1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሊንከን ጉብኝት፤ የቤቶች ፈረሳና እና ከተማ አትገቡም

ዓርብ፣ መጋቢት 8 2015

በአዲስ አበባ የቤቶች ፈረሳ በቅጽበት ቤት አልባ ያደረጋቸው ነዋሪዎችን በእንባ አራጭቷል፤ ሕጻናት ተማሪዎች፤ እናቶችና አረጋውያንንም ለጎዳና መዳረጉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች አነጋጋሪ ሆኗል ። የከተማዪቱ ከንቲባ «ከፍተኛ ፍልሰት»ን «መንግሥትን በመጣል በኃይል ሥልጣን» ከመቆጣጠር ጋር አያይዘው መናገራቸው በርካቶችን አስቆጥቷል ።

https://p.dw.com/p/4Oqaz
Äthiopien | Addis Abeba |  Rathaus
ምስል Seyoum Getu/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በአዲስ አበባ የቤቶች ፈረሳ በቅጽበት ቤት አልባ ያደረጋቸው ነዋሪዎችን በእንባ አራጭቷል፤ ሕጻናት ተማሪዎች፤ እናቶች እና አረጋውያንንም ለጎዳና መዳረጉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኗል ። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ «ከፍተኛ ፍልሰት» ሲሉ የገለጡት ወደ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ የሚደረገው ጉዞ «መንግሥትን በመጣል በኃይል ሥልጣን ለመቆጣጠር ያለመም ነው» ማለታቸው በርካቶችን አስቆጥቷል ። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ የሚመሩት መንግስት እና ሕወሓት ፕሪቶሪያ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረጉ በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል ። ጉብኝቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው ። 

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አንቶኒ ብሊንከን ከውጭ ጉዳይና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጋር
የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አንቶኒ ብሊንከን ከውጭ ጉዳይና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጋርምስል Ethiopian Foreign Ministry

ከተማ አትገቡም ክልከላ
በዚሁ በያዝነው ሳምንት የአዲስ አበባ ምክር ቤት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ሲጀምር የመስተዳድሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተናገሩት በርካቶችን አስቆጥቷል ። ንግግሩ የሚያስከትለው ጣጣ እና አደጋም እጅግ ያሠጋናል ያሉ ብዙዎች ናቸው ። ከንቲባዋ በንግግራቸው፦ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ዳርቻዎች ወደ ከተማዋ ይደረጋል ያሉት «ፍልሰት» የከተማዋ የፀጥታ ስጋት ወደ መሆን መሸጋገሩን ለምክር ቤት አባላት ገልፀዋል ። «ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግሥትን በመጣል በኃይል ሥልጣን ለመቆጣጠር ያለመም ነው » ነው ሲሉም ተደምጠዋል ። ይህ የከንቲባዋ ንግግር በማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች እና ፖለቲከኞች ዘንድ በብርቱ ተወቅሷል ።

እንዳገር ሣኅለ ማርያም የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ስጋት ምናምን ፈፅሞ ኖሮ አይደለም» ሲሉ ጽፈዋል ። ሁኔታውንም፦ «ቀጥታ የጥላቻ ቅስቀሳና ትርክት ፈጠራ ነው » በማለት አደጋው ለሁሉም መሆኑን ገልጠዋል ።  «… አያ-ጅቦ፤ ሳታመኻኝ ብላኝ … እንዳይሆን ነገሩ!!!…» ያሉት ደግሞ ወንዴ ዘውዴ ናቸው ትዊተር ላይ ። በሕይወት ጥላሁን የተባሉ ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው በእንግሊዝኛ ባሰፈሩት ጽሑፋቸው «እውነታውን ፈጽሞ መደበቅ አይችሉም» ብለዋል ። 

«የሚገርመው አዲስ አበባ ያለው ባለስልጣን በሙሉ ከተለያየ በተለይ ከኦሮሚያ እና ደቡብ ፈልሶ የመጣ» ነው፤ «ከከንቲባዋ ጀምሮ» ሲሉ የጻፉት ደግሞ ገብረ ማርያም ናቸው። አብዱ ቃሃር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው፦ «ዘንድሮ ብዙ እንሰማለን አዲስ አበባ ለመግባትም ቪዛ ሳንጠየቅ አንቀርም፤ አረ ወገን ምንድነው እየሆነ ያለው?» በማለት ምሬት እና ሥጋታቸውን በጽሑፍ አንጸባርቀዋል ። 

የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ
የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታምስል Solomon Muchie/DW

ፍጹም ተፈሪ በበኩላቸው ፌስ ቡክ ላይ ቀጣዩን አጠር ያለ ጽሑፍ አስፍረዋል ። «እንደኔ ሀሳብ ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ፍልሰት ለመቀነስ ሌሎች ከተሞች(እንደ ጎንደር፤ ደሴ፤ ድሬዳዋ፤ ሰመራ፤ አምቦ፤ ሆሳዕና እና ሌሎች የመሳሰሉ ከተሞች) ላይ ኃይለኛ ትኩረት መስጠት፤ በደንብ መልማት፤ ሳቢነታቸውን መጨመር እና ጠንካራ ኢንቨትመንት መደረግ አለበት»ም ብለዋል።

«ክብርት ከንቲባችን አዳነች አቤቤ በእውቀት የላቀች፤ ብስለትን የተላበሰች የፅናት እና የጥንካሬን ጥግ ያየንባት ትጉህ ከንቲባችን ናት» ሲሉ የጻፉት ደግሞ ቤላ ሚላን ናቸው ትዊተር ላይ ። አርምሞ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ የከንቲባዋን ንግግር፦ «የጥላቻ ንግግር» ሲሉ በእንግሊዝኛ በአጭሩ ጽፈዋል ።

በርካቶች አደገኛ ያሉትን የከንቲባዋን ንግግር በተመለከተ የተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫ አውጥተዋል ። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የንቲባዋን ንግግር «አደገኛ፤ ከፋፋይ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ» ብሎታል።  «አገረ መንግሥቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የዓለም አቀፍ ወንጀል ጥሪ ነው» ሲልም ጉዳዩን በጽኑእ ተቃውሞታል ።

ወደ አዲስ አበባ ከተማ እንኳን ደህና መጡ በእንግሊዝኛ
ወደ አዲስ አበባ ከተማ እንኳን ደህና መጡ በእንግሊዝኛ ምስል Seyoum Getu/DW

እናት፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ የተባሉ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ደግሞ የከንቲባ አዳነች አቤቤ ንግግር «የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት የሚነፍግ፣ በከፍተኛ ሴራና ፍረጃ ለበለጠው የዘር ፍጅት የሚያመቻችና ዜጎችን የማሸማቀቅ አካል ነው» በማለት አውግዘውታል ።

ቤት ፈረሳ፥ ጎዳና መውደቅ እና የምንዱባን እንባ
በአዲስ አበባ ከተማ ላለፉት አራት እና አምስት ዓመታት ሔድ መለስ ሲል የቆየው የቤቶች ፈረሳ ከሰሞኑ በመዲናዪቱ እምብርት እና በዙሪያዋ ተጠናክሮ ቀጥሏል ።

በሲሚንቶ እና በአርማታ የተገነቡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቤቶች በቡልዶዘር ሲደረመሱ የሚያሳይ አጠር ያለ ቪዲዮ በማያያዝ ግራ መጋባታቸውን በትዊተር ጽሑፋቸው ያሰፈሩት ኩሱራ ባሮ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው ። «እኔ የሚገርመኝ» ይላሉ ኩሱራ «እኔ የሚገርመኝ ሕገወጥ የመሬት ወረራ ይላሉ። ካርታ ያላቸው ዘመን የተሻገሩ ቤቶችም ሌሎችም በሕጋዊ መንገድ የተገነብ ናቸው። የሚገርመው የአማራ እየተለየ የሚፈርስበት» ብለዋል ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፈረሱ ቤቶች ከፊል ገጽታ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፈረሱ ቤቶች ከፊል ገጽታምስል Seyoum Getu/DW

ፒን ትሩዝ በሚል የትዊተር ተጠቃሚ በእንግሊዝኛ ያሰፈሩት ጽሑፍም በግንብ የታጠሩ ግቢዎችና ቤቶች በቡልዶዘር ሲፈርሱ የሚታይበት ቪዲዮ ተያይዞበታል ። የቤት ፈረሳውንም «ሕግ በማስከበር ስም» የሚፈጸም «ድሆች ላይ ያነጣጠረ ዘር ተኮር» ብለውታል ። «በማንኛውም መስፈርትም ተቀባይነት የሌለው» ሲሉ ገልጠውታል ።

ተመሳሳይ የቪዲዮ መልእክት ያያዙት ልጅ ብሩክ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «አሁን ይሔ አያሣብድም ማርያምን ጥሬ ቆርጠሞ የሠራውን ቤት ፈረሳ» በማለት ጽፈው በሁለቱም ዐይኖቹ የሚያነባ ምልክት አስፍረዋል። «የሰው ሀገር መንግስት ቤት ለሌላቸው ቤት እዬሠራ ይሰጣል፤ የኛ መንግስት ከሞቀ ቤታቸው እያባረረ ጎዳና ተዳዳሪ ጥገኛ ያደርጋል » ሲሉም ጽሑፋቸውን ቋጭተዋል ።

ዓለማየሁ ፍቅሬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «የበኩላችንን የልማቱ ተባባሪ እንሁን» ሲሉ ጽፈዋል ። «በእርግጥ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን የከተማዋ ውበትም እየጨመረ በመሆኑ፤ የተሠሩ ሥራዎች ናቸውና ፈረሳው የተጀመረው በድንገት» አይደለም ብለዋል። «መንግሥት ቀደም ብሎ አሳውቆ አመቻችቶ በእቅዱ መመረት የጀመረ» ሲሉም ጠቅሰዋል ። «መውደቂያ አጣን ባዮች» ሲሉ የገለጧቸው ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎችን «መቸገራቸው ባያስደስትም በሕጋዊ መንገድ መኖርያ ፣ ካሳ ተከፍሏቸው ጊዜ ተሰጥቷቸው መንግሥት የተቻለውን ያህል ያደረገ» ነው ብለዋል ። «የከተማውን የልማት ዕድል ለመጠቀም ያስችለን ዘንድ በጥገኝነ ሲኖሩ የነበሩ ደግሞ እንደነበሩ ወደ ለማ ሰፈር ተሸጋሽገው ወይም ቀይረው በጥገኝት እንዲቀጥሉ የበኩላችንን የልማቱ ተባባሪ እንሁን» ሲሉ ጽሑፋቸውን ደምድመዋል ። 

«የኢትዮጵያን ጉድ ተመልከቱ ። ከተማ አሳመርን እያሉ ሕዝብን ወደ ጎዳና ይጥላሉ፤ አየ ስልጣኔ ።» ይህን አስተያየት የሰጡት አዲስ አበባው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ። ሙለር ገብ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው፦ «ሕገወጥ ግንባታ ይፍረ» ሲሉ ጽፈዋል ። ኦቢሪ ሳሚ የተባሉ ሌላ የፌስ ተጠቃሚም፦ «ሕገ ወጥ ቤት መፈረስ ችግር የለውም ። መንግስትም ለተፈናቀይ ዜጎች በምትኩ ለነሱ መጠለያ የምሆን ቦታ ያመቻቻል የምል ግምት አለኝ » ብለዋል ። 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፈረሱ ቤቶች ከፊል ገጽታ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፈረሱ ቤቶች ከፊል ገጽታምስል Seyoum Getu/DW

በአጭሩ፦ «እንግዲህ መቻል ነዉ» ያሉት ደግሞ አዲሱ ዓማን ናቸው ፉስቡክ ላይ ። ዴቭ ተክሉ ፌስቡክ ላይ፦ «የጊዜ ጉዳይ ነው ! የጊዜ እንጂ የሰው ጉልበተኛ የለም!!!» ሲሉ ጽፈዋል ። ጌታቸው ማሞ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «የግፎች ሁሉ ግፍ! እግዚአብሔር ይመለከታል፣ በሕገወጥ ሽፋን የሚሰራው የጥላቻ ሥራ!» ነው ብለዋል ።  

የብሊንከን ጉብኝት

ከሰሜን ኢትዮጵያ አስከፊ ጦርነት በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አንቶኒ ብሊንከን ረቡዕ መጋቢት 6 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ ጎብኝተዋል ። ከውጭ ጉዳይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተነጋግረዋል። ከጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ፤ ለብቻ ደግሞ ከሕወሓት መሪዎች ጋርም መወያየታቸውን በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አንቶኒ ብሊንከን የአንድ ቀን ጉብኝታቸውን አጠናቀው በቦሌ አየር ማረፊያ ሽኝት እንደተደረገላቸው ትዊተር ገጹ ላይ ጽፏል ።

«የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ማለት ይሄ አይደል» ይላሉ ጋሸው ሶሌላ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ። «ጦርነትና መፈናቀል ሲኖር በደስታ ይረዱናል። አገሪቷን የሚለውጥ ልማት ግን መስማትም መርዳትም አይፈልጉም። እንደ አባይ ግድብ አይነት ሀገር በቀል ግዙፍ ኘሮጀክት ላይ ስንት ሴራ ሲያሰሩ እንደነበር አንረሳውም። በርዳታ ብዛት የጠብታ ያክል መፍትሄ አይመጣም። ይልቁንስ መንግስት የዜጎችን መፈናቀል ማስቆምና ከእንደዚህ አይነት የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት መጠበቅ ነው ያለበት» ብለዋል ።

የዩናይትድ ስቴትስ ውች ጉዳይ ልዑካን ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ባልደረቦች ጋር
የዩናይትድ ስቴትስ ውች ጉዳይ ልዑካን ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ባልደረቦች ጋር ምስል Ethiopian Foreign Ministry

ዩናይትድ ስሬትስ ለኢትዮጵያ ለአስቸኳይ ርዳታ የሚውል ከ331 ሚሊየን ዶላር በላይየሰብአዊ ርዳታ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኗን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ይፋ አድርገዋል ። ይህን ውሳኔ በተመለከተ ፈጣን ነው ባቡሩ በሚል የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ሌላ ጥሩ ዜና» ብለውታል ።

«መቅደም ያለበት ተጠያቂነት ነው» ያሉት ሙለር ኃይሉ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ። «በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት» ወራሪዎች ያሏቸው ኃይላት «ከትግራይ ምድር ጠቅልለው ሊወጡ፤ መሰረተ ልማቶች ሊመለሱ፤ የተበደለ» መካስ አለበት ብለዋል። ሆኖም በጦርነቱ «ንፁሀን የጨፈጨፉ ፣ ሴቶች የደፈሩ፣ የእምነት ተቋማት ያቃጠሉ» ለሕግ መቅረብ እንዳለባቸው ገልጠዋል።

ሳሚ ደፋሩ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፦ «ትግራይን ጥሩ ነው መደገፋቸው ግን እሚገርመኝ አማራ እና አፋርን ግን መንግሥትም ሆነ አሜሪካ ሢጠሩት ሠምቸ አላቅም ጦርነቱ እኮ አፋር እና አማራ ላይ ነው የነበረው» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።

ብሩክ ዮናስ የውጭ ጉዳዩን ጉብኝት አስመልተው በፌስቡክ ገጻቸው ሲጽፉ፦ «ለሰላም ለፍቅር ያድርግልን አቦ...ጦርነት ፣ ጥላቻን ያርቅልን» ብለዋል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ