1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳግም ኮሌራ በሀረሪ ክልል ሕይወት አጠፋ

ረቡዕ፣ መጋቢት 4 2016

በሀረሪ ክልል በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ እስከትናንት ድረስ ቢያንስ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ተገልጧል ። ከሰባ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ዐስታውቋል ። 31 ሰዎች ታክመው ወደ ቤታቸውመ መመለሳቸውም ተገልጧል ።

https://p.dw.com/p/4dT5l
Hyänen Äthiopien
ምስል Reuters/T.Negeri

በኮሌራ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ተገልጧል

በሀረሪ ክልል በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ እስከትናንት ድረስ ቢያንስ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ተገልጧል ።  ከሰባ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን የክልሉ ጤና ጽ/ቤት ዐስታውቋል ። 31 ሰዎች ታክመው ወደ ቤታቸውመ መመለሳቸውም ተገልጧል ።  ለወረርሽኙ መከሰት ከዐርብ ጀምሮ በአካባቢው በካፊያ መልኩ መጣል የጀመረው ዝናብ የፍሳሽ ቆሻሻዎችን በደንብ ሳያስወግድ ይበልጥ ለብክለት በር መክፈቱ ሳይሆን እንዳልቀረ የሀረሪ ክልል ጤና ጽ/ቤት ገልጿል ። ከሁለት ሳምንት በፊትበጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲም የኮሌራ ወረርሺኝ ተከስቶ  ከአራት መቶ የማያንሱ ተማሪዎች መያዛቸውን በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች ስለ መናገራቸው በዶይቼ ቬለ መዘገቡ ይታወሳል ።  የድሬዳዋ ወኪላችን መሳይ ተክሉ ቀጣዩን ዘገባ ልኮልናል ።

በኮሌራ በሽታ ሦስት ሰዎች ሞተዋል

የሀረሪ ክልል ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ ለዶይቼ ቬለ (DW) በስልክ በሰጡት መረጃ፦ በክልሉ ከተከሰተ ቀናት አስቆጥሯል ባሉት የኮሌራ በሽታ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ፤ ከሰባ በላይ ሰዎች መያዛቸውን እንዲሁም የተወሰኑት ህክምና አግኝተው ወደ ቤት መመለሳቸውን ገልፀዋል።

ወረርሽኙ የተቀሰቀሰበት ዋንኛ መንስኤ በላብራቶሪ ምርመራ እንደሚረጋገጥ የጠቀሱት ኃላፊው ነገር ግን ባልተዳረሰ መልኩ ካለፈው አርብ ጀምሮ ማካፋት የጀመረው ዝናብ ለተፈጠረው ብክለት መንስዔ ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በሐረሪ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመከላከል
ቀደም ባሉት ጊዜያት በሐረሪ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመከላከል የውኃ ጉድጓዶች የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ እንደነበር ተገልጧል ። ፎቶ፦ ከክምኅት ማኅደርምስል Mesay Teklu/DW

ሁለት መቶ ያህል ሰዎች ሊታከሙበት የሚችል ጊዜያዊ ህክምና መስጫ ማቋቋምን ጨምሮ በክልሉ ደረጃ የወረርሽኙን ጉዳት ለምከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አቶ ያሲን ተናግረዋል። የከተማይቱ ነዋሪ የሆኑ አንድ አስተያየት ሰጪ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ብለዋል። በሀረሪ ክልል ከወራት በፊት በተከሰተ ተመሳሳይ የኮሌራ ወረርሽኝ ጉዳት መፍረሱን መዘገባችን ይታወሳል ።

የወረርሽኙ መከሰት እና ያስከተለው ጉዳት

የሀረሪ ክልል ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ  አቶ ያሲን አብዱላሂ እስከ ትናንት ባሉት ተከታታይ አራት ቀናት ከሰባ በላይ ሰዎች በኮሌራ ተይዘው ወደ ህክምና ተቋማት መምጣታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ታማሚዎቹ የክልሉ ተጎራባች ከሆነው የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን እና ከሀረሪ ክልል መሆናቸውንም ኃላፊው አስረድተዋል። በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ሕይወታቸውን ካጡ ሦስት ሰዎችም አንዱ ከሀረር ሲሆን፤ ሁለቱ ከምስራቅ ሀረርጌ ዞን አዴሌ እና ፈዲስ አካባቢዎች ህክምና ለማግኘት የመጡ ሰዎች መሆናቸው ተገልጧል ።

ጥንታዊቷ የሐረር ከተማ
ጥንታዊቷ የሐረር ከተማምስል Mesay Tejkelu/DW

እስካሁን ባለው ደረጃ በበሽታው ተይዘው የሚመጡ ሰዎች በክልሉ ባሉ ጤና ጣቢያዎች እና በሆስፒታል ደረጃ ህክምና እያገኙ መሆናቸውን ያስረዱት የክልሉ ጤና ጽ/ቤቱ ኃላፊ በወረርሽኙ ሳቢያ የከፋ ሁኔታ ቢያጋጥም በሚል ሁለት መቶ ያህል ሰዎችን መያዝ የሚችል ጊዜያዊ የህክምና መስጫ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

ሰፊ የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚታይባቸው የምስራቅ ሀገሪቱ ተጎራባች አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ  መከላከል የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልገው ብዙዎች ያነሳሉ።

መሳይ ተክሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር