1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድርቅ በአፋር ክልል ያስከተለው አደጋ

ማክሰኞ፣ ጥር 28 2016

በቅርቡ የተከሰተው ድርቅ እንዲሁም የሰሜኑ ጦርነት ጥሎት ባለፈው አደጋ ምክንያት 40 በመቶ የክልሉ ሕዝብ አስቸኳይ የምግብና የውኃ አቅርቦት ፈላጊ እንዲሆን ማድረጉ ተገለፀ። የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት እስከ ስድስት መቶ ሺህ ያህሉ የክልሉ ሕዝብ በድርቅ ምክንያት ለችግር መዳረጉን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4c6Gs
ድርቅ በአፋር ያስከተለው አደጋ 
ድርቅ በአፋር ያስከተለው አደጋ ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

በአፋር ክልል ስድስት መቶ ሺህ ያህሉ ሕዝብ በድርቅ ችግር ላይ ወድቋል

ድርቅ በአፋር ያስከተለው አደጋ 

በቅርቡ የተከሰተው ድርቅ እንዲሁም የሰሜኑ ጦርነት ጥሎት ባለፈው አደጋ ምክንያት 40 በመቶ የክልሉ ሕዝብ አስቸኳይ የምግብና የውኃ አቅርቦት ፈላጊ እንዲሆን ማድረጉ ተገለፀ። የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት እስከ ስድስት መቶ ሺህ ያህሉ የክልሉ ሕዝብ በድርቅ ምክንያት ለችግር መዳረጉን ባለፉት ሦስት ሳምንታት በስድስት ዞንኖች ውስጥ በሚገኙ 15 ወረዳዎች ላይ በተከናወነ የድርቅ ዳሰሳ ጥናት መለየቱን ለዶቼ ቬለ አስታውቋል። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን በተለይም ለዶቼ ቬለ እንዳሉት በተደጋጋሚ እና በተደራራቢ በተስተዋሉ የተፈጥሮ እና ሰው ያስከተላቸው ችግሮች ምክንያት በማህበረሰቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል። 

ምን ያህል ሕዝብ የጉዳት ሰለባ ሆኗል? 

ከሁለት ሚሊዮን ያህሉ የአፋር ሕዝብ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው በድርቅ ምክንያት ቀጥተኛ የጉዳት ሰለባ መሆኑን የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ በተለይ በሰሜናዊ ዞን እና በዞን አራት ውስጥ መሠረታዊ አገልግሎቶች ጦርነት እንዲቋረጡ ከማድረጉም በላይ አሁን ከሞት ከሰተው ድርቅ ተዳምሮ የሕዝቡን አኗኗር ለፈተና መዳረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል።
"ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ የሀገር ውስጥ እና ዓለምአቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በማቀናጀት የድርቅ ዳሰሳ ጥናት በስድስት ዞንኖች በ15 ወረዳዎች ላይ ተከናውኗል"። ብለዋል።
ወረርሽኝ ሌላኛው የእርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር እንዲያሻቅብ እያደረገ የሚገኝ ችግር መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል። ኮሌራ ዋናው መሆኑንም አስታውቀዋል። በተደጋጋሚ እና በተደራራቢ የተፈጥሮ እና ሰው ያስከተላቸው ችግሮች ምክንያት በማህበረሰቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል የሚሉት ኃላፊው ተቋርጦ የቆየው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እርዳታ ሊጅመር ምዝገባ ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል። "227 ሺህ ሕዝብ ከብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር የቅድሚያ ቅድሚያ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ተለይተው እርዳታ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ ነው" ከብሔራዊ ተቋሙ የተመደበው የእርዳታ ኮታ አብዛኛው ድጋፉን ወደሚሹት ወረዳዎች መሰራጨቱን ገልፀዋል። 

በአፋር ጦርነት ያደረሰው ጉዳትም አሁን ድረስ አልሻረም 

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ክፉኛ ከጎዳቸው እና ከፍተኛ ሰብዓዊ እና የቁስ ውድመት ካደረሰባቸው ክልሎች አንዱ አፋር ክልል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ድርቅን "ድርቅ በተለያዩ አከባቢዎች ተከስቷል፡፡ ድርቁ የሰው ሕይወት እንዳይቀጥፍ ተባብረን መስራት አለብን" ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ 
ሸዋዬ ለገሠ