ለሌላቸው ሴቶች በነፃ መታደል ነበረበት። « የወር አበባ መቀበያ ሴት ልጆች ባለማግኘታቸው ለሰውነት የማይመች ነገር ይጠቀማሉ፤ ካርቶን፣ ዓመድ የሚጠቀሙ ሴቶች አሉ፣ የሚተኙበትን ፍራሽ ቦጭቀው ፓንታቸው ላይ የሚያደርጉ ሴቶች አሉ» ስትል የችግሩን ክብደት እና የፍትሄ ይሆናል የሚለውን ሀሳብ ትገልፃለች። 

ዘገባውን በድምፅ ያገኙታል።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ