1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መቀሌ ዉስጥ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች ተደበደቡ

ዓርብ፣ መጋቢት 27 2016

ለዩኒቨርሲቲው በተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረባቸው፥ ከዩኒቨርሲቲው ምላሽ ባለማግኘታቸው ደግሞ ቅሬታቻው ለማሰማት ሰልፍ መውጣታቸው ይገልፃሉ። ተማሪዎቹ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉ ወደ የከተማው ማህል ክፍል ጉዞ ላይ በነበሩበት ወቅት ጥይት በመተኮስ፣ በድብደባ እና አፈሳ ፖሊስ ሰልፉን በሐይል መበተኑ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4eToi
የመቐለ ፖሊስ መምርያ ፅሕፈት ቤት ሐላፊ ኮማንደር አንድነት ነገሰ
የመቐለ ፖሊስ መምርያ ፅሕፈት ቤት ሐላፊ ኮማንደር አንድነት ነገሰምስል Million Haileselasie/DW

መቀሌ ዉስጥ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች ተደበደቡ

 

ዛሬ ረፋድ 4 ሰዓት ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ አሪድ ግቢ ተነስተው ያላቸው ቅሬታዎች ለማሰማት ወደ መቐለ ከተማ ጎዳናዎች ይጓዙ የነበሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች ፖሊስ በወሰደው የሐይል እርምጃ በርካታ ተማሪዎች አካላዊ ጉዳት ሲደርስባቸው፥ ሌሎች ታስረዋል። እነኚህ በተለያዩ ችግሮች ለዓመታት ትምህርታቸው ሲስተጓገል የነበረ እና ዘንድሮ ሊመረቁ ይጠብቁ የነበሩ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፥ ሌላ ተጨማሪ ዓመት መማር እንደሚጠበቅባቸው ከተገለፀላቸው በኃላ ለዩኒቨርሲቲው በተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረባቸው፥ ከዩኒቨርሲቲው ምላሽ ባለማግኘታቸው ደግሞ ቅሬታቻው ለማሰማት ሰልፍ መውጣታቸው ይገልፃሉ። ተማሪዎቹ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉ ወደ የከተማው ማህል ክፍል ጉዞ ላይ በነበሩበት ወቅት ጥይት በመተኮስ፣ በድብደባ እና አፈሳ ፖሊስ ሰልፉን በሐይል መበተኑ ገልፀዋል። በሰልፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች እየተሳተፉ የነበሩ ሲሆን፥ ከእነዚህ መካከል 10 ተማሪዎች እንደታሰሩባቸው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ለዶቼቬለ ገልፀዋል።የሰልፉ ተሳታፊ ከነበሩ ተማሪዎች መካከልየኢንጅነሪንግ ተማሪዋ ብርክቲ ገብረሕይወት "ዩኒቨርስቲ ከገባን 8 ዓመት አድርገናል። በእኛ ምክንያት ሳይሆን በመንግስት በጦርነቱ መስተጓጐል ገጥሞናል።እሱ ታሳቢ ተደርጎ እንዲካካስ ግዜው ነው የምንጠይቀው" የምትል ሲሆን ይህ ለማለት ሰልፍ ሲወጡ ከባድ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ተናግራለች።

 

ሌላ አስተያየቱ የሰጠን ስሙ ሊጠቀስ ያልፈለገ ተማሪ በበኩሉ "አስር ተማሪዎች ታስረውብናል። ድምፃችሁ አታሰሙም ተብለን ነው የታፈንነው" ብሏል። የመቐለ ፖሊስ መምርያ ፅሕፈት ቤት ሐላፊ ኮማንደር አንድነት ነገሰ በበኩላቸው ሰልፍ ለማድረግ አስቀድሞ ለፖሊስ ማሳወቅ ይገባል ይህ ስላልሆነ እንዲበተን አድርገናል ብለዋል።  ኮማንደር አንድነት "ለመቐለ አስተዳደር ካላሳወቅክ፣ መብት ስለሆነ ብቻ ሰልፍ መውጣት አይቻልም። አንድ ስብሰባም ቢሆን አስተዳደር ማወቅ አለበት። ከህግ ውጭ የሚሄድ ካለ ሐይል እንጠቀማለን። ይህ ግልፅ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የመቐለ ፖሊስ  ከተማ በከፊል (ፎቶ ከክምችት)
የመቐለ ፖሊስ ከተማ በከፊል (ፎቶ ከክምችት)ምስል Million Hailesilassie/DW

ቁጥራቸው ባይጠቅሱም የፖሊስ አዛዡ የታሰሩ ተማሪዎች መኖራቸው አረጋግጠውልናል። የመቐለ ዩኒቨርሰቲ አመራር አባል የሆኑት ዶክተር ሀይለኪሮስ ስብሃት በበኩላቸው የተማሪዎቹ ጥያቄ ለመፍታት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ንግግር እንደሚደረግ ገልፀውልናል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ